የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱ ነው ::ለዚህም ቅድሚያና ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ሲያረጋግጥ ቆይቷል ::ይሁንና እየደረሰ ካለው ጥፋት ጋር ሲመዛዘን እየወሰደ ያለው እርምጃ ፈጣን አይደለም የሚል ቅሬታን አስከትሏል ::ትዕግስት መልካም ቢሆንም በሀገሪቱ እየተስፋፋ ከመጣው ሥርዓተ አልበኝነት አኳያ ሲታይ ትዕግስቱ በዛ የሚል አስተያየት ሲሰጥ እየተሰማም ነው። ህገወጦችን ለህግ በማቅረብ በኩልም ተለሳልሷል እየተባለም ነው፡፡
በሀገሪቱ እዚህም እዚያም ይፈነዱ የነበሩ ግጭቶች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የተከናወነው ተግባር እሳት ከማጥፋት የዘለለ አይደለም ፤ በህገወጦች ላይ ጠንካራ እርምጃ ባለመወሰዱ ሳቢያ ህገወጥነት ይበልጥ እየተስፋፋ መጥቷል የሚል አስተያየት ሲሰነዘር እንደነበርም ይታወቃል፡፡
ይሁንና መንግሥት የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚያመለክቱ እርምጃዎችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መውሰድ ጀምሯል ::ተለሳልሷል ሲባል የቆየበትን የህግ የበላይነት የማስከበሩን ጉዳይ አሁን በእርግጥም ቅድሚያ አጀንዳው እያደረገ መምጣቱን እያሳየም ነው፡፡
በቅርቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ 26 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መስርቷል ::እነዚህ ተጠርጣሪዎች የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ሲሆኑ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ነው ክስ የተመሰረተባቸው ::ተጠርጣሪዎቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን አላግባብ በመገልገል በፈጸሙት የሙስና ወንጀልም ነው ክስ የተመሰረተባቸው ::
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ ያቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን ለፓርላማው ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት እንደተጠቆመውም፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችንም ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ::
የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በቅርቡ እንዳሉትም ፣ዜጎች እንዲፈናቀሉ አድርገዋል የተባሉ 680 ያህል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤ በ468 ተጠርጣሪዎች ላይ ደግሞ ክስ የተመሰረተ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለው ግን 48ቱን ብቻ ነው ::
እነዚህ እርምጃዎች መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እየቀጠለ ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው ::ዜጎችን አፈናቅለዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ይህን ያህል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም በጥንካሬ መውሰድ ይገባል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያረጋግጥ እንደቆየው ሰዎችን እስር ቤት ሰብስቦ ካስገባ በኋላ የማጣራት ሥራ ውስጥ አይገባም፤ በትንሽ በትልቁም ጉዳይ ህዝብ ላይ መሳሪያ አይደግንም ::
ከዚህ ይልቅ ቅድሚያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይሰራል፤ በተጠርጣሪዎች ላይ ከተመሰረተው ክስ መረዳት የሚቻለውም አስፈላጊው መረጃ መጣራቱን ነው ::ይህን መጥላት አያስፈልግም ::የተጠረጠሩበትን ወንጀል በዝርዝር ሳይዙ ክስ መመስረትም ሆነ ማሰር ያለፉት ገዥዎች ያደረጉትን ስህተት መድገም ነውና ::
መንግሥት እያንዳንዱን ወንጀል በማጥናት ወደ እርምጃ የገባበት መንገድ በጥሩ ጎኑ ሊወሰድ ይገባል ::ይህም መንግሥት በአቋሙ መጽናቱን የሚያሳይ ሲሆን ፣ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ እንዲሁም ክስ የመመስረቱ ተግባር መፋጠን ይኖርበታል ::በዚህም የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ ይቻላል ::አሁን በሀገሪቱ ካለው ውስብስብ ህገወጥ ተግባር አኳያ አቅምን አስተባብሮ ተጠርጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን ማስከበር ያስፈልጋል፡፡
ህገወጥ ድርጊትን ተከታትሎ ሕገወጦችን ለህግ ማቅረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ ግጭት ተቀስቅሶ የዜጎችን ህይወት ከቀማ፣ ካፈናቀለ፣ ሀብትና ንብረታቸውን አሳጥቶ የሀገሪቱን ሀብት ካወደመ እንዲሁም ገጽታዋን ካበላሸ በኋላ ሳይሆን ቀደም ብሎ በማጥናትም መከላከሉ ተገቢ ነው። ወንጀል ከተሰራ በኋላ ተጠርጣሪዎች እንዳይያዙ ሽፋን የሚሰጡ አመራሮችንም አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል።
ዜጎችን ያፈናቀሉ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ የተሄደበትን ርቀት በጥሩ ጎኑ በመውሰድ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ያስፈልጋል፡፡አመራሩ ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ በኩል እየተጠረጠረ ነው ::ዜጎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ስለመሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአንድ በኩል ግጭት ቀስቅሶ በሌላ በኩል ደግሞ ለሰላምና መረጋጋት የሚሰራ ለመምሰል ጥረት የሚያደርግ አመራር እንዳለ ተገንዝቦ አስተማሪ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው። መንግሥት አሁን አንድ ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀዋል ::አብሮት የሚጓዘውንና የማይጓዘውን መለየትና በህግ መጠየቅ ውስጥ መግባት፡፡
የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ሥራም እነዚህን የለውጡ ነጭ እሾሆች የሚነቅል መሆን ይኖርበታል ::እነዚህ አመራሮች ለውጡን ለመቀልበስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ተላላኪዎች አይደሉም ብሎ መናገርም አይቻልም ::በመሆኑም በብዙዎች መስዋዕትነት የመጣውንና የህዝቡን ይሁንታና አድናቆት ያተረፈውን ለውጥ ለመጠበቅና ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ የህግ የበላይነት የማስፈኑ ሥራ እነዚህን አመራሮች የሚምር መሆን አይኖርበትም፡፡
መንግሥት ተጠርጣሪዎችን የገቡበት ገብቶ መያዝ የሚያስችለው ስልጣንም አቅምም አለው ::የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ሥራ በዋናነት የመንግሥት ቢሆንም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ይጠይቃልና ስልጣኑንና አቅሙን አሟጦ ከመጠቀሙ በፊት ግን ከክልሎች ጋር በተጠርጣሪዎች ጉዳይ ላይ አብሮ በመስራት እንዲተባበሩ ማድረጉ መልካም ነው፡፡
ስለሆነም የህግ የበላይነትን የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት መንግሥት ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ የጀመረውን ሥራ ፍጥነትን በማላበስ ሊያጠናክር ይገባል እንላለን ::
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2011