አዲስ አበባ፡- ለ2011/ 2012 የመኸር እርሻ የሚያስፈልገው የማዳበሪያ አቅርቦት ከውጭ ተገዝቶ እየተጓጓዘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።ለምርት ዘመኑ ከአንድ ሚሊዮን 160 ሺ በላይ ኩንታል የዘር ፍላጎት መቅረቡንም ገልጿል፡፡
በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓት ግብይት ዳይሬክቶሬት በግዢ የሚቀርቡ የግብርና ግብዓቶች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘውዱ ስሜ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ በ2011/12 የምርት ዘመን አንድ ሚሊዮን 613 ሺ 246 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል።በአሁኑ ወቅትም አንድ ሚሊዮን 278 ሺ 982 ሜትሪክ ቶን ከውጭ ለማስገባት እቅድ ተይዞ እስካሁን አንድ ሚሊዮን 175 ሺ ሜትሪክ ቶን የማዳበሪያ ግዢ ተከናውኗል፡፡
በቅርቡ ተጨማሪ ግዢ ለማከናወን ጥያቄ መቅረቡን ባለሙያው ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት 100 ሺ ሜትሪክ ቶን የማዳበሪያ ግዢ መታዘዙን አስታውቀዋል፡፡ ባጠቃላይም እስካሁን አንድ ሚሊዮን 27 ሺ 847 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።
ከተገዛው ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ የደረሰው 796 ሺ 230 ነጥብ 58 ሜትሪክ ቶን መሆኑን ባለሙያው አመልክተው፣ ከዚህ ውስጥ 701 ሺ 887 ያህሉ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ወደ ክልሎች እንዲጓጓዝ መደረጉን ገልፀዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ለሚያቀርቡት መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት 631 ሺ 457 ሜትሪክ ቶኑን ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 236 ሺ 099 ሜትሪክ ቶኑን ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ተደርጓል።
በተመሳሳይ በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓት ግብይትና የገጠር ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት በብዛት የሚቀርቡ የግብርና ግብዓቶች ግብይት ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ስመኝ ተጫኔ በበኩላቸው የምርጥ ዘር አቅርቦት ዝግጅትን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ የብእር እህል፤ ጥራ ጥሬና የቅባት እህል በተያዘው የሰብል ዘመን አንድ ሚሊዮን 160 ሺ 521 ኩንታል የዘር ፍላጎት ቀርቧል፤በዚሁ መሰረት ለአርሶ አደሩ የመኸር እርሻ አስፈላጊው ምርጥ ዘር እየቀረበ ይገኛል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የድቃይ በቆሎ ዘር እጥረት ማጋጠሙን የተናገሩት ባለሙያዋ፣ ይህንንም ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነና በቅርቡ ለአርሶ አደሩ የሚሰራጭበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ