አቶ ጀማል መሀመድ እና አቶ ማሞ ኃይሌ፣ በከሚሴና አካባቢዋ የሚኖሩ የአማራና ኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ናቸው፡፡ ከልጅነታቸውም አብረው አፈር ፈጭተውና ተጫውተው ያደጉ፤ በአካባቢው እንዳለው ማንኛውም ኅብረተሰብ ዛሬም ድረስ በሁለት አጎራባች ቀበሌዎች በሰላምና በፍቅር ተደጋግፈው በወንድማማችነት እየኖሩ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ በቅርቡ በአካባቢው ተከስቶ የነበረው ግጭት ለእኚህ ሁለት አባቶች ትልቅ ጭንቀትን ያሳደረ ነበር፡፡ ምክንያቱ እንደእነርሱ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ያሉ ወንድማማች ህዝቦች ምንም በማያውቁት ምክንያት፤ በጥቂት እኩያን እሳት ጫሪነት ሊጋጩ፤ ብሎም ሊገዳደሉ ሆነና ነው፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን አቶ ጀማል እና አቶ ማሞ ተገናኝተው በመወያየት «የአላላ የሰላም መሪዎች» ያሰኛቸውንና ዛሬ ላይ እውቅና ያስቸራቸውን አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ፡፡
«እኛ በሕይወት እያለን እነዚህ ወንድማማች ህዝቦች አይጋጩም፤ አይገዳደሉምም» ሲሉም ቃል ተግባብተው ስለ ህዝቦች ሰላም ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ቃል ተግባቡ፡፡ የየቀበሌዎቻቸውን ህዝብ ሰብስበውም እንዲህ አሉ፡፡ በቅድሚያ አቶ መሃመድ፣ «እኔ በሕይወት እያለው ከጎረቤት ህዝብ ጋር አትጋጩም፤ ይሄንን ማድረግ ከፈለጋችሁ ግን መጀመሪያ እኔን ገድላችሁ ሂዱና ጨርሷቸው» ሲሉ ለህዝቡ ነገሩ፡፡ አቶ ማሞም በተመሳሳይ አደረጉ፡፡
ይህን ጊዜ ለግጭትና እልቂት ተዘጋጅቶ የነበረው የሁለቱ ቀበሌ ህዝብ የሁለቱን ግለሰቦች ሀሳብ በማጤንና ሊሳሳት እንደነበር ገብቶት ወንድማማቾችን የግጭት ሃሳቡን በመተው ለጥፋት ተዘጋጅተው የነበሩ የሞት መሳሪያዎች ከሰሙ፡፡ እንዲህ እንደ እነ አቶ ጀማልና አቶ ማሞን ዓይነት አባትና መሪ ያጡት ግን በሴረኞች ለተጠነሰሰ የግጭት ድግስ ተገዢ ሆነው ወንድማማቾች ተገዳድለውባቸዋል፤ አንዱ አንዱን አፈናቅለውባቸዋል፤ ወንድም የወንድሙን ሃብትና ንብረት የመዝረፍና የማውደም ድርጊቶችም ተፈጽመውባቸዋል፡፡ የሰው ልጅ በማህበራዊ ጉድኝቱ ለመልካም የመተባበሩን ያክል፤ በየአጋጣሚዎች ለሚፈጠሩ መቃረኖችም ጎራ ከፍሎ መጋጨቱ እማይቀር ነው፡ ፡
ለመልካም ትብብር መጎልበት፤ ለመጥፎ ቅራኔዎች ደግሞ መክሰም ቀን ከሌት የሚተጉ የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎችና ለፈጣሪያቸው የተገዙ የሃይማኖት አባቶች እንደየአካባቢያቸው ባህልና ወግ መክረውና ገስጸው አጥፊውንም ቀጥተውና ተበዳይንም አስክሰው በይቅርታ ችግሩን ይቋጩታልና፡፡ ከሚሴና አካባቢዋም ይሄንኑ ባህልና ወግ የተላበሱ ህዝቦች የሚኖሩባት እንደመሆኗ፤ በአካባቢው ሰዎች ቅራኔ ሲያሳድሩና ወደ ጠብና ግጭት ሲያመሩ፣ በአካባቢው የተጣላን በሚያስታርቁ፣ የህዝብ ራስ ሆነውም በሚሰሩ አበጋር ጊቢ ውስጥ ይሰባሰባሉ፡፡
የአበጋር ምሳሌ የሆኑ እኚህ የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶችም በተከሰተው ግጭት በህዝቦች መካከል ያለው ቁርሾ እንዲሽርና ሰላም እንዲሰፍን ሥራ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ሰሞኑንም የሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ ወረዳ ህዝቦች የሰላምና ወንድማማችነት ጉባዔ በከሚሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ጉባዔ፣ «ሠላምና ሠላማዊ አብሮነት በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረቡት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ሽመልስ ኃይሉ እንዳሉት፤ የሰው ልጅ በህይወት መኖርን ጨምሮ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች ሁሉ ሊከበሩ የሚችሉት ሰላም ሲኖር ነው፡፡
ከሁከትና ጦርነት ነጻ መሆን የሰላም መገለጫ ሊሆን ቢችልም፤ ሰላም ግን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ትስስርን፣ አንድነትና መረዳዳትን የምትሻ ታላቅ ነገር ናት፡፡ ሆኖም በህዝቦች መካከል ግጭትን የሚጋብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የአንድ ህብረተሰብ ማህበራዊ ትስስር የሚለካው ግን ግጭት ባለመኖሩ ሳይሆን ባለው ጠንካራ የግጭት አፈታት ስርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የገዳ፣ አኝዋክ አኩድሆ፣ ኪቻ፣ ሚዳ እና ሽምግልናን የመሳሰሉ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች አሏት፡፡ የከሚሴ አካባቢ ህዝብን ማህበራዊ ህዝብ ትስስርና የሰላምን ታላቅነት የሚናገረውም የተፈጠረው ግጭት ሳይሆን ግጭቱን ለመፍታት መስራታቸው ነው፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ይሄንኑ ሃሳብ አንጸባርቀዋል፡፡ በተለይ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት ሊሆን የማይገባው ነበር ፡ ከሆነ በኋላ ግን ግጭቱን እያሰቡ ወንድማማችነትን ከመፈተን፣ በአገርና አካባቢው ወግ መሰረት አጥፊ ተቀጥቶና ክሶ፤ ተበዳይም ይቅር ብሎ የነበረ አብሮነትንና ሰላምን መመለሱ ይበጃል፡፡ ቀድሞውንም ግጭቱ የህዝቡ ሳይሆን ከውጭ የተላከ የጥፋት ሀሳብ እንደመሆኑ፤ አንድ ሰው ሲገደል አማራ ኦሮሞን ወይም ኦሮሞ አማራን የገደለበት ሳይሆን አንድ ኢትዮጵያዊ የጎደለበት እንደመሆኑ ህዝቡ የነበረ ሰላምና አንድነቱን ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መንግሥት የሚጠበቅበትን የቤት ሥራ በአግባቡ መስራት እንደሚገባው ነው ተሳታፊዎቹ ያስገነዘቡት፡፡
«እኛ ቀድሞውንም አንድ ነን፤ አሁንም አንድ ነን፤ ወደፊትም በአንድነታችን እንጓዛለን» የሚሉት አቶ ጀማል፤ ችግሩ የተከሰተው እነዚህ ወንድማማች ህዝቦች በማያውቁት ነገር አሜሪካም ሆነ አገር ውስጥ ሆነው የተደላደለ ኑሮን እየገፉ በወንድማማቾች ደም ለመደላደል የሚሹ አካላት በሰሩት ሴራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እርሳቸውና አቶ ማሞ ቀበሌዎቻቸውን ከዚህ ግጭት የታደጉ ቢሆንም፤ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተፈጠረውን ቁርሾ ለማሻር በዚህ መልኩ የውይይትና እርቅ የማውረድ ሥራ መጀመሩም የሚመሰገን መሆኑን በመግለጽ፤ በወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረን ጠባሳ ለማሻርና ሰላሙን ለማስፈን ከግለሰብ እስከ መንግሥት ሁሉም ከልቡ መስራት እንደሚገባው መክረዋል፡፡
ለእርሳቸውና ለአቶ ጀማል ብሎም ሌሎች ለሰላም የተጉ አካላት በመድረኩ የተሰጣቸውን እውቅና ተከትሎ «ይህችን ቀን በማየቴ ደስ ብሎኛል፣ እንኳን ደስ አለን» በማለት መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ማሞ በበኩላቸው፤ «እኛ አብረን አፈር ፈጭተን ያደግን የድሃና አርሶ አደር ልጆች ሆነን ሳለ፤ እኛ እያለን ሁለት ወንድማማች ህዝብ መጋደል እንደሌለበት መክረን በወሰድነው እርምጃ ህዝቡ ወንድማማችነቱን በማረጋገጡ ከልብ ሊመሰገን ይገባል» ብለዋል፡፡
ይህም ችግሩ የህዝቡ አለመሆኑን አመላካች እንደሆነ በመጠቆምም፤ ይሄን ያልተረዱ አካባቢዎች የተፈጠረው አደጋ ያሳዘናቸው ቢሆንም አሁን ላይ በዚህ መልኩ ሰላም ለማውረድ በጋራ መሰባሰባቸው የሁለቱ ህዝቦች ትስስር በቀላሉ የሚበጠስ እንዳልሆነ አረጋጋጭ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው፤ በግጭቱ ለመርሳት የሚከብድ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ሽማግሌዎች ይሄንን ጠባሳ ለመሻር የጀመሩት ተግባር የሚበረታታ ነው፡፡ በሂደቱ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ቢችሉም ሽማግሌዎቹ ከፖለቲካ ወይም ከሌላ አቅጣጫ የሚነፍስ ንፋስ የማይጎትታቸው እውነተኛ ሽማግሌ ሆነው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሰላም ከሁሉ የላቀች ናት ፖለቲካውም ሆነ ሌላው ነገር ከሰላም በታች ነው ያሉት ዶክተር አምባቸው፤ ህብረተሰቡ ለሰላሙ የማይተካ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ::የክልሉ መንግሥትም የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የሚሰራ እንደመሆኑ ይሄን ማድረግ ያልቻለ አመራር ብሎም ችግሮችን ለማባባስ የሚሰራ በየትኛውም ቦታ ያለ አካል ላይ ለህዝብ ጥቅም ሲባል እርምጃ እንደሚወሰድ አብራርተዋል ::መድረኩም «ህዝቦች ከሰቀቀን የሚወጡበትን ሥራ ለመስራት ቃል ኪዳን የምንገባበት እንጂ ሁሉም ሥራ እዚሁ የሚያልቅበት አለመሆኑን አውቃችሁ ሁላችሁም በኃላፊነት መስራት ይጠበቅባችኋል» ሲሉም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2011
ወንድወሰን ሽመልስ