ለእሷ የክረምቱ ትርጉም ከሁሉም ይለያል፡፡ ጊዜና፣ ወቅቱን የምታየው በጥንቃቄ ነው፡፡ ሁሌም ዝናብና ቅዝቃዜው ጭቃና ጎርፉ ከሕይወቷ ይታገላሉ፣ ከኑሮዋ ይጋፋሉ፡፡ ሰማዩ ጠቁሮ ባጉረመረመ ቁጥር ከልብ ይከፋታል፡፡
ሽቅብ አንጋጣ በተመለሰች ጊዜ አንደበቷ አንዳች ነገር ሲያጉረመርም ይሰማል፡፡ ፈጣሪዋን ቀኑ ብራ እንዲሆን ትማፀናለች፡፡ ፀሀይ እንድትደምቅ፣ ዝናብ እንዳይመጣ ትለምናለች፡፡ ዝናቡ ከመጣ እንጀራዋ አይሰምርም፣ ውሎዋ አያምርም፡፡ መሬቱ ከራሰ ፣ ቦታው ከቀዘቀዘ እሷነቷ ይደበዝዛል፡፡ ውሎ ጨዋታዋ ይፈዛል፡፡
ለፋጡማ ኡስማን ይህ አይነቱ የዕለት ልመና ልምድ መሆን ከያዘ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ክረምቱ በጊዜው እንዳሻው ሊሆን ግድ ብሏል፡፡፡ ወቅቱ ነውና ዝናብ፣ ካፊያው፣ ጭቃ በረዶው ይፈራረቃል፡፡ እሷ ግን ይህ የተፈጥሮ ሕግ ያስጠላታል፡፡ ዝናቡን አትወደውም፣ ዳመናውን አትፈቅደውም ፡፡ ማልዶ ቀኑ ከጨለመ ስጋት ይገባታል፣ ሆድ ይብሳታል፡፡
ከዝናቡ ኋላ የምታየው ጅረት ያለፈችበትን መንገድ እያሳያት ነው፡፡ ያልጠራውን ድፍርስ ውሃ ከዕንባዋ ትመስለዋለች፡፡ ዛሬም ድረስ ዓይኖቿ ርጥብ ናቸው። በየሰበብ ምክንያቱ ለማልቀስ ፣ ከዕንባ ውሎ ለማደር አይቦዝኑም፡፡ ሁሌም ከዚህ ክረምት ማግስት የሚሆነውን ታስባለች፡፡ ነገዋ ያስጨንቃታል፡፡ ዕጣ ፈንታዋ ያሳስባታል።
ከዓመታት በፊት…
ልጅነቷ መልካም ነበር፡፡ እናቷን ያጣችው ገና በጠዋቱ ቢሆንም ተከፍታ አላደገችም፡፡ ታላላቆቿ እያሰቡላት፣ ለታናናሾቿ መከታ ሆና ዘልቃለች፡፡ የገጠር ሕይወት የኑሮዋ መሠረት ነው፡፡ እንደልጅነቷ ከማጀት ከጓዳው ያጣችው አልነበረም፡፡ ቤት ካፈራው ሳትነፈግ ፍቅር ተመግባ አድጋለች፡፡ የዛኔ ጭንቅ ትካዜን አታውቅም፡፡ በቤተሰቦቿ ትከሻ በታላላቆቿ ሃሳብ እንዳሻት መሆን መብቷ ነበር፡፡
በዕድሜዋ ከፍ ማለት ስትጀምር አርቃ ማሰብ ያዘች። ያደገችበት ቀዬ የኖረችበት መንደር በቂ አልመስል አላት፡፡ አዲስ አበባ እህቶቿ ይኖራሉ፡፡ ታላላቆቿ ናቸው። እነሱ ከቤት ሲወጡ ሰበብ ምክንያት ነበራቸው፡፡ ራሳቸውን መቻል፣ ኑሯቸውን መለወጥ ፈልገዋል፡፡
እህቶቿን ጨምሮ ሌሎች ዘመዶቿ ከከተማ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በኑሮ ተቀይረዋል፡፡ ትዳር ይዘው ልጆች ወልደዋል። ከመንደሩ ወጣቶች ጥቂት የማይባሉት ለፍቶ አዳሪ ናቸው። ወንዶቹ ለሥራ አይቦዝኑም፡፡ ሴቶቹ በአቅማቸው ይሮጣሉ። ጉልት የሚሰሩ፣ ጀብሎ የሚያዞሩ፣ ሱቅ የሚነግዱ ጥቂት አይደሉም፡፡ ከነዚህ መሀል አንዳንዶቹ አረብ ሀገር ተጉዘዋል፡፡
ፋጡማ ስለ አረብ ሀገር ጉዞ ብዙ ሰምታለች። ሁሌም ታሪክ ለጆሮዋ ሲደርስ ግን ተዥጎርጉሮ፣ ተለያይቶ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ጥሩ ገንዘብ፣ በቂ ጥሪት ይዘው እንደሚመለሱ ተነግሯታል፡፡ እነዚህኞቹ ሀገር ቤት ተመልሰው ቤት ይሰራሉ፣ ቤተሰብ ይጠቅማሉ፡፡ ለሌሎችም ይተርፋሉ፡፡
እንዲህ አይነቱ እውነት ለፋጡማ ውስጧን ይማርካል። እነሱን ስታስብ ስለራሷ ታልማለች። ስለወደፊት ኑሮዋ ታቅዳለች፡፡ ሠርታ ካገኘች፣ ለፍታ ካደረች ነገ ጥሪት ይኖራታል፡፡ ራሷን ጠቅማ ለሌሎች ትበጃለች፡፡ ለቤተሰብ ትተርፋለች፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ፋጡማ የአረብ ሀገር ሕይወት አደገኛ መሆኑ ይነገራታል፡፡ ብዙዎች ገንዘባቸውን ተነጥቀው፣ ጤናቸውን አጥተው ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ሕይወታቸውን የሚያጡ፣ ከፎቅ የሚወረወሩ፣ በፈላ ውሃ የሚቃጠሉም ብዙ ናቸው፡፡ በአእምሮ ህመም የሚፈተኑ፣ በጭንቀት የሚሰቃዩ ፣ የአልጋ ቁራኛ ሆነው ከሰው እጅ የወደቁ ጥቂት አይደሉም፡፡ ፋጡማ ይህን ሁሉ ስትሰማ ስታረጋግጥ ኖራለች፡፡
ባገኘችው አጋጣሚ ‹‹አረብ ሀገር ለእኛ መልካም ሆኖልናል›› ያሉትንም ቀርባ ጠይቃለች፡፡ የሚያውቁትን በጎነት ሁሉ ዘርዝረው ነግረዋታል፡፡ ገንዘብ መያዛቸውን፣ ሀብት ማፍራታቸውን፣ ተመላልሰው መሄዳቸውን ከመልካም አያይዘው በጎ መሆኑን ጠቁመዋታል፡፡
በዚህ ሕይወት ያለፉ አንዳንዶች ደግሞ የስፍራውን መጥፎነት በራሳቸው እማኝነት ሊያሳይዋት ሞክረዋል፡፡ ብዙ ወገኖች ገንዘብ ብለው ጤና ማጣታቸውን፣ ሕይወት መነጠቃቸውን አካል ማጉደላቸውን አሰድረድተዋታል፡፡ እነሱን ጨምሮ ባዶ እጃቸውን የተመለሱ በርካቶች አሁን ላይ ለሌላ ሥራ አቅም ጉልበት እንዳጡ፣ ተስፋ በቆረጠ አንደበት ነግረዋታል፡፡
አዲስአበባ…
ፋጡማ ኑሮን በአዲስ አበባ ስትጀምር ብዙ ጉዳዮች አሰበች፡፡ በሥፍራው ለመኖር ሠርቶ ማደር ግድ ይላታል። ከሰራች ራሷን መቻል፣ ሌሎችን ማገዝ አለባት። ሽማግሌው አባቷ ገጠር ናቸው፡፡ ለእሳቸው የአቅሟን አበርክታ ለመመረቅ፣ ለመመስገን መሥራት አለባት፡፡ አዲስ አበባ ለዚህ ሃሳቧ አልራቀም፡፡ ዘመዶቿ እንደሚተዳደሩት መስላ ለማደር ዕድል በእጇ ነው፡፡
ፋጡማና የከተማ ኑሮ ጥሩ ተላምደዋል፡፡ አሁን መውጫ መግቢያውን አውቃለች፣ ከብዙዎች ተላምዳለች፣ ባህርይዋን ያስተዋሉ መልካምነቷን ይወዱታል፡፡ ሰላምታዋ፣ አክብሮቷ ከበርካቶች እያግባባ ፣ እያስተዋወቃት ነው፡፡ እንዲህ መሆኑ ተመችቷታል፡፡ ከሰው መግባባት መላመዷ ሰላም አውሎ ይመልሳታል፡፡
እንደ ምኞት…
ፋጡማ አዲስ አበባ ከገባች ወዲህ ብዙ ሞክራለች፣ ከእህቶቿ አድራ ንግዱን፣ ሩጫውን፣ ሰርቶ ማደሩን አይታዋለች፡፡ ይህ ሁሉ የልቧን አላደረሰም፡፡ ቀድሞ ትሰማው የነበረውን አንድ ጉዳይ ማየት እያሰበች ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ የልቧ ይሞላል፣ የሃሳቧ ይደርሳል፡፡
እሷ ስለአረብ አገር ሕይወት በጎ ከክፉ ሰምታለች። የምታወቀው መልካም ጉዳይ ዓይኗን ሲስብ አእምሮዋን ሲያሳምን ቆይቷል፡፡ በለስ ቀንቷት እንደቀናቸው ሰዎች ከሆነች ሃሳቧ ይቃናል፣ ዓላማዋ ይሰምራል፡፡ ባህር ተሻግራ ጉልበቷን ገብራ፣ የምታገኘው ገንዘብ ስለነገዋ መሠረት ነው፡፡ የተሻለ ከያዘች ኑሮዋ ይቃናል፡፡
ፋጡማ ከዚህ በተቃራኒ የሰማችው ጉዳይ ሲያሳስባት ኖሯል፡፡ ክፋቱ፣ ተንኮሉ ፣ ጉልበት ብዝበዛው ያሰጋታል። እንዲያም ሆኖ መልሳ ትበረታለች፡፡ ስአአረብ ሀገር ክፋት የነገሯት አንዳንዶች ተመልሰው መሄዳቸውን ስትሰማ እንቅፋቷ ከፊቷ ይወገዳል፡፡ ውስጧ ይበረታል፣ ለመሄድ ትነሳለች ሠርቶ ለመለወጥ፣ ይዞ ለመምጣት ትበረታለች፡፡
አሁን ፋጡማ ከውሳኔ ደርሳለች፡፡ በውስጧ ሲጣሉና ሲራኮቱ የኖሩት ሃሳቦች መታረቃቸው ተሰምቷታል። ስለአረብ ሀገር ክፋት የሰማችውን በወስጧ ይዛ መልካምነቱን ብቻ እያሰበች ነው፡፡ ይህ እውነት ለመንገዷ አነሳስቶ ጓዝ አሸክፏታል፡፡ ሰርቶ ለማደር፣ ይዞ ለመገኘት ከዚህ የተሻለ ምርጫ አላገኘችም፡፡
ጉዞ ወደ ቤሩት…
ገጠር ወልዶ ያሳደጋት ወጣት አሁን ባህር ተሻግራ ከአረብ ሀገር ምድር ተገኝታለች፡፡ ሀገረ ቤሩት የእሷ ማረፊያ በሆነች ማግስት ራሷን ያገኘችው በሰው ቤት ሥራ ላይ ነበር፡፡ የዚህ አገር ሥራ ሀገር ቤት እንደምታውቀው አይነት ውሎ አይደለም፡፡ ጉልበትና ላብ ይጠይቃል፡፡ ብዙ ዋጋን ያስከፍላል፡፡ እንቅልፍና እረፍት ቅንጦት ናቸው ፡፡ ሥራውን፣ የሰዉን ባህርይ ፣ ምግቡን በዋዛ አይለምዱትም።
በእርግጥ ካገሯ ስትወጣ ይህ እንደሚያጋጥም ታውቃለች። ሁሉን እንደሁኔታው አስማምቶ፣ እንደጠባዩ መስሎ ማደር፣ ግድ ይላታል፡፡ ይህ ሲገባት ‹‹አቤት… ወዴት…›› ይሉትን አውቃለች፡፡ መስላ ለማደር፣ ሆኖ ለመገኘት አትሆነው የለም፡፡ ውላ አድራ ከአሠሪዋቿ ተላምዳለች። ከመብቷ ይልቅ ግዴታዋ እንደሚበልጥ እየገባት ነው፡፡
የቤሩቷ ማዳም
በቤሩት የሰው ቤትን ሀሁ የጀመረችው ከአንድ ቤተሰብ ነበር፡፡ ቤተሰቡ ሰፊና የተቀላቀለ ነው፡፡ የቤቱ ወይዘሮ በፋጡማ አጠራር ‹‹ማዳም›› ውሃ ቀጠነ ባይ ተቆጪ ናት። ሰበብ እየፈለገች ትነጫነጫለች፡፡ ምክንያት እየመመዘዘች ነገር ታነሳለች፡፡ ፈረንሳዩ ባሏ ባህርይው ከእሷ ይለያል። ለሰው አዛኝ ተጨናቂ ነው፡፡ ይህ ማንነቱ በሚስቱ ዘንድ አይወደድም፡፡ ሁሌም ድርጊቱ ያበሽቃታል፣ ያናድዳታል፡፡
የእህት የወንሟን ልጆች የምታሳድገው ወይዘሮ ሰው እንዲያርፍ፣ እንዲቀመጥ አትፈልግም፡፡ ሥራ እየጫነች፣ ጫና እያበዛች እረፍት ትነሳለች፡፡ በእሷ ፊት ከባሏ ትዕዛዝ መቀበል ነውር ነው፡፡ ቀና ብሎ ማውራትም እንዲሁ፡፡
እረፍት የለሿ ፋጤ ከዕለት ተግባሯ ውጭ ሌላ ዓላማ የላትም፡፡ ከማለዳ እስከምሽት በሥራ ተግታ ትውላለች። የማዳም ቁጣና መነጫነጭ ከድካም ታክሎ ቢያዝላትም ታዛዥነቷ አልጎደለም፡፡ የተባለችውን ትፈጽማለች፣ የግዴታዋን ትወጣለች፡፡
የወይዘሮዋ ቁጣ ሰበቡ ሥራ ብቻ አይመስልም። ፋጤን የምታያት በክፉ ዓይኖቿ ነው፡፡ ርምጃዋ ደስ አይላትም፡፡ ሰላምታዋን ፣ ንግግሯን አትወደውም። ለሠራተኛዋ በየወሩ ደሞዝ የሚከፍላት አባወራው ነው። ይህ መሆኑ ለማዳም ሰላም አልሰጠም፡፡ በዚህ ሰበብ እንዳይቀርብ እንዳያገኛት ትሰጋለች፡፡
ጥርጣሬ ከ ስጋት…
ሰበበኛዋ ማዳም ፋጤን ሰላም መንሳት ቀጥላለች፡፡ የባሏ መልካምነት ለእሷ ትርጉሙ ሌላ ሆኗል፡፡ ትህትናው፣ ሰብዓዊነቱ፣ አቀራረቡ አልተመቻትም፡፡ እሱ ሥራ ሲወጣ ሠራተኛዋን ታንገላታለች፡፡ ውሎ ሲመለስ ዓይኖቹን እየተከተለች ርምጃውን፣ ትቃኛለች፡፡
ፋጤ ጉዳዩ በገባት ጊዜ ውስጧ በስጋት ተያዘ፡፡ እንደ እሷ ለእንጀራ ካገራቸው የወጡ ሴቶች የደረሰባቸውን ታውቃለች፡፡ የማዳሞች ክፉ ጥርጣሬ ከፎቅ አስጥሏቸዋል፣ ከፈላ ውሃ ቀቅሏቸዋል፡፡ አካላቸውን ያጡ፣ ሕይወታቸውን የተነጠቁ ጥቂት አይደሉም፡፡ አሁን ፋጤ ፍራቻዋ ከተራ ስጋት እያለፈ ነው ፡፡ እንቅልፍ አጥታለች፣ ሰላም፣ ደስታ ርቋታል፡፡
ከቀናት በአንዱ የማዳም ባለቤት ጓዙን ሸክፎ ለመንገድ ተዘጋጀ፡፡ የሻንጣውን መጫን ያየችው ፋጤ ድንጋጤ ዋጣት፡፡ ለሰውዬው ድንገት መነሳት ሰበብ የሆነች ቢመስላት ልቧ መታ ፣ ላብ አጠመቃት ፡፡ ቆይታ ፈረንሳዊው ወደ ሀገሩ ለእረፍት እየሄደ መሆኑን አወቀች፡፡ ውስጧ ተረጋጋ፣ እፎይታና ሰላም ተሰማት፡፡
ፈረንሳዊው ሀገሩ ከሄደ በኋላ ሕይወት ከማዳም ጋር ቀጠለ፡፡ ፋጤ ለጥቂት ቀናት ሰላም ያገኘች መሰላት። ‹‹አሁን ወይዘሮዋ የምትናደድበት ጉዳይ የለም›› ስትል አሰበች። እንደቀድሞው እየታዘዘች፣ ያለቻትን ሁሉ ፈጸመች፡፡ ሰውዬው በሀገሩ ቆይቶ ወራትን አስቆጠረ ፡፡ የእሱ ሄዶ መቅረት የፋጤን ደሞዝ ክፍያ አዘገየው፡፡
ሴትዬዋ በትዕዛዝ ከማሠራት በቀር ስለፋጤ ደሞዝ ግድ አልሰጣትም፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ ሠራተኛዋ ናት። እንዳሻት ታሠራታለች፣ ታዛታለች፡፡ ነገም ቢሆን ከዚህ ልምዷ ፈቀቅ አትልም፡፡
እንደዋዛ ስድስት ወራት ያለደሞዝ መንጎዱ የገባት ፋጤ ቆም ብላ አሰበች፡፡ በዚህ ከቀጠለች ዓመት ሊያልፋት ይችላል፡፡ ቤሩት ላይ የምታውቃቸውን ሰዎች አስታወሰች። እነሱ እንደፋጤ ላሉ ሴቶች መፍትሄ አያጡም፡፡ ቤት ተከራይተው ፣ ሰብሰብ ብለው ይኖራሉ፡፡ በድንገት አግኝታ አወራቻቸው፡፡ ጠፍታ እንድትመጣ ነገሯት ፡፡ ፓስፖርታና ጥቂት ልብሶቿን ይዛ ከእነሱ ደረሰች፡፡
ሰዎቹ ሌላ ቤት ከመግባትና ሀገሯ ከመሄድ ምርጫ ሰጧት፡፡ ፋጤ ከማዳሟ ወጥታ ሌሎች ዘንድ መቀጠል አልፈለገችም፡፡ ውሳኔዋ ሀገሯ በሰላም መግባት ሆነ። ያሰበችው አልቀረም፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላ ወደ አገር ቤት ተመለሰች፡፡ የስድስት ወር ደሞዝ ቢቀርባትም አልተከፋችም፡፡ ቤተሰቦቿን ሰላም ማግኘቷ አስደሰታት፡፡
ትግል ከጤና ጋር…
አሁን ፋጡማ አገር ቤት ገብታ ሕይወት ቀጥላለች፡፡ እንዲህ ከሆነ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን ሌላ ፈተና ገጠማት። ምክንያቱን ሳታውቀው በድንገት ታመመች፡፡ ህመሟ በቀላሉ የሚድን አልሆነም፡፡ ደርሶ እጅና አግሯን ያሰራት ችግር ከአልጋ አዋላት፡፡
መላው ቤተሰብ ስለእሷ ተጨነቀ፡፡ ፈጥነው ሀኪም ዘንድ ወሰዷት፡፡ የተሰጣት መድሃኒት ለውጥ አላመጣም። አልጋ አስይዞ የሚያሰቃያት ህመም ቀስ እያለ ከቤት አዋላት። ፋጤ በእድሏ አዘነች፡፡ ከዓመታት በኋላ የገጠማት ህመም ያስጨንቃት ያሳስባት ያዘ፡፡
ውሎ አድሮ ቤተሰብ ስለ ጤናዋ መከረ፡፡ ህክምናው ቀርቶ ‹‹ቁርዓን›› እንዲቀራላት ተወሰነ፡፡ ፋጤ በሃሳቡ ተስማማች፡፡ እንደታሰበው በእምነቱ ሥርዓት ሂደቱ ቀጠለ፡፡ ፋጤ ውላ አድራ ጤና ይሰማት ያዘ፡፡ ወራት ያስቆጠረው ጥረት በፈውስ ሲጠናቀቅ ወጣቷ እንደገና ለርምጃ ፈጠነች፡፡
አዲስ ህይወት…
አሁን ፋጡማ በሀገሯ መሬት የነጻነት አየር መተንፈስ ይዛለች፤ ጤናዋ መመለሱ እፎይታ ሰጥቷታል፡፡ ጠዋት ማታ ፈጣሪዋን እያመሰገነች ስለ ነገዋ እያሰበች ነው፡፡ አዲስ አበባ ለእሷ ምርጫዋ ሆናለች፡፡ አሁን በአቅሟ ሰርታ ማደር ይቻላታል፡፡ ይህን እያሰበች ሳለ ያለችበት አካባቢ በማህበር አደራጅቶ የመነገጃ ስፍራ እንደሚሰጥ ሰማች፡፡
ፋጡማ ከሚመለከታቸው ቀርባ ሁሉን ስታስረዳ ሰሚ አላጣችም፡፡ ከመሰሎቿ ጋር እንድትደራጅ ይሁንታን አገኘች፡፡ ከቀናት በኋላ ላስቲክ ወጥራ የሥራ ቦታዋን አዘጋጀች፡፡ የጀበና ቡናዋ ደንበኞችን ሳበላት፡፡ ሻይዋን የወደዱ፣ ባህርይዋን የለመዱ ቤቷን አዘወተሩት፡፡ ትኩስ ብስኩትና አምባሻ ከፈጣን ምግቦች እያዘጋጀች ኑሮን ቀጠለች ፡፡ ትናንትን ረሳች፣ ዛሬ ላይ ቆማ ነገን አሰበች፡፡
በአካባቢዋ አቅሟን የሚመጥን ቤት ተከራይታለች፡፡ ታናናሽ ወንድሞቿ አብረዋት ይኖራሉ፡፡ ያለፈችበት መንገድ ከባድ ቢሆንም ፈጣሪዋን አማራው፣ ወቅሳው አታውቅም፡፡ ባላት ነገር ደስተኛ ነች፡፡ ፋጤ ስለነገ ያላት ህልም ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዛሬ የተሻለ መንገድ ላይ መቆም ዓላማዋ ሆኗል፡፡ ለዚህም ስኬት ጠዋት ማታ ትለፋለች፣ ትደክማለች፡፡
በድንገት…
አንድ ማለዳ በእሷና በመሰሎቿ ላይ የሆነው እውነት የፋጤን ልብ ሰበረው፡፡ ተደራጅተን ይዘነዋል ያሉት የላስቲክ ጎጆቿቸው በአፍራሽ ግብረሃይል ድምጥማጡ ሲጠፋ በዓይናቸው አረጋገጡ፡፡ ፋጤ ይህን ባየች ጊዜ ድንጋጤና ብሶት በውስጧ ነገሰ፡፡ በሆነባት ድርጊት ተንገዳግዳ መውደቅ እንደሌለባት የወሰነችው ወዲያው ነበር። ከፈረሳው የተረፈውን የቡና ዕቃ ይዛ ቤቷ አልገባችም፡፡ ከአንድ አጥር ጥግ ቆማ ስለነገው አሰበች፡፡
ማግስቱን ሲኒዎቿን ደርድራ ጀበናዋን አቅርባ ደንበኞቿን ጠበቀች፡፡ እንደቀድሞው ቤት ከለላ የላትም፤ ጸሀይዋ ብትከር ፣ዶፍ ዝናብ ቢመጣ የሚያስጠጋት የለም። እሷን ያሉ ፈልገው አላጧትም፡፡ ካለችበት ደርሰው ሻይ ቡናዋን ጠየቁ፡፡ ካልተመቸው ሥፍራ ቆመው ‹‹አይዞሽ፣ በርቺ›› አሏት፡፡ ይህን ያዩ የአካባቢው ደንቦች ዝም አላሉም። ዕለቱን ደርሰው ስለምን ሲሉ አጣደፏት፡፡
አሁን ቤት የላትም፣ ለእንግዶች ፣ ለደንበኞች ማረፊያ የሚሆን ምቹ ሥፍራም እንዲሁ፡፡ ደንቦቹ አልከፉባትም። ዝናብ ክረምቱን ከቻለች እንድትሠራ ፈቀዱላት፡፡ ፋጤ ‹‹በረደኝ፣ ዝናብ፣ ዶፉ ያዘኝ›› ብላ አልቀረችም፡፡ ጠዋት በዝናብ፣ ረፋድ በጎርፉ እየታጠበች ከእንጀራዋ ትውላለች። እርጥቡ እንጨት፣ ለመቀጣጠል አይፈትናትም፡፡ ከሰል ንፋሱ ሁሌም የእሷ ተባባሪ ነው፡፡
ከአንድ ጥግ የምታሳድረው ጓዟ ማለዳ ላይ በውሃ ርሶ ታገኘዋለች፡፡ ቅዝቃዜውን ችላ፣ ፀሀይዋን እየናፈቀች ቡና ሻይዋን፣ ብስኩት አምባሻዋን ታቀርባለች፡፡ ፋጤ ክረምቱ እስኪያበቃ፣ ወጀቡ እስኪያልፍ ከሕይወት ከኑሮ ትግል ገጥማለች፡፡ ጸሀይዋ ደምቃ እስክትወጣ እጅ አትሰጥም፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2015