ሴቶችና የአሸንዳ በዓል በትግራይ

የምንገኝበት የነሐሴ ወር ከጨለማው ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበት፣በአዲስ አመት አዲስ ተስፋ የምንጠብቅበት መሸጋገሪያ ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። የመጀመሪያው የበዓል ማብሰሪያ ከሆነው የቡሄ በዓል ጀምሮ ደመቅ የሚልበት፣በተለይ ደግሞ ልጃገረዶች የሚደምቁበት ወር ነው።

ከነሐሴ 16ቀን እስከ አዲሱ አመት መስከርም ወር ድረስ ያለው የሴቶች ጊዜ ነው። ተውበውና ደምቀው የሚታዩበት፣በአጠቃላይ ሴቶች ከፍ ብለው ጎልተው የሚወጡበት ወር ነው። በመሆኑም ልጃገረዶች ነሐሴ ወር ግም ሲል ጀምሮ ነው የማብቂያውን ጊዜ በጉጉት የሚጠብቁት።

ልጃገረዶች ከቤተሰቦቻቸው ለጨዋታ ነፃነት የሚያገኙበት ወቅት በመሆኑ ለአልባሳቶቻቸው፣ ለፀጉር አሰራራቸው፣ለእጃቸው አምባር፣ለእግራቸው አልቦ፣ለአንገታቸው ድሪ ወይንም ከብር የተሰራ ጌጥ፣ ለጆሮአቸው ጉትቻ፣ በአጠቃላይ ለሚዋቡበት ተጨንቀውና ተጠበው ይዘጋጃሉ። ያቺ የሚናፍቋት የጨዋታ ጊዜ ከመድረሷ በፊትም በአንድ አካባቢ የሚኖሩና አብሮ አደግ ልጆች ተሰባስበው፣ ከመካከላቸውም መሪ መርጠው ስለጨዋታቸውም ይመካከራሉ። በዓሉን የሚያደምቁትና ለጨዋታውም የሚጓጉት ልጃገረዶች ይሁኑ እንጂ አዋቂዎችም ቢሆኑ የልጅነት ጊዜያቸውን የሚያስታውሳቸው በመሆኑ እነርሱም የሚጠብቁት በዓል ነው።

እንዲህ በሰፊ ዝግጅትና በጉጉት የሚጠበቀው የልጃገረዶች ጨዋታ አሸንዳ፣አሸንድዬ፣ሻደይ፣ሶለል በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣የስም አጠራሩም እንደየአካባቢው ይለያያል። ባህላዊ ይዘት ያለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

ክብረ በዓሉ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በትግራይና በአማራ ክልሎች ውስጥ በስፋት የሚከናወን ሲሆን፤ሁሉቱ ክልሎች በየአመቱ በዚህ ወቅት በልጃገረዶች ጨዋታ ይደምቃሉ። በዓሉ ከሁለቱ የሀገሪቱ አካባቢዎች ውጪም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎችና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የየአካባቢዎቹ ተወላጆች ጨዋታውን በማስለመዳቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ሰፊ ሰው የሚያሳትፍ የአደባባይ በዓል በመሆኑም በውጭው ፌስቲቫል እንደሚባለው አይነት በከተማ አስተዳደር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት ከፍ ወዳለ ደረጃ እየተሸጋገረ የመጣ በዓል እንደሆነም አይዘነጋም።

ሆኖም ላለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ በገጠማት አለመረጋጋትና በተለይም በዓሉ ደምቆ በሚከበርበት የሰሜኑ ክፍል ጦርነት መካሄዱና አካባቢዎቹም በጦርነት ቀጣና ውስጥ መሆናቸው በዓሉን አደብዝዞታል። ይሁን እንጂ በዓሉ በተለያየ አካባቢና አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የክልሎቹ አካባቢዎችም ይከበር ስለነበር ጭርስኑ አልተዘነጋም።

ወደ ሰላም ስምምነት ከተገባ በኋላ የዘንድሮው አሸንድዬ፣አሸንዳ በዓል በትግራይ ክልል የመጀመሪያ ስለሆነ ያለውን ደባብና የበዓል ትውስታውን በተመለከተ እንዲህ ቃኝተናል።

በትግራይ ክልል ውቅሮ ተወልደው ያደጉትና አሁን ደግሞ መቀሌ ከተማ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት በስልክ ያገኘናቸው ወይዘሮ መሰረት ገብረዮሐንስ ትውስታቸውንና በአካባቢው ያለውን ድባብ እንዲህ አጫውተውናል። አሸንዳ አሸንድዬን ተጫውተው ያለፉበት ጊዜ ቢሆንም አሁን ላይ በሚገኙበት እድሜ ላይ ደግሞ ልጃገረዶቹ ሲጫወቱ ልጅነታቸውን ወደ ኋላ መለስ ብለው የሚያስታውሱበት በመሆኑ በጉጉት ነው የሚጠብቁት። በየአመቱም እንደ አዲስ የሚያዩትና ጥሩ ስሜት የሚሰጣቸው በዓል እንደሆነም ይገልጻሉ።

በዓሉ መንፈሳዊ ይዘቱ እንደሚያመዝን የሚናገሩት ወይዘሮ መሠረት፤ ልጃገረዶች ተሰባስበው በአካባቢያቸው እየተዟዟሩ ሲጫወቱ በጥሩ ያልተቀበላቸውን በግጥም ይሰድባሉ በጥሩ ያስተናገዳቸው ደግሞ ያወድሱታል፤ያሞግሱታል።

በየቤቱ ዞረው ተጫውተው ያገኙትን ገንዘብ እንኳን ከረሜላ ወይንም ሌላ ነገር በመግዛት ለግላቸው እንደማያውሉና ለቤተክርስቲያን እንደሚሰጡ ነው የነገሩኝ። ለጨዋታ ሲሰባሰቡም ሆነ ጨዋታቸውን ጨርሰው ሲለያዩ ማሳረጊያቸው ቤተክርስቲያን እንደሆነና ይህም መንፈሳዊ ይዘቱ ያመዘነ መሆኑን ማሳያ አድርገው ይገልጻሉ። በየቤቱ እየዞሩ የሚጫወቱትና እጁ ያልተፈታላቸውን ንፉግ ያሉትን ሰው በግጥም የሚያወርዱበትን የስድብ ናዳ ከባህላዊ ጋር ያያይዙታል።

ወይዘሮ መሠረት፤የአንድ አካባቢ ልጆች ተሰባስበው ከበዓሉ ዝግጅት ጀምሮ በጨዋታ ወቅትም ለቀናት አንድ ላይ ሆነው የሚያሳልፉት ጊዜ፣ስለሚለብሱት ልብስ፣ስለመዋቢያቸው፣ከበሮ የሚመታ፣ገንዘብ የሚሰበስብ መሪ መምረጥ፣እነማን ቤት እንደሚሄዱ ስለሚያደርጉት ምክክር፣የማይረሱት ትውስታ እንደሆነ ነው ያጫወቱኝ።

ሁሉም በጨዋታው ላይ ተውቦና ደምቆ ለመገኘት በሚያደርገው ዝግጅት አዲስ ልብስ እንዲገዛላቸው ቤተሰብ ማስቸገር የተለመደ ቢሆንም ከሌላ የእህትና የቤተሰብም ቢሆን ለብሶ በአቅም ለመድመቅ የሚደረገውንም ጥረት አንስተውልኛል። ነሐሴ ወር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሃሳቡም ቀልቡም የሁሉም ልጃገረዶች ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በዓሉ በከተማና በገጠር ልዩነት እንዳለውም አንስተውልኛል። እርሳቸው እንዳሉት የገጠሩ ከአለባበስ ጀምሮ ይለያል። በገጠሪቱ ክፍል ልጃገረዶች በእጅ ፈትል የተሰራ የባህል ልብስ ነው የሚለብሱት። በጨዋታ ወቅትም በየቤቱ ሲሄዱ ሳንቲም መስጠት አልተለመደም። ምግብ ነው የሚቀርብላቸው።

በከተማው በአልባሳት በኩል ሽፎን የሚባለው የጨርቅ አይነት በመለመዱ በስፋት የሚለበሰው ይኸው ነው። ሳንቲም መቀበልም ተለምዷል። በከተማ በእድሜ ከፍ ያሉም ተሰባስበው ይጫወታሉ። ክበረ በዓሉ እየሰፋ በመሄዱ በተለያዩ ተቋማትም መከበር ጀምሯል። የሚሳተፈውም ሰው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ለበዓሉ ትኩረት መሠጠቱና የሚሳተፈውም ሰው እየጨመረ መሄዱንም ወ/ሮ መሰረት ወደውታል። እርሳቸውም ለልጆቻቸው ለማስተላለፍ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነው የነገሩኝ።

በክልሉ ተካሄዶ የነበረው ጦርነት ትልቅ ጉዳትና ኪሰራ ያደረሰ መሆኑንና ነዋሪውም ከነበረው ጉዳት ውስጥ ገና ያልወጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ያለው የበዓል ድባብ የቀዘቀዘ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዓሉ እንዳይዘነጋ በትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስለተሰራው ሥራ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢትዮጵያ ህሉፍ እንደሚከተለው ገልጸውልኛል።

ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንደነገሩኝ የአሸንዳ በዓል ከቤተሰብ ነፃነት የሚገኝባት ቀን በመሆኗ ማንም አያሳልፋትም። ሌላ ቀን ከቤት አካባቢ የማትርቅ ልጃገረድ በአሸንዳ ጊዜ ግን ከአብሮ አደግ ጓደኞችዋ ጋር በመሆን ያለሰአት ገደብ በአካባቢዋ የመዟዟር ነፃነት ይሰጣታል።

ነፃነቱ ግን በጥበቃ የታጀበ እንደሆነ ነው ወይዘሮ ኢትዮጵያ የነገሩኝ። ልጃገረዶቹ ከቀናት በፊት ዝግጅት ሲያደርጉ በየቤቱ ሲዞሩ በመንገድ ላይ የሚተናኮል፣የያዙትንም ገንዘብ ለመቀማት የሚመክረውን የሚከላከልላቸው ወይንም የሚጠብቃቸው ከአካባቢያቸው ወንዶች እንደሚምርጡ ነው የገለጹልኝ። በዚህ አጋጣሚ ለእጮኝነት ለመምረጥም አሸንዳን ጠብቀው የሚወጡ ወንዶች እንዳሉም ነግረውኛል።

ወይዘሮ ኢትዮጵያ እጮኛ ለመምረጥ ብለው ከሚወጡ ጋር በተያያዘ እንደነገሩኝ፣ ሁሉም ልጃገረዶች አምረውና ደምቀው ስለሚወጡ ከመካከላቸው ቆንጆ ለመምረጥ ያስቸግራል። ያኔ አይኑ የገባች ልጃገረድ በኃላ ላይ እንዳሰበው ሊሆን ስለማይችል የአካባበው ማህበረሰብ ‹‹በአሸንዳ ጨዋታ ላይ ልጃገረድ አትምረጥ›› የሚል አባባል አለው። በአሸንዳ ላይ እጮኛ መምረጥ የተለመደው በተለይ በገጠሩ አካባቢ ነው።

በአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች በመኪናም ይሁን በእግሩ የሚሄድን ሰው በተለይ ወንዶች አስቁመው ይጫወታሉ። ጨዋታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ መጠበቅ እንጂ አልፎአቸው መሄድ አይቻልም። እንደውም አላፊ አግዳሚው ሳንቲም መስጠት ይጠበቅበታል። እነርሱም እስኪሰጣቸው ድረስ፤ መልኩን፣ቁመናውን፣ አለባበሱን፣ብቻ የሌለውን ሁሉ እያነሱ በግጥም ያወድሱታል። ሳንቲም ከሰጣቸው በምስጋና ይሸኙታል። ካልሰጣቸው ደግሞ በግጥም ንፉግነቱን ይገልጹለታል።

ሰውዬው ወይም ሴትዮዋ የልጃገረዶቹን ተግሳጽ ተቀብሎ መሄድ እንጂ ለምን የሚል ተቃውሞም ሆነ ለመማታት የሚመክር የለም።

ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንዳጫወቱኝ የአሸንዳ ልጃገረዶች በዓሉን በዚህ መልኩ ለማክበር ማልደው ነው ከቤታቸው የሚወጡት። ለጨዋታው ከመቸኮላቸው የተነሳ ቁርስ እንኳን አይጠብቁም። ወደ ቤታቸውም የሚመለሱት ምሽት ላይ ነው፡ለአሸንዳ ጨዋታ በቡድን በተሰባሰቡ ልጃገረዶች መካከል ያለው መተሳሰብና መከባበር፣ሲገናኙ ብቻ ሳይሆን ሲለያዩም ቤተክርስቲያን በመሄድ ለሚቀጥለው አመት በሰላም እንዲገናኙ በፀሎት፣መልካምና ቸር ተመኝተው ነው የሚለያዩት።

የአሸንዳ ጨዋታ በቡድን ስለሚካሄድ አንዱ ቡድን ሌላው ቡድን ላይ ያየውን ደስ የማይል ነገር ለመንቀፍ ሲል በግጥም የሚመላለሱት ነገርም አለ። ጨዋታው ካለቀ በኋላ ወደኋላ ተመልሶ ቂም የሚይዝ የለም። ሁሉም በጨዋታነቱ ስለሚወስደው በሰላም ነው የሚቋጨው። ይሄ ሁሉ ነው አሸንዳን አይረሴና ተናፋቂ የሚያደርገው።

በትግራይ ክልል አሽንዳ እንደየአካባቢው ስያሜ እንዳለውም ነው ወይዘሮ ኢትዮጵያ የነገሩን፣በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አሸንዳ፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ አይነዋሪ፣ማሪያ ተብሎ ይጠራል። በዓል አከባበሩ ላይ ግን ልዩነት የለውም። ወይዘሮ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከትውስታ በስተቀር ጨዋታውን ለልጆቻቸው አስተላልፈዋል። በተቻላቸው መጠንም ልጆቻቸው በበዓሉ እንዲታደሙና ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውንም ለማሟላት ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የገለጹልኝ።

አሸንዳ በአንድ ወቅት የዓደባባይ በዓልነቱ ጎልቶ የወጣበትንም ጊዜ ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንዲህ አስታውሰውናል። እርሳቸው እንዳሉት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሸንዳ በፌስቲቫል ደረጃ ጎልቶ እንዲከበር በሰፊው ተንቀሳቅሷል። እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርግም ወደ አስር አመት አካባቢ ይሆነዋል። በወቅቱም የአሸንዳ በዓል የመላው የትግራይ ሴቶች በዓል ተደርጎ ተወስዶ ነበር። ቀደም ሲል በዓሉ በድምቀት ሲከበር የነበረውም መቀሌና አክሱም ውስጥ ነው። መቀሌ ከተማ ላይ ከ16 እስከ 18 ባሉት ቀናት፣ተንቤን አካባቢ ደግሞ ከ18 እስከ 19 ባለው ጊዜ ይከበራል። የአሸንዳ በዓል አከባበር የሚጠናቀቀው አክሱም አይነዋሪ በሚባል ፕሮግራም ነሐሴ 24 ቀን በማካሄድ ነው።

አሸንዳ ከሴቶች በዓልነቱም ባሻገር ለተለያዩ የልማት ስራዎች ማነቀቃቂያ እንደሚውል ዳይሬክተሯ ነግረውናል። ለመልካም ነገር የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብም በዓሉን እንደ አንድ አጋጣሚም በመጠቀም ሥራዎች ተሰርተዋል። በዓሉ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን፣በቅርስነትም በተባበሩት መንግሥታት የባህል፣የትምህርትና ሳይንስ ድርጅት(ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ሲባልም የበለጠ ደማቅ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ነበር የቆየው።

የአሸንዳ በዓል በአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አካባቢዎች የሚወደድ እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሮ ኢትዮጵያ። አሁን የተገኘው ሰላም ተጠናክሮ ከቀጠለና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውም ሲረጋጋ ቀደም ሲል ይሰራበት የነበረው በዓሉን ወደ ፌስቲቫል ደረጃ የማሳደግ እንቅስቃሴ እንደሚቀጥልና አዳዲስ ነገሮችም ሲኖሩ በመቀመር ሥራዎች እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።

በነበረው ጦርነት ምክንያት ቢቆራረጥም አሁን ደግሞ ሰላም ሰፍኖ ወደ ቀደመው እንቅስቃሴ እየተገባ መሆኑ ይታወቃል። ምንም እንኳን ጦርነቱ ካደረሰው ጉዳት ለማገገም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም በዓሉ አመቱን ጠብቆ በመምጣቱ እንዲሁ ይታለፋል ወይ? የሚል ጥያቄ ወይዘሮ ኢትዮጵያ አንስተንላቸው በሰጡን ምላሽ፤ከጦርነቱ በፊት ተከስቶ በነበረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ጀምሮ ነው የአሸንዳ በዓል መቀዛቀዝ የጀመረው።

በኋላም አለመረጋጋቱ ተባብሶ ወደ ጦርነት ውስጥ በመገባቱ ነገሮች እየከፉ በመሄዳቸው በትግራይ ክልል ለሶስት አመታት ያህል የአሸንዳ በዓል አልተከበረም ማለት ይቻላል። ሰላሙ ከመጣ በኋላም ቢሆን ከነበረው አሳዛኝ ሁኔታ ህዝቡ ገና ስላልወጣ ሥነልቦናውም አልተመለሰም።

ሆኖም የትኛውም ችግር ቢያጋጥም በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ የመጣ በመሆኑ አሁንም የማስቀጠል ኃላፊነትን መወጣት ስለሚያስፈልግ በዓሉን በተለያየ ዝግጅት ለማክበር የሚያስችል የተለያዩ የቅድመዝግጅት ሥራዎችን ሰርቷል።

ቀድሞ በነበረው አይነት ድምቀት ለማክበር አቅሙም የማይፈቅድና ህብረተሰቡ አሁን ያለበትን ስሜትም ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ስለሚያስፈልግ፣ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው ዝግጅት የተደረገው።

ካርኒቫል የሚባለውን የአከባበር ሁኔታ በማካተት በተለያዩ ሰዎች የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡበት እንዲሁም ታዳጊዎችን የሚያሳትፍ የቁንጅና ውድድር መድረክ በማካሄድ፣ በዓሉ ይከበራል።

የትግራይ ተወላጆች የዲያስቦራ ማህበረሰቦችም የራሳቸው ፕሮግራም ይኖራቸዋል። ከዚህ ቀደም ተጀምሮ እንደነበረው በመሪ ቃል የአከባበር ሥነሥርዓት መሠረት የአሁኑም ‹‹አሸንዳችን ለሰላምና መልሶ መቋቋም›› በሚል መሪ ቃል ነው የሚከበረው።

በተለይም በጦርነቱ የተጎዱትን ለማገዝ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ይኖራሉ። የተጎዱትን የማቋቋሙ ተግባር በሥነ ልቦና ማረጋጋትንም ያካትታል። በዓሉ በመቀሌ፣ተቤንና አክሱም ቀደም ሲል እንደሚከናወነው ነው የሚፈጸመው።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 16/2015

Recommended For You