የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን የጋሞ ዞን አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከኦል ግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የተፈጠረ ውዝግብን ያስመለክተናል። «የጋሞ ዞን እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተላለፈን መመሪያን በመተላለፍ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ጋሞ ዞን ቦንኬ ወረዳ ኮሸሌ ቀበሌ በኢንቨስትመንት የወሰድኩትን 1ሺ500 ሄክታር የእርሻ ቦታ ማልማት እንዳልችል እክል ፈጥረውብኛል፤ የተፈጸመብኝን በደልም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ ይፍረደኝ» ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና የምርመራ ክፍል አቤት ብለዋል። የዝግጅት ክፍሉ ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን መረጃዎችና ማስረጃዎች በጥልቀት በመመርመር የምርመራውን ዘገባ እንደሚከተለው አዘጋጅቶ ለአንባብያን አቅርቧል።
ከአቤቱታ አቅራቢው አንደበት
ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ስብሃቱ ለዝግጅት ክፍላችን የምርመራ ቡድን፤ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን፣ ቦንኬ ወረዳ፣ ኮሸሌ ቀበሌ ያለው 1ሺ500 ሄክታር እርሻ ሥራ እንዲስጓጎል ተደርጎብኛል፤ በአስተዳደርም በደል ደርሶብኛል ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። በተደጋጋሚ የደረሱ ችግሮችን ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ቢያሳውቁም አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘታቸው ለከፋ አደጋ መዳረጋቸውን አስረድተዋል።
«የጋሞ ዞን አንዳንድ አመራሮች ከፍተኛ በደል ፈፅመውብኛል። ጥቂት ባለሀብቶች ከአንዳንድ የወረዳው ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ድርጅታቸው ለዓመታት የደከመበትን ቦታ ለሌላ አካል አሳልፎ ሰጥቷል፤» የሚሉት አቶ ልዑል፤ ከዚህ ባሻገርም የሌሎች ጥቃቶች ሰለባ በመሆናቸው ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውን ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተፃፈ ደብዳቤን ውሳኔ ተቀባይነት እንዳያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ልዑል እንደተናገሩት፤ ወደ ጋሞ ዞን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ግብዣ ቀርቦላቸው የሄዱ ሲሆን፤ በወቅቱ በስፍራውም ምንም ዓይት መሠረት ልማት ባለመኖሩ 50 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ ካለአንዳች አካል ድጋፍ በራሳቸው ገንብተው ነው ሥራ የጀመሩት። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብም በተደጋጋሚ ያመሰገናቸው ሲሆን፤ በክልል ደረጃም ሕዝብን አሳታፊ በሆኑ መሠረት ልማቶችና የልማት ሥራዎች ታታሪ በመሆናቸው በክልል ደረጃም አንደኛ ወጥተው ተሸልመዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን በዞኑም ሆነ በወረዳው ያልተለመዱ የግመልና የዳልጋ ከብቶችን በማላመድ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እሳቤ የሚቀይሩ ሥራዎች ማከናወናቸውን ይጠቁማሉ። ለዚህም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ተደጋጋሚ ሽልማቶች እንደተበረከተላቸውም ተናግረዋል።
አቶ ልዑል እንደሚያስረዱት፤ ምንም እንኳን ይህን የመሰለ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የጠየቀ ሥራ ቢያከናውኑም፤ ለሕግና መመሪያ የማይገዙት የወረዳው አንዳንድ አመራሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር አላደረጋችሁም፤ የተማረ የሰው ኃይል አላስገባችሁም፤ ግብር አልከፈላችሁም በሚል ሰበብ 200 ሄክታር ለሽያጭ የደረሰ ሙዝ ቆርጠው ሸጠውባቸዋል፤ 38 ሄክታር የሚሆን የሙዝ ማሳን በማን አለብኝነት አውድመውባቸዋል። ከ200 በላይ ከብቶች ሸጠውባቸዋል፤ ማሽነሪዎች ተፈታተው ተወስደዋል። ኦል ግሪን የልማት ባንክ ከፍተኛ ዕዳ እያለበትና የእርሻ ቦታው በኦልግሪን ሥም ተመዝግቦ እያለ ቦታው ለሦስተኛ ወገን ተሰጥቷል።
ይህ ተግባር እንደ ሀገር ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ነው የሚሉት አቶ ልዑል፤ ኦልግሪን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበደረው 46 ሚሊዮን ብር በቀን 40ሺ ብር እየወለደ አሁን ላይ 102 ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል። በድርጅታቸው ላይ የተደረገውን ዘረፋ ድርጅቱን ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉንም አስረድተዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ እንዲሰጧቸው፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምላሸ
ዝግጅት ክፍላችን ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥር T1/2/12935 ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፃፈው ደብዳቤ፤ የባንኩ ተበዳሪ የሆነው ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በመመሪያ የተፈቀደለትን መብቱ ጥሰት ስለመፈጠሩ፤ የኢንቨስትመንት ቦታውም በሌሎች አካላት ስለመወረሩ እና በባንክ ስም ብድር የተወሰደበት ተሽከርካሪ በሌላ አካል እጅ ሲገባ ባንኩ ዝምታ መምረጡን ለምን? ሲል ጠይቋል። ባንኩም ከጉዳዩ ጋር አባሪ ይሆናሉ ያላቸውን መረጃዎች ሰጥቷል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኦንጎይንግ ኮንሰርን ፕሮጀክትና አኳየርድ አሴትስ ማናጅመንት ዳይሬክተር አቶ ታዬ ጅሩ እንደሚሉት፤ ኩባንያው የወሰደው ብድርና የደንበኛው መዋጮ በተመለከተ በሰጡት መረጃ ኦልግሪን በ1996 ዓ.ም በሦስት ግለሰቦች ሽርክና በሁለት ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ተቋቁሞ ከመጋቢት 1997 ዓ.ም ጀምሮ ካፒታሉን ወደ አምስት ሚሊዮን ብር በማሳደግ የማኅበሩ መሥራች በሆኑት ወይዘሮ ቀለሟ አለሙ እና አቶ አብርሃም ልዑል ተጠቃሎ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጋሞ ዞን፣ ገረሴ ወረዳ፣ ኮሻሌ ቀበሌ የሚገኝ በባንኩ ከፊል የብድር ፋይናንስ እና በማኅበሩ የግል መዋጮ 1ሺ500 ሄክታር ላይ የጥጥ የእርሻ ልማት ለማከናወን የተቋቋመ ኩባንያ ነው።
03/06/2002 ዓ.ም በተፈረመ የብድር እና የመያዣ ውል 19 ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሳ እንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ብር፤ እ.ኤ.አ መስከረም 28 ቀን 2014 በተፈረመ የብድር ክፍያ ማራዘሚያ እና የተጨማሪ ብድር ውል ሃያ ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስምንት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር የተፈቀደለት ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለፕሮጀክቱ ከፊል ወጪ መሸፈኛ የሚሆን ብድር ብር 47ሚሊዮን 916ሺህ 763 ተፈቅዷል።
ከዚህ ውስጥ 46ሚሊዮን 426 ሺህ 990 ብር ለድርጅቱ የሥራ ማስኬጃ ተለቅቆለታል። በተያያዘም ደንበኛው የካፒታል መዋጮ 26ሚሊዮን 062ሺህ 793 ብር እንዲያወጣ በማድረግ በጠቅላላው ብር 72ሚሊዮን 489ሺህ 783 ለግንባታ፣ ለመሬት ማልማት ሥራ፣ የእርሻ ማሽን እና ኢኩፕመንት፣ ለመኪና፣ ለመስኖ ሥራ፣ ለሥራ ማስኬጃ ወዘተ እንዲውል መደረጉን ያብራራሉ።
ሆኖም ኩባንያው ሥራውን ከጀመረ ጊዜ ወዲህ እክሎች እንደገጠሙት የሚናገሩት አቶ ታዬ፤ በመጀመሪያ ዙር በ850 ሄክታር ላይ ጥጥ በማምረት እና በመሸጥ ዕዳውን እ.ኤ.አ ጥር 2012 መክፈል እንደሚጀምር ተወስኖ ውል ተዋውሏል። ሆኖም በባለ አክሲዮኖች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት፤ ያልተጠበቀ ዝናብ በመከሰቱ፣ ወደ ፕሮጀክቱ የሚያደርስ የመንገድ መሠረተ ልማት እጦት እና በፀጥታ ችግር ምክንያት ፕሮጀክቱ በሚፈለገው ደረጃ ወደ ሥራ እንዳይገባ ሆኗል።
ይሁንና እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ባንኩ ለኩባንያው ያደረጋቸው ተጨማሪ ድጋፎች መኖራቸውን ያወሳሉ። ለምሳሌ፣ እ.ኤ.አ በ2012 ደንበኛው የገጠመውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ብድሩ እንዲራዘምለት ተወስኖ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 የብድር ማራዘም ውል ከባንኩ ጋር ተዋውሏል። ባንኩ እ.ኤ.አ መስከረም 28 ቀን 2014 የብድር ክፍያ ማራዘሚያ እና የተጨማሪ ብድር ብር 28ሚሊዮን 464ሺህ 838 (ሃያ ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስምንት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር) ድጋፍ አድርጓል። የፕሮጀክቱ ትግበራን መዘግየት ተከትሎ የተፈጠሩትን ተጨማሪ ወጪዎች ለመሸፈን እ.ኤ.አ ኅዳር 2019 ተጨማሪ ብድር ብር 271 ሚሊዮን ባንኩ የፈቀደ ቢሆንም፤ ደንበኛው የሚጠበቅበትን መዋጮ ብር 9ነጥብ1 ሚሊዮን ማዋጣት ባለመቻሉ ምክንያት ብድሩን ሳይጠቀም ቀርቷል።
ተበዳሪው ብድሩን በውሉ መሠረት መክፈል ሳይችል በመቅረቱ ባንኩ በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና 1147/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የ30 ቀን የሕግ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ምንም ዓይነት ክፍያ ባለመፈፀሙ የባንኩ እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተገኙበት ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ለሐራጅ አፈፃፀም እንዲረዳ ድርጅቱን በጊዜያዊነት ተረክቦታል ይላሉ።
አቶ ታዬ እንደሚሉት፤ ሁኔታዎችን መረዳት አስፈላጊ በመሆኑ ኩባንያው ያለበት የብድር ዕዳ ለማወቅ በተደረገ ጥረት፤ እ.ኤ.አ ነሐሴ 11 ቀን 2023 ድረስ ፕሮጀክቱን ለማስተዳደር የወጣ ወጪን ጨምሮ ጠቅላላ ውዝፍ ውስጥ የገባ ዋና ብድር 47ሚሊዮን 829ሺህ 370ብር ከ87 ሣንቲም፤ እና ውዝፍ ውስጥ የገባ ወለድ ብር 53ሚሊዮን 868ሺህ 811 ከ31 ሣንቲም በጠቅላላው ብር 101ሚሊዮን 698ሺህ 182 ከ18 ሣንቲም የባንኩ ዕዳ መኖሩን ይናገራሉ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር መ/10-1/748/30 በቀን ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲሁም በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ተቋማት ተገቢውን የአዋጭነት ጥናት በተፋጠነ ሁኔታ በመሥራት ለኢንቨስትመንት ካፒታል ወይም የሥራ ማስኬጃ ወይም ለሁሉም የሚሆን ብድር በባንኩ አሠራር መሠረት እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት ኅዳር 2012 የፕሮክቱ ትግበራ መዘግየት ተከትሎ የተፈጠሩትን ተጨማሪ ወጪዎች ለመሸፈን ተጨማሪ ብድር ብር 27 ሚሊዮን ባንኩ የፈቀደ ቢሆንም፤ ደንበኛው የሚጠበቅበትን መዋጮ ብር 9ነጥብ1 ሚሊዮን ማዋጣት ባለመቻሉ ምክንያት ብድሩን መጠቀም አለመቻሉን ያስረዳሉ። ስለሆነም ግለሰቡ በመመሪያ የተፈቀደውን እንዳይጠቀም ባንኩ አላገደም።
የጋሞ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቁጥር 187/126 ሐምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም ለድርጅቱ ከተሰጠው 1ሺ500 ሄክታር መሬት ውስጥ ያልለማውን 1000 ሄክታር መሬት በመቀነስ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ለሚችል አቅም ላለው ባለሃብት እንዲተላለፍ፤ ቀሪው እየለማ የነበረው 500 ሄክታር መሬት ደግሞ በባንኩ እጅ ሆኖ ለሌላ ባለሃብት እንዲተላለፍ ለባንኩ በደብዳቤ መግለፁን ተከትሎ፤ የባንኩ አመራር በደብዳቤ ቁጥር ፕማብማዳ-//304/2022 በቀን ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅለት ጠይቆ፤ ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ውሳኔው ስለሚሻርበት እና የመያዣ መብት ስለሚከበርበት አግባብ በተመለከተ በባንኩ በኩል ተነስቶ ውይይት ተደርጓል።
የክልሉ የበላይ አመራር ሁኔታዎችን አገናዝቦ የዞኑን ውሳኔ መሻር ወይም የማዘግየት ሥልጣን ስላለው ዞኑ በጉዳዩ ላይ ከክልሉ ጋር መመካከሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በፍጥነት ከክልሉ የከፍተኛ አመራር ጋር ተነጋግረን መፍትሄ እንድናገኝ ማሳወቃቸውን ነው አቶ ታዬ የሚናገሩት።
በዚሁ መሠረት ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ፕማብማዳ- 0/304/2022 ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ለርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ባንኩ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ፕሮጀክቱ ላይ ሐራጅ በማካሄድ ለሌላ አልሚ ባለሃብት ለማስተላለፍ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን በመግለፅ የተቀነሰውን መሬት በተመለከተ የውይይት መድረክ እንዲመቻችልንና ይኸው አስቀድሞ እንዲገለፅልን የተጠየቀ ቢሆንም ምንም ምላሽ አልተገኘም ብለዋል።
አቶ ታዬ እንደሚሉት፤ የኢንቨስትመንት ሥራው በሌሎች አካላት እንዳይወረር ከመከላከል አኳያ ባንኩ ከኩባንያው የተለየ መብት ባይኖረውም ጉዳዩን ግን በቸልታ አልተመለከተም። በተጨማሪም ለጋሞ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር ፕማብማዳ-l/205/2022 በቀን ግንቦት 30 ቀን 2014 የፕሮጀክቱ መሬት ይዞታ በሕገወጥ መንገድ እንዳይወረር አስፈላጊው ከለላ እንዲደረግለት እና መሬት የወረሩትን
እንዲያስለቅቁ ባንኩ በጽሑፍ ማሳወቁን ይጠቁማሉ። ማኅበሩ በተለያዩ ጉዳዮች ሲከሰስ ፍርድ ቤት ቀርቦ በአግባቡ ባለመከራከሩ ምክንያት በሌለበት እየተወሰነበት ስለሆነ የባንኩን የመያዣ መብት ሊያጣብብ፤ ሊያሳጣ ወይም ሊጎዳ እንደሚችል በመገንዘብ ተከራክሮ መብቱን አስከብሯል።
ለአብነትም ኦልግሪን የከሳሽ መቅደስ ይርጉን ዕዳ ባለመክፈሉ ምክንያት የድርጅቱ ንብረትና የባንኩ መያዣ በሆነ ፒካፕ መኪና ባንኩ ሳያውቅ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሐራጅ ከተሸጠ በኋላ በአፈፃፀም ክሱ ላይ ጣልቃ በመግባት እና ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት የዞን ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻር ካደረገ በኋላ መኪና በሀራጅ ተሸጦ በፍርድ ቤት በአደራ የተቀመጠውን አጠቃላይ ገንዘብ 360ሺ ብር ለማኅበሩ የብድር ዕዳ ክፍያ እንዲውል ተደርጓል።
ከሳሽ ሰይድ ዮሴፍ እና በፍርድ ባለእዳ አቶ ልዑል ስብሃት መካከል በነበረው ክርክር ባንኩ የመያዣ ንብረት በሆነው እና የሰሌዳ ቁጥሩ 03-05545ደህ የሆነ ፒክ አፕ ተሽከርካሪ በሐራጅ እንዲሸጥ ለከሳሽ ማካካሻ እንዲውል በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመታዘዙ ባንኩ ታኅሣሥ 09 ቀን 2013 ጣልቃ ገብ አቤቱታ በማቅረብ መብቱን አስከብሯል። በከሳሽ ወልዴ ገንቦ እና በተከሳሽ ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በነበረው ክስ ባንኩ በመያዣ የያዛቸው ንብረቶች ለከሳሽ መወሰኑን እና ጨረታ መውጣቱን ባንኩ ሰምቶ ለጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ በመከራከሩ የጨረታ ሥነሥርዓት እንዲቋረጥ አድርጓል።
በሌላ በኩል ማኅበሩ በብድር ውል ላይ የተቀመጠውን ስምምነት በመጣስ በባንኩ ለብድር መያዣነት የተያዙትን ሁለት የጭነት መኪና እና አንድ ድርብ ተግባር መኪናዎችን ለባንኩ እንዲያስረክብ በደብዳቤ ቢጠየቅም ከፕሮጀክቱ አድራሻ ላይ እንዲሰወሩ በማድረጉ ምክንያት በፖሊስ ታድነው እንዲያዙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ለሁሉም የፌዴራል እና የክልል የመንግሥት አካላት በደብዳቤ ተጠይቀዋል። በዚሁ መሠረት አንደኛው የጭነት መኪና ታድኖ የተያዘ ሲሆን ሌሎች ሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ አሁንም ክትትል እየተደረገ ይገኛል ሲሉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥረት እስከምን ድረስ አንደነበረ ያወሳሉ። ምንም እንኳን እነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶችና ሂደቶች ቢኖሩም ኦልግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሁኔታዎችን አስተካክሎ ወደ ሥራ መግባት ቢፈለግ፣ የልማት ባንክ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ታዬ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል ችግሩ ተፈጠረ ወደተባለበት የጋሞ ዞን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዞኑ አመራሮች ምላሽ በሰጡ ጊዜ ያገኘነውን ምላሽ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መመሪያ
በሐምሌ 13 ቀን 2009 ዓ.ም በቁጥር መ110-1/748/30 የተጻፈው መመሪያ እንደወረደ፡-
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለልማት ባንክ፣ ለብሔራዊ ባንክ ፣ ለገቢዎች ሚኒስቴር ፣ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤
ጉዳዩ፡- በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ተቋማት ስለመደገፍ ይመለከታል።
በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች በነበረው አለመረጋጋት ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨስትመንት እና የንግድ ተቋማት መኖራቸው የሚታወቅ ነው። እነዚህ ተቋማት እና ግለሰቦች ከጉዳታቸው አገግመው ሲሳተፉበት በነበረው ኢንቨስትመንት እና የንግድ ሥራ ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ መቀጥል እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ተገቢ መሆኑን ታምኖበታል።
በመሆኑም በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች ከደረሱ የሰላም መደፍረሶች እና አለመረጋጋቶች ጋር በተያያዘ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለወደሙ ንብረቶች የጉዳት ግምት ለሠራተኛው የተለያዩ ዓይነት ድጋፎችን በማቅረብ ሊሳተፉባቸው የነበሩትን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ሥራዎች ለማስቀጠል በማሰብ ከዚህ በታች በተመለከተው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት እንዲፈጽሙ የተወሰነ መሆኑን እናስታውቃለን።
1. የልማት ባንክ
1.1 ከዚህ በፊት ጉዳት የደረሰባቸውን ዝርዝር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሲደርሰው ተገቢውን የአዋጭነት ጥናት በተፋጠነ ሁኔታ በመሥራት ለኢንቨስትመንት ካፒታል ወይም የሥራ ማስኬጃ ወይም እንደሁኔታው ለሁሉም የሚሆን ብድር በባንኩ አሠራር መሠረት እንዲቀርብ ይደረግ። ኢንቨስትመንቱ እንደሁኔታው ለተሽከርካሪ ግዢ የሚቀርብ ብድር ሊጨምር ይችላል።
1.2 በማሽነሪዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ባንኩ በሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት ማሽነሪዎችን አሠራሩ በሚፈቅደው አግባብ ሊያቀርብ ይችላል።
2 የብሔራዊ ባንክ
ለማሽነሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እንደሁኔታው ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲስተናግዱ የሚያስችል ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ።
3. የገቢዎች ሚኒስቴር
3.1 ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሚደርሰው ዝርዝር መሠረት ጉዳት የደረሰባቸው ድርጅቶች በወቅቱ የትርፍ ግብር ግዴታቸውን ለመወጣት አቅም ለሌላቸው ድርጅቶች ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ምህረት እንዲደረግላቸው ይሆናል።
3.2 የግብር እፎይታ ጊዜያቸውን ላልጨረሱ ድርጅቶች የጉዳት መጠናቸውንና የባከነውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ የግብር እፎይታ ጊዜያቸው እንዲከለስ ያደርጋል።
3.3 ጉዳት ለደረሰባቸው ማሽነሪዎች እና ተሽከርካሪዎች በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሚላክ ዝርዝር መሠረት የጉምሩክ ኮሚሽን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስተናግድ ይደረጋል።
4. ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
4.1 የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸውን ተቋማት ለይቶ እና አደራጅቶ ለልማት ባንከ መላክ፤
4.2 በጥናቱ መሠረት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት የተጎዱ ዕቃዎችን ለመተካት የካፒታል ዕቃዎች እና ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ሲያመጡ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ በመፍቀድ ለጉምሩክ ኮሚሽን ደብዳቤ መጻፍ
4.3 ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ቫውቸር ማውረድ፣ የባንክ ብድር እና የግብር ዕዳ ክፍያ የማራዘም ጥያቄ ሲያቀርቡ እያጣራ ለሚመለከተው አካል የድጋፍ ደብዳቤ መጻፍ፤ ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታ ድጋፍ እንዲያደርግ እናስታውቃለን።
ከሰነድ የተገኙ ማስረጃዎች
ከዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን ጋር የሚገናኙ በርካታ ሰነዶችን በምርመራ ማግኘት ችለናል። ሁሉንም ሰነዶች በዚህ ዝግጅት ማጠቃለል ስለማይቻል አንባቢያን አይተው መፍረድ ያስችላሉ ያልናቸውን የተወሰኑ የሰነድ ማስረጃዎችን ብቻ አቅርበናል።
ሰነድ አንድ፡- ከኦል ግሪን ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተላለፉ መመሪያዎችን ዋቢ በማድረግ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለያዩ ጊዜያት ለማኅበሩ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረጉ በደብዳቤዎች ጠይቋል። ከእነዚህ መካከል በቀን በ8/6/2011 ዓ.ም በቁጥር አጠ/85/65 የተጻፈው ደብዳቤ አንደኛው ነው። በዚህ ደብዳቤ እንደተመላከተው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ጋሞጎፋ ዞን ቦንኬ ወረዳ ኮሼሌ ቀበሌ የሚገኘው የኦል ግሪን ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር የእርሻ ፕሮጀክት በአካባቢው በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት እንደደረሰበት፤ በዚህም ዘጠኝ ሚሊዮን ስድስት መቶ ዘጠና አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰማኒያ አምስት ብር የሚገመት ጉዳት እንዳጋጠመው፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ማኅበሩ ከደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት በማገገም ወደ ሥራ መግባት ይችል ዘንድ ለማኅበሩ ተጨማሪ ብድር እንዲፈቅድለት የሚል ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ6/10/2011 ዓ.ም በቁጥር አጠ /85/138/ በተጻፈው ሌላ ደብዳቤ እንደተመላከተው የኦል ግሪን ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ከደረሰበት ጉዳት በማገገም ወደ ሥራው መግባት ይችል ዘንድ አፋጣኝ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ፈቃድ በመስጠት እንዲተባበር ይጠይቃል።
ሦስተኛው ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጻፈው ደብዳቤ ደግሞ በ15/1/2013 ዓ.ም ቁጥር አጠ/85/7 ነው። በዚህ ደብዳቤ እንደተመላከተው የኦል ግሪን ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን እና ጉዳቱም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መጠናቱ፤ ከጉዳቱ በማገገም ተወዳዳሪ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለማኅበሩ የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምለት ትብብር የተጠየቀበት ይገኛል።
ሰነድ ሁለት፡- ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተጻፉ ደብዳቤዎችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቀን 27/2/2012 ዓ.ም በቁጥር ፕማብማዳ/231/2019 ለኦል ግሪን ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በተጻፈው ደብዳቤ እንደተመላከተው፤ ድርጅቱ በደረሰበት ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ውስጥ መሆኑን እና በዚህም ማኅበሩ ፕሮጀክቱን ማስቀጠል አለመቻሉን በባንኩ በመታወቁ ባንኩ ለፕሮጀክቱ ማስኬጃ ብር 27 ሚሊዮን 629 ሺህ 793 ከዋና ብድር መፍቀዱን እና የብድር ጊዜውም እንዲራዘም፤ ይሄን ለማድረግም የግል ማኅበሩም ብር ዘጠኝ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ሰባት መዋጮ እንዲያዋጣ፤ የመዋጮ ገንዘቡም በድርጅቱ ስም በተከፈተ ዝግ አካውንት ገቢ በማድረግ የተፈቀደውን አዲስ ብድር ከማኅበሩ ጋር እንዲፈራረሙ ውሳኔ መደረሰኑን የሚያሳይ ነው።
ሰነድ ሦስት፡- ኦል ግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚጠበቅበትን ልማት ማልማት አልቻለም በሚል የጋሞ ጎፋ ዞን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀን 23/04/2010ዓ.ም ማኅበሩን ከሥራ ማገዱን አስታውቆ ነበር።
ይህን ተከትሎ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በቀን 15/06/2010 ዓ.ም ቁጥር ደኢ/መ214/4948 በተጻፈ ደብዳቤ እንደገለጸው፤ የጋሞ ጎፋ ዞን ኢንቨስትመንት አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ በማኅበሩ ተመዝግቦ የሚገኝ እያንዳንዱ ንብረት የልማት ባንክ በብድር ማስያዣነት የተመዘገበ ስለሆነ ከባንኩ እውቅና ውጪ የማኅበሩን ንብረት ማንም ምንም መንካት አይችልም። ከዚህ ባሻገር ባንኩ በመያዣነት የሰጣቸውን ንብረቶች መንካት የመንግሥትና የሕዝብን ገንዘብ የሚያሳጣ ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ በመንግሥት ፖሊሲ አስፈጻሚ ተቋማት ላይ ቅንጅታዊ አሠራር እና መተማመንን የሚያሳጣ በመሆኑ፤ የዞኑ ኢንቨስመንት አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰደው እርምጃ ደረጃውን ያልጠበቀና የባንኩን መብት እንዲሁም ማኅበሩ ከባንኩ ጋር የገባውን ውል ያላጤነ በመሆኑ ምንም የመሬት ቅነሳ ሳያስፈልግ ባለሀብቶቹ ወደ ልማት ሥራ ተጠናክረው እንዲገቡ እንዲደረግ እና ዞኑም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተጻፈለትን መመሪያ ተፈጻሚ እንዲደርግ የሚያሳስብ ነው። ይሁንና ይህ ሁሉ ተፈጻሚ አልሆነም፡፡
ሰነድ አራት ፡- በቀን 29/07/2012 የወጣ ጨረታ
በዚህ ጨረታ ሰነድ እንደተመላከተው፤ ኦል ግሪን አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ2010 እና በ2012 ዓ.ም የእርሻ ሥራ ግብር፣ የመሬት መጠቀሚያ እና የሠራተኞች የሥራ ግብር ሰባት መቶ ሃያ አራት ሺህ ሦስት መቶ ሃምሳ ስምንት ብር ከሰማኒያ ዘጠን ሳንቲም ባለመክፈላቸው የግብር ባለሥልጣን ገረሴ ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት በታክስ አዋጅ ቁጥር 166/2009 አንቀጽ 41 ንዑስ አንጽ አንድ እና ሁለት በተሰጠ ሥልጣን መሠረት የባለዕዳውን ንብረቶች ማለትም 21 የቁም እንስሳት እና በገረሴ ወረዳ ኮሻሌ ቀበሌ የሚገኘውን 135 ሄክታር ላይ ያረፈን የለማን የሙዝ ምርት ጨምሮ ለጨረታ አቅርቧል።
ወድ አንባቢያን እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አንደኛ ግብር አልከፈሉም ተብሎ ለጨረታ የቀረበው ልማት ባንክ በብድር ማስያዣነት የያዘው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰባት መቶ ሃያ አራት ሺህ ሦስት መቶ ሃምሳ ስምንት ብር ከሰማኒያ ዘጠኝ ሳንቲም ግብር ባለመክፈላቸው ለጨረታ የቀረበው የለማ ሙዝ ብቻ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጣ መሆኑን የገበያ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ ምርመራ ያደራጀነው መረጃ ይሄ ብቻ አይደለም። በመሆኑም ሌሎች መረጃዎችን እና ምላሽ መስጠት ሲገባቸው ያልሰጡን አካላትን ምላሽ አካትተን፤ ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ጨምረን በቀጣዩ እትማችን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር እና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10/2015