ያልተለመደው ሽልማት

አንዱ ሲደክም ያልደከመው የደከመውን ማበርታት ግድ የሚልበት ወቅት አለ። ሰፋ ሲልም፣ የሠራን አካል “በርታ”፣ “ጎበዝ”፣ “በዚሁ ቀጥል”፤ “እናመሰግናለን።” ብሎ ከንግግር በዘለለ መድረክ በማዘጋጀት ሽልማት እና እውቅና መስጠትም የግድ የሚልበት ወቅት አይጠፋም። በሀገራችን ብዙ የሚባሉ የሽልማት አይነቶች አሉ፤ በተለይም በኪነጥበቡ ዘርፍ።

በብዙዎች ያልተለመደ ሽልማት ሲኖር ደግሞ፣ እርሱን ማበረታታት እንዲሁም እውቅና መስጠትም ተገቢ ይሆናል። “ፎከስ ኦን ኤቢሊቲ ኢትዮጵያ የአጭር ፊልም ፌስቲቫል” በሀገራችን ካልተለመዱ የሽልማት አይነቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ ስለ አካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ነው።

አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ የፎከስ ኦን ኤቢሊቲ ኢትዮጵያ ፌስቲቫል እና “የማለዳ አዋርድ” መሥራች እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ድርጅታቸው አካል ጉዳተኛነት ላይ ብቻ የሠሩትን አጫጭር ፊልሞች፤ ወይም አጫጭር ፊልም ሰሪዎች የሰሯቸውን ታሪክ በፊልም፤ ወይም በዘጋቢ ፊልም መልክ አወዳድሮ ይሸልማል። ታዲያ በዚህ ውድድር ላይ አካል ጉዳተኛ ብቻ ሳይሆን ጉዳት አልባውም መሳተፍ ይችላል። ብቻ ጉዳዩ ስለ አካል ጉዳተኞች ብዙዎችን የሚያስተምር መሆን ግድ ይለዋል።

ፌስቲቫሉ ወደ ኢትዮጵያ

በአንድ ወቅት የሀገራችን ፊልም በአውስትራሊያ ሀገር በሚገኝ ‹‹ፎከስ ኦን ኤቢሊቲ የፊልም ፌስቲቫል›› ተወዳድሮ አሸንፎ ነበር። ስለዚህም ሽልማቱን ለምን ወደ እኛ አናመጣውም? በሚል ቅን ሃሳብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ተደረገ። ‹‹እስካሁንም አካል ጉዳተኞች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ አንድ መቶ አስር ፊልሞች እጃችን ላይ አሉ። እነዚህም በኢትዮጵያ ብቻ የተሠሩ ናቸው።›› አሁን ኢትዮጵያ የፌስቲቫሉ ዋና መቀመጫ ሆና ከኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ እና ከሌሎች ሀገራት በተለይ ተመርጣለች። በ2024 ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ “ፎከስ ኦን ኤቢለቲ አፍሪካ” በሚል ስያሜ ፊልሞችን አወዳድሮ ለመሸለም በአስተናጋጅነት ተመርጣለች።

“ማለዳ አዋርድ”

ከፌስቲቫሉ በተጨማሪም የ‹ማለዳ አዋርድ› ሽልማት የሚካሄድ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ሥራዎችን ለሠሩ አካል ጉዳተኞች እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ነው። ዘርፎቹም በሙዚቃ፣ በጋዜጠኝነት፣ በሥራ ፈጠራ፤ በመሳሰሉት ዘርፎች እንደሆኑ አቶ ሚኪያስ ይናገራሉ። የኪነጥበብ ዘርፍ ለምን እንደተመረጠም ‹‹ተቀባይነቱ ሰፊ በመሆኑ ነው። ተወዳዳሪዎቹ ያላቸውን ታሪክ በአጭር ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንታሪ) ማስገባት ችለዋል።›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ።

ፋይዳ

እንደ አቶ ሚኪያስ ንግግር በ“ፎከስ ኦን ኤቢሊቲ ኢትዮጵያ ፌስቲቫል›› ግንዛቤ መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ በ“ማለዳ አዋርድ›› ደግሞ መነቃቃት ተፈጥሯል። ሥራውን እንኳንም ጀመርነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ‹‹በጣም ብዙ ያልተነኩ ታሪኮች እንዳሉ አውቀናል። እኛ ጋ የሚያስገቡ ተወዳዳሪዎች ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ክልሎችም ያላቸውን ባህል፣ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ያለውን አመለካከት፤ እንዲሁም መፍትሄ የሚሉትን ጨምሮ ነው የሚያስገቡት።›› ሲሉም ነው የሚያስረዱት።

በወጣቶች ውስጥ አብሮ የመሥራት፣ አብሮ የማደግ ስሜትን መፍጠር ተችሏል። በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመዞር፣ ፊልሞችን በማሳየት ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል። ‹‹ብዙ ታሪኮችን ባገኘን ቁጥር ለእኛም ትምህርት ሆኖን ነበር። አሁን ላይ ደግሞ መነቃቃትን ፈጥረናል።›› ይላሉ ስራ አስኪያጁ።

በ2021 በተደረገ ውድድር በአጭር ፊልም ሽልማት አምስት ሺህ ዶላር ያገኘው ከእኛ ሀገር ነው። በ2022ትም ብዙ ፊልሞች አሸንፈዋል። እንዲሁም ከአሜሪካ ቴሌቪዥን አካዳሚ ጋር በመሆን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ተደርጓል፤ ከሆሊውድ እንደዛው። በአጠቃላይ ሽልማቱ አካል ጉዳተኞች ሥራቸውን፤ ብሎም የሚገጥሟቸውን ችግሮ በሚገባ ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሯል።

እንደ አቶ ሚኪያስ ማብራሪያ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ፌስቲቫል አካል ጉዳተኞች በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላይ ያላቸውን ሀሳብ እንዲያካፍሉ፤ እንዲሁም ምርቶቻቸውን እንዲያቀርቡ ሰፊ እድልን ፈጥሮላቸዋል።

ፈተናዎች

አካል ጉዳተኞችን ትኩረት አድርገው በሚሠሩ ሥራዎች አመቺ ወይም ሊያሰሩ የሚችሉ መንገዶች በጣም ጥቂት ናቸው። ‹‹እውነት ለመናገር እንደ ሀገር የትብብር ወይም ተባብሮ መሥራት ላይ ትንሽ ይቀረናል። ምክንያቱም ይህ ሽልማት በሀገራችን የመጀመሪያው ነው። ነገር ግን በአፍሪካ ደረጃ ይህን ያህል ፕሮጀክት የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ ካለም ውስን ነው።›› የሚሉት አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ በጋራ ለመሥራት ፍላጎቱ ያላቸው ጥቂቶች ብቻ ሲሆኑ፤ ይህም ሥራቸውን ፈታኝ እንዳደረገው ይገልጻሉ።

‹‹በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኛ ማኅበረሰብ አለ። በመሆኑም፣ ይህንን ህብረተሰብ የሚወክል የፊልም እና የሚዲያ ሽልማት ድርጅት በመመስረት ይፋ ማድረግ ነበር ዓላማችን›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አካል ጉዳተኛ ማኅበረሰብ አለ። ይህንን ማህበረሰብ መሰረት በማድረግ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ፍላጎታችንን አቅርበን ነበር። ነገር ግን አብሮ፣ በትብብር የመሥራቱ ነገር ቀዝቀዝ ያለ ነው።›› ሲሉም በሥራቸው ስለገጠማቸው ፈተና ይናገራሉ።

ፈተናዎች ይኑሩ እንጂ አንዳንድ የውጭ ድርጅቶች አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውም ፈተናውን ‹‹ለበጎ ነው፤ ያልፋል›› ብለው እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው የገለፁት አቶ ሚኪያስ፣ በ‹ፎከስ ኦን ኤቢሊቲ ኢትዮጵያ ፌስቲቫል› ላይ ለመወዳደር ማንኛውም ሃሳብ አለኝ የሚል ሠው፣ ሞባይልን ጨምሮ፣ መቅረጽ በሚችልበት መሳሪያ ሁሉ በመጠቀም በዘጋቢ ፊልም ወይም በአጭር የፊልም ዘርፍ በመወዳደር፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ፣ አንድም ለሽልማት፣ አንድም ስለአካል ጉዳተኞች ግንዛቤ ለማዳበር ያስችላቸዋልና ቢወዳደሩ መልካም ነው ባይ ናቸው።

እንደ ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ በቀጣይም የተለያዩ መዳረሻዎችን በአፍሪካ ደረጃ የመክፈት ዕቅድ አለ። የተለያዩ አገራትም አብረው የመሥራት ፍላጎት አላቸው። በአሁኑ ወቅት አካል ጉዳተኞችም ሆኑ ፊልም ሠሪዎች፣ እንዲሁም ሌላው ማሕበረሰብ አጋጣሚው ተፈጥሮለታል።

አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ “ለውጥ መፍጠር የሚቻለው አብሮ መሥራት ሲቻል ነውና አብራችሁን የሠራችሁ እናመሰግናለን፤ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎቻችሁ ደግሞ በሀሳብ፣ በጉልበት – – – ኑና አብረን እንሥራ።” በማለትም ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You