ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ማን ነው?

ነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ማን ነው?” በሚል ርእስ የግል አስተያየቴን ሰጥቼ ነበር። በወቅቱ ለንባብ በበቃው ጽሑፍ ላይ ባቀረብኩት አስተያየትም፣ አንድ ዲፕሎማት ብቁ ነው ከሚያስበለው ጉዳዮች ውስጥ የሚከተሉት ተጠቅሰው ነበር።

እነዚህም የአገራችንን ፖሊሲ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ሀሳቡን በጥሩ ቋንቋ መግለፅ የሚችል፣ ጥሩ የመግባባት ክህሎት ያለው፣ የተመደበበትን አገር ህግና ባህል የሚያከብር፣ በዓለም አቀፍ ህግ ለዲፕሎማቶች የተሰጠን መብትና ግዴታ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለአገር ክብርና ጥቅም ጠንክሮ የሚሰራ፣ በሥራ አጋጣሚ በእጁ የሚገኙ አገራዊ ሚስጥሮችን የሚጠብቅ፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችለውን በቂ መረጃና ንባብ የሚያከናውን የሚሉት ናቸው።

በእለቱም በሌላ ጽሑፍ ተመልሼ እንደምንገናኝ ለእናንተ ለአንባብያንም ቃል ገብቼ ነበር። እነሆ በቃሌ መሰረትም ዛሬም “ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ማን ነው?” በሚል ተመሳሳይ ርዕስ ያለፈው ጽሑፌ ቀጣይ ክፍል የሆነውን አስተያየቴን ያቀረብኩ ሲሆን፤ ከባለፈው እንደ ቀደመው ጽሑፌ ሁሉ በዚህም ጽሑፍ አንድ ዲፕሎማት ብቁ ሊያስብሉት የሚችሉ ቀሪ ነጥቦችን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

በተመደበበት አገር የራሱን አገር እንጂ የግል ጥቅም የማያስቀድም

በአገራችን ህግ መሰረት አንድ የፓርላማ አባል መቶ ሺ ህዝብ ይወክላል። በህግ የተደነገገ ባይሆንም አንድ አምባሳደር ወይም ከዚያ በታች ያለ ዲፕሎማት ወደ ውጭ አገር ተመድቦ ሲሄድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ ያላትን ኢትዮጵያ ወክሎ ነው የሚሰራው። በመሆኑም አንድ ዲፕሎማት ሆኖ ወደሌላ አገር የተሰማራ ሰው እራሱን ሳይሆን አገሩን ወክሎ ነው የሚሰራው። በዚህ ሂደት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው የአገሩ ጥቅም እንዲከበር ነው።

በዓለማችን ላይ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ መብትና ከለላ ይሰጣቸዋል። ይህንን ከለላ (Immunity) ለግላቸው ጥቅም ሳይሆን ለአገር ጥቅም እንዲያውሉት የተሰጠ ነው። በዓለም አቀፉ ህግ የተሰጠ ከለላን በመጠቀም ለግል ሥራ የሚጠቀምበት ከሆነ ተጠያቂ ከመሆን አያልፍም። በተለያዩ አገራት እንደሚሰማው አንዳንድ ዲፕሎማቶች የተሰጣቸውን ከለላ በመጠቀም የተለያዩ ህገወጥ ስራዎችን ሲሰሩ ይገኛሉ።

ይህ ዓይነት ተግባር ሲፈጸም ዲፕሎማቱ ከለላው ተነስቶ (Persona non grata) ወደ መጣበት አገር እንዲመለስ ይደረጋል። በመሆኑም አንድ አገርን ወክሎ በዲፕሎማትነት የሚሰራ ሰው የሚያከናውናቸው በጎም ሆነ በጎ ያልሆነ ተግባር የግለሰቡ ተደርጎ ሳይሆን የአገሩ እንደሆነ የሚቆጠረው። ስለዚህ ዲፕሎማቶች ቅድሚያ ለአገራቸው ጥቅም መቆም አለባቸው።

እውቀቱን ለአዲስ ዲፕሎማቶች ለማስተላለፍ የሚተጋ

አገራችን ኢትዮጵያን በመልካም ስም ያስጠሩ ጉምቱ ዲፕሎማቶች ነበሩን፤ አሁንም አሉን። እንዳንዶቹ በህይወት እያሉ ለተተኪ ትውልድ በማሰብ የስራ ልምዳቸውንና ተሞክሮአቸውን በመጽሀፍ በማሳተም አስተላልፈዋል። ብዙዎቹ ጉምቱ ዲፕሎማቶቻችን ግን ወደመጽሀፍ ሳይቀይሩት አልፈዋል። አገራቸውን ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩ በርካታ ዲፕሎማቶች በጡረታ ውስጥ የሚገኙም አሉ። አሁን በስራ ላይ ያሉት ታላላቅ ዲፕሎማቶቻችን እና በጡረታ ውስጥ ያሉ ዲፕሎማቶቻችን ለተተኪ ወጣት ዲፕሎማቶች እውቀታቸውን እንዲያስተላልፉ ማድረግ ይገባል፤ እየተደረገም ነው።

በመሆኑም የአንድ ጥሩ ዲፕሎማት መለኪያ ለበርካታ ዓመታት ያካበተውን ልምድ እና ተሞክሮ ለሌሎች ዲፕሎማቶች የማካፈል ፍላጎትና ተግባር ነው። በመጽሀፍ ላይ ስለዲፕሎማሲ ስራ ንድፈ ሀሳብ ማግኘት ይቻላል፤ የስራ ተሞክሮ ግን በስራ ውስጥ በማለፍ አሊያ ብዙ ተሞክሮ ካላቸው መማርን ይጠይቃል። ዲፕሎማሲ ስራ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ብቻ የሚሰራ አይደለም። ሌሎች ተቋማትም የአገራችንን ዲፕሎማሲ የሚያግዝ ስራ ይሰራሉ።

ለአብነት ያክል ፓርላማ የፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ያከናውናል። መከላከያ ሚኒስቴርም በወታደራዊ አታሼ አማካኝነት የዲፕሎማሲ ስራ ይሰራል። በመሆኑም አንድ ብቁ ዲፕሎማት ከሚያሰኝ መስፈርት ውስጥ እውቀቱንና ልምዱን ለሌሎች ዲፕሎማቶችና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ማስተላለፍ ሲችል ነው የሚል እምነት አለኝ።

የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን አጠቃቀሙ ጥሩ የሆነ

የዲፕሎማሲ ሥራ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሲሆን የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። አሁን ባለንበት ዓለም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መስፋፋት ለዲፕሎማቶች ሥራ እንደመልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ነው። በቀድሞ ጊዜ ይህንን መሰል ቴክኖሎጂ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ባልነበረበት ጊዜ የመንግስታትን መልዕክት ለሌላው ለማድረስ በእግር ጉዞ የሚከናወንበት እና በርካታ ወራት ወይም ዓመታት የሚወስድ ነበር። በአፄ ቴዎድሮስ እና በእንግሊዟ ንግስት በነበረችው ንግስት ቪክቶሪያ መካከል ሲደረግ የነበረውን የመልዕክተኞች ምልልስ እንደአብነት መውሰድ ይቻላል።

ከዚህ አንጻር ዲፕሎማቶች ዘመኑ የዋጀውን ቴክኖሎጂ ለስራቸው ያግዛቸዋል። መረጃዎችን ለመልቀቅም ሆነ ለመቀበል የተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎችን ማለትም ቲዊተር߹ፌስ ቡክ߹ ቴሌግራም እና ወዘተ መጠቀም ሲችሉ ለሌላው አገር ህዝብና ባለሥልጣናት ፈጣን ተደራሽ ይሆናሉ። ይህንን የዲፕሎማሲ ሥራ ግን የቴክኖሎጂውን አጠቃቀም ብቻ ማወቁ በቂ አይደለም።

የሚለቀቀውም መረጃ በጥንቃቄ የተዘጋጀ መሆን አለበት። አንድ ዲፕሎማት በሚለቀው የቲዊተር መረጃ የግሉ እምነት (ሀይማኖት߹ብሔርና ወዘተ) ላይ የተንጠለጠለ ሊሆን አይገባም። የግሌ አካውንት ነው በማለት እንደሌሎች ሰዎች ማንኛውንም መረጃ መልቀቅ ችግር ሊፈጥር ይችላል። ምክንያቱም መረጃው የደረሰው የውጭ አገር ሰው የኢትዮጵያ አቋም እንጂ የግለሰቡ አቋም አድርጎ አይወስደውም።

በመሆኑም ዲፕሎማቶቻችን የመረጃ ማግኛ እና መልቀቂያ የቴክኖሎጂ እውቀታቸው የላቀ እንዲሆን ያስፈልጋል። ብቁ ዲፕሎማት ከሚያሰኘው መስፈርት ውስጥ ለአገራችን የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉትን መረጃዎች ለሚመለከተው አካል በፍጥነትና በአግባቡ ማድረስ ሲችል ነው።

ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተባብሮ የሚሰራ (Team Sprit)

የዲፕሎማሲ ሥራ በቅንጅትና በትብብር እንጂ በአንድ ግለሰብ ብቻ የሚከናወን ሥራ አይደለም። በአንድ ኤምባሲ ውስጥ አምባሳደርና ሌሎች ዲፕሎማቶች የሚመደቡት በትብብር እንዲሰሩና ለአንድ ዓላማ እንዲሰሩ ነው። ለዚህም ሲባል የትብብር ሥራ ወይም (Team Sprit) መኖር የግድ ይላል።

በማንኛውም መስሪያቤት እንደሚከሰተው በሥራ ሂደት በሰራተኞች መካከል አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ይህ ሁኔታ ተፈጥሯዊ ነው። በአንድ ኤምባሲ ውስጥ የዲፕሎማቶች አለመግባባት ካለ ሥራውን በእጅጉ ይጎዳዋል። ሆኖም አገር ወክለው እየሰሩ እስከሆነ ድረስ ችግሮችን በጥበብ በመፍታት ማለፍ የግድ ይላል። አልያ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የሚጎዱት የአገር ጥቅምም አብሮ የሚጎዳ ይሆናል።

በመሆኑም የአንድ ብቁ ዲፕሎማት መለኪያ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተባብሮ እና ተቀናጅቶ የመሥራት አቅም፤ ፍላጎትና ችሎታው ሲኖረው ነው። ይህ ሲሟላ ሥራውም በአግባቡና በተያዘለት ጊዜ ይከናወናል።

በእቅድ የሚመራ እና የጊዜ አጠቃቀም ክህሎት ያዳበረ

አንድ ዲፕሎማት በእቅድ በመመራት የጊዜ አጠቃቀሙ የላቀ ሊሆን ይገባል። የጊዜ አጠቃቀም ስልት ማወቅ ለዲፕሎማቶች ወሳኝ ነው። ስኬታማ የጊዜ አጠቃቀም ስልት ያለው ዲፕሎማት ምንም ክህሎት ከሌለው ዲፕሎማት እጅግ የተሻለ ነው። ጊዜ ለሁሉም ሰው በእኩል የተሰጠ ሀብት ነው። ጊዜያቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙ ስኬታማ ሲሆኑ ይህንን የማይከውኑ ደግሞ በሥራቸውም ሆነ በግል ህይወታቸው ወደኋላ የሚቀሩ ናቸው።

አንዳንድ ሰው ገንዘቡን እንጂ ጊዜውን በእቅድ አይጠቀምም። በወር አንድ ጊዜ የሚከፈለውን ደመወዝ ለሰላሳ ቀናት አብቃቅቶ መኖር የሚችል ሰው የጊዜ አጠቃቀም ላይ ግን ለገንዘብ የሚሰጠውን ትኩረት ያህል አይሰጥም። ገንዘብም ሆነ ጊዜ በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው የሚባክኑ ናቸው። ገንዘብ ተመልሶ ሊመጣ የሚችል ቢሆንም የባከነ ጊዜ ግን ተመልሶ የማይገኝ ነው።

አንድ ጋናዊ ስለጊዜ አጠቃቀም ሲናገር እኛ አፍሪካውያን ጊዜን በአግባቡ ባለመጠቀማችንና በመዘግየታችን የአፍሪካ ጊዜ የሚል ስያሜ ተሰጥቶናል ብሏል። የዲፕሎማሲ ሥራ ከጊዜ አጠቃቀም ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው። አንድ ዲፕሎማት የቀጠሮ ሰዓት ማክበር አለበት። የቀጠሮ ሰዓት በጸሃፊ በኩልም ይሁን በሚያዘው ሞባይል ሶፍዌር አማካኝነት ጠንቅቆ መያዝ ያስፈልጋል። የቀጠሮ ቀንና ሰዓት ካላከበረ አንድ ዲፕሎማት በእራሱና በአገሩ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

ለአብነት ያክል በአንድ የባለብዙ ወገን ኮንፍረንስ ላይ የአገራችንን ጥቅም የሚመለከት ጉዳይ ላይ በሰዓቱ ሳይደርስ የቀረ ዲፕሎማት ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ መቀየር የሚችለው ነገር አይኖርም። በመሆኑም የአንድ ብቁ ዲፕሎማት መለኪያ የሰዓት አጠቃቀሙ ነው።

በውጭ አገር የሚገኙ ዜጎቻችንን ያለአድልዎ የሚያገለግል

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ከሶስት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይነገራል። ስርጭቱም የተለያየ ሲሆን በአሜሪካ፣ በአረብ አገሮች፣ በአውሮፓ አገሮችና በጎረቤት አገሮች ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ዜጎች ከአገር የሚወጡበት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው። በትምህርት፣ በዲቪ፣ በህገወጥ መንገድ በስራ እና ወዘተ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ዜጎች ናቸው።

በመሆኑም አንድ ዲፕሎማት የዜጎችን ግላዊ ሁኔታ (ሀይማኖት፣ ብሄርና ፖለቲካ አመለካከት) ግምት ውስጥ ሳያስገባ ለአንድ ዜጋ የሚሰጠውን አገልግሎት ያለአድልኦ የመስጠት ግዴታ አለበት። በመንግስት የተለየ ክልከላ የተደረገበት (exception) ጉዳይ እስከሌለ ድረስ ሁሉም ዜጋ ማግኘት ያለበትን የፓስፖርት፣ የቪዛ የደህንነት እና ወዘተ ጉዳዮች ሊነፈጉ አይገባም::

በሰው አገር ውስጥ ከሚደርስባቸው በደል እና ችግር አንፃር ትዕግስት የሌላቸውና ቁጡ የሆኑም አገልግሎት ፈልገው ሊመጡም ይችላሉ። በሳል ዲፕሎማት ግን ይህንን ግምት ውስጥ የሚያስገባ እና የዜጎችን ችግር በአግባቡ እንዲፈታ ያደርጋል። ይህ ሲሆን ነው በውጭ አገር የሚኖሩ የዜጎች መብት የሚከበረው።

እነዚህ ዜጎቻችንን የእውቀት፣ የማቴርያል፣ እና የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ የአገርን ኢኮኖሚ የሚያግዙ ፕሮጀክቶችንና ኢንቨስትመንቶችን ማከናወን የሚቻለው እነሱንም ማገልገል ሲቻል ነው። በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎች አካላቸው እንጂ ልባቸው ሙሉ በሙሉ ውጭ አገር ነው ማለት አይቻልም። ዜግነት የቀየሩትም እንኳን ተመሳሳይ ስሜት ለአገራቸው አላቸው። በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ማድረግ የአንድ ጎበዝ ዲፕሎማት ስኬት ነው።

የተመደበበት አገር ሁኔታ በጥልቀት የሚከታተልና የአገር ጥቅምን የሚያይ

መንግስታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመፍጠር ኤምባሲ የሚከፍቱት ከዚያ አገር ጋር በሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ጥቅም አገኝበታለሁ ብለው ሲያስቡ ነው። ምንም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ባህላዊ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት የሌላቸው አገሮች ኤምባሲዎችን አይከፍቱም። አንድ ኤምባሲ መክፈት ማለት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቅ በመሆኑ ትርፍና ኪሳራ አብሮ ይታያል። ትርፍ የግድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ላይሆን ይችላል፤ የፖለቲካ ትርፍ የሚያመጣም ከሆነ ኤምባሲ ሊከፈትበት ይችላል።

በመሆኑም አንድ የውጭ አገር የተመደበ/በች ዲፕሎማት አንዱና ዋናው ስራ ስለተመደበበት አገር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ማወቅና በጋራ ሊያሰሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማግኘት ነው። ለዚህም ሲባል የተመደበበትን አገር ፖሊሲና የየእለት ሁኔታ መከታተል ያስፈልጋል።

ለምሳሌ በአንድ የአውሮፓ አገር የተመደበ ዲፕሎማት የተመደበበት አገር ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያለንን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትስስር ትኩረት ሰጥተን ለመስራት ወስነናል የሚል መረጃ ቢለቁ ይህ ምን ጥቅም ለአገር ሊያስገኝ ይችላል በሚል መረጃዎችን ማጠናከር፣ የሚመከታችውን ባለስልጣናት የማነጋገርና አገራችን ጋር በጋራ ብንሰራ የሚጠቅም መሆኑን ማሳየትና የስበት ኃይል መሆን ይገባዋል። ይህንን ለማድረግ መነሻ የሚሆነው የተመደበበት አገር ፖሊሲ፣ ውሳኔ እና ፍላጎት በጥልቀት በመከታተልና በማወቅ ነው።

ጥሬ መረጃዎችን የመተንተን ብቃት

በአሁኑ ጊዜ ዲፕሎማቶች በመረጃ ማነስ ብቻ ሳይሆን በመረጃ ብዛትም ይቸገራሉ። የሚገኝ መረጃ ሁሉ ለትንታኔ የሚጠቅም ላይሆን ስለሚችል የመረጃ ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የመሰብሰብና የመተንተን አቅም ሊኖር ይገባል። በተበታተነ መልኩ የሚገኙ መረጃዎችን አገጣጥሞ ስዕል የሚሰጥ ትንታኔ መስጠት የአንድ ጎበዝ ዲፕሎማት ተግባር ነው። ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የተተነተነ መረጃ (Analysis) ለእውነታ በጣም የቀረበ በመሆኑ ለውሳኔ ሰጪዎች እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።

ዲፕሎማቶች ለስራ የሚያስፈልጓቸውን እስከ ዘጠና ፐርሰንት የሚሆን መረጃዎች በግልፅ ከተለቀቁ (open source) ውስጥ ሊያገኙ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ። የቀረውን አስር ፐርሰንት መረጃ ሌሎች ሰዎችን በማግባባትና እንደ አስፈላጊነቱም የኢንተለጀንስ ባለሙያዎች ሊያሟሉት የሚችሉት እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

ይህ ማለት ከፍተኛ ጥሬ መረጃ በነጻ የተለቀቁ ከመሆናቸው አንፃር እነሱን በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ቅርፅ ያለው ትርጉም መስጠት የአንድ ዲፕሎማት ዋና ስራው ነው። መረጃን የመሰብሰብና አደራጅቶ የመተንተን ብቃት መኖር በውጭ ግንኙነት ስራ ዙርያ ውሳኔ ለመስጠት ያግዛል። ጠንካራ ዲፕሎማት ይህንን ክህሎት ያዳበረ ነው።

በእርግጥ ዲፕሎማቶች የሚያከናውኑት ትንታኔ መለስተኛ ጥናት በማድረግ እንጂ እንደአካዳሚክ ጥናት እጅግ ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ አይደለም። ይህንን ለማከናወን በቂ ጊዜም የላቸውም። ጥልቅ ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ሲኖር ለዚህ የተቋቋመ የምርምር ተቋም የሚያከናውነው ነው።

በመግቢያዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ነሀሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ማን ነው?” በሚል ርዕስ ያወጣሁት ጽሑፍም ሆነ ዛሬ በተመሳሳይ ርዕስ ያቀረብኩት ሃሳብ አንድ ዲፕሎማት አገሩን ወክሎ ወደ አንድ ሀገር ለስራ ሲመደብ ቢያንስ ምን ምን መሰረታዊ ጉዳዮች ሊኖሩት ይገባል የሚለውን ግንዛቤ ያስይዛሉ ያልኳቸው ነጥቦች ናቸው። እናንተ አንባብያንም በዚህ ላይ መጠነኛ ግንዛቤ እንደያዛችሁ አምናለሁ። ለዛሬው በዚህ አበቃሁ። ሰላም !

ከመላኩ ሙሉዓለም ቀ.

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የውጭ ግንኙነት ተመራማሪ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 16/2015

Recommended For You