አዲስ አበባ፦ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሀብት ለመጠበቅና የደን ልማቱን ለማስፋፋት 2ነጥብ5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የደን ልማት ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸው ተገለጸ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለደን ልማቱ የሰጡት ትኩረት በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሬድ ፕላስ አድናቆትን አትርፏል፡፡
በአካባቢ ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን_የብሔራዊ አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤የደን ልማት ሥራዎቹ የሚከናወኑት ከኖርዌይ መንግሥት በተገኘ ወደ 80 ሚሊዮን ዶላርና ከዓለም ባንክ በተገኘ 18 ሚሊዮን ዶላር በሚደርስ ድጋፍ ነው፡፡
በጋምቤላ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 59 ወረዳዎች የደን ማልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ዶክተር ይተብቱ ተናግረዋል፡፡ ይህን የደን ልማት ለማካሄድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና ግብረ ኃይል መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡
በማገዶ እንጨት በከሰል ማክሰል በእርሻ መሬት ፍለጋ እና በሌሎችም ሰበቦች ደኖች እየተጨፈጨፉ መሆኑ ይታወቃል ያሉት ዶክተር ይተብቱ፣ የደን ልማቱን የማስፋፋትም ሆነ የደን ውድመቱ የመከላከሉን ሥራ በአዋጅ በተቋቋመ አንድ መሥሪያ ቤት ላይ ብቻ መጣል እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው ተነሳሽነት ከዚህ አኳያ የሚታየውን ትልቅ ችግር ሊቀንሰው ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
በሌሎች ሀገሮችም እንደታየው የደን ልማቱ ሊሳካ የሚችለው በመሪዎች ሲመራና ሲደገፍ መሆኑን አመልክተው፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደን ላይ ትኩረት ሰጥተው ለማስተባበር ለመምራት ተልዕኮውን መውሰዳቸው በጣም ትልቅ እርምጃ እና በመንግሥት ለደን ልማቱ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል ።
የተያዘው የደን ልማት ለማገዶ እንጨትና ለከሰል ማክሰል እንዲሁም ለእርሻ መሬት እየተባለ የሚወድመውን ደን ለመተካት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ህዝቡም ለደን ልማቱ ትኩረት እንዲሰጥና ግንዛቤውን ከፍ እንዲያደርግ ለሚከናውነው ተግባር እንደሚጠቅም ገልጸዋል።
የደን ልማቱ ከዝናብ፣ከኃይል ማመንጫ፣ከአየር ንብረት ፣ከውሃ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው ጠቅሰው፣ ከውጪ የሚገቡ የተለያዩ የደን ውጤቶችን የሚያስቀር መሆኑንም ገልጸዋል፡ ፡
ልማቱ ትኩረት አግኝቶ ቢሠራበት ኢኮኖሚውንም ይዞ ሊነሳ የሚችል ነው ያሉት ዶክተር ይተብቱ፣ በኃይል ማመንጨት በእርሻ በዝናብ በኢንዱስትሪ በመስኖ በአካባቢ ጥበቃ ሁሉ ያሉ ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ