ክረምቱን – በክረምት

 በእኔ እይታ ክረምት ሲባል ከራሱ ውበትና ትዝታ ጋር ይታወሳል፡፡ ሰኔ ‹‹ግም›› ሲል አንስቶ በዝናብ የሚርሰው የደረቅ አፈር ሽታ ስሜቱ የተለየ ነው። በጋውን ክው ብሎ የከረመው መሬት አቧራውን ከልቶ ከእርጥበት ሲዋሀድ ሽታው ልዩ ትርጉም አለው፡፡ አንዳች የተለየ ነገር ውስጥን ሰቅዞ ይይዛል፡፡

ይሄኔ አካል ቢበርድ፣ ቢቀዘቅዘው ተኮራምቶ እንደማይቀር ያውቀዋል፡፡ ለምን ቢሉ ቀጥሎ የምትወጣውን ደማቅ ፀሐይ ተስፋ ያደርጋልና፡፡ በክረምቱ የአፈሩ ሽታ አፍንጫን አይረበሽም፣ ዓይኖች ደንግጠው አያፈጡም፡፡ ሁለመና ለዚህ ስሜት እጅ ይሰጣል፣ ሁሉም በሚሆነው እውነት ለሚታየው ዓለም ራሱን ያስገዛል፡፡ ለታላቁ ክረምት፤ በወቅቱ ለሚመጣው በረከት፡፡

ክረምት ለእኛ ጊዜን ቆጥሮ የሚደርስ ብርቃችን ነው። ወቅቱን ደርሶ በመጣ ጊዜ ‹‹ኤጭ! ወዲያ›› አንለውም፡፡ ‹‹መጣልን›› እንጂ ‹‹መጣብን›› ስንል አንሰማም፡፡ እርግጥ ነው በክረምት አንጀት በሚገባ፣ ውስጥን በሚያንሰፈስፍ ብርድ እንጎበኛለን፡፡

ይህን ጊዜ ሞቅ ባለ ልብስ ተጀቡነን፣ የሚያመች ጫማን ረግጠን በፍቅር አናጣጥመዋለን፡፡ እንዲህ በመሆኑም አንማረርም፣ አንበሳጨም፡፡ የዚህ ወቅት ብርድና ውርጭ ለአብዛኞቻችን በጊዜው ፋሽን የመድመቂያ ሰዓት ነው፡፡ ካፊያ ዝናቡ፣ ዳመና ጨለማው በረከት እንጂ መርገምት አይሆንም ፡፡

የክረምቱ ውርጭ አንጀት ገብቶ ሁለመናን ሲያርድ፣ ሲያንቀጠቅጥ ጥርስ አይነከስበትም፡፡ ቂም አይያዝበትም። ለአፍታ ብልጭ የምትለውን ፀሐይ መሻማት፣ መናፈቁ የልምድ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ጣይቱ ‹‹ደመቀች፣ ፈዘዘች›› ብሎ የሚቆጣ፣ የሚያማት አይኖርም፡፡ ሁሉም እንደጊዜው ባህርይ ውሎ፣ አምሽቶ ያድራል፡፡

የክረምቱ ጊዜ በትምህርት ለከረሙ የአንድ መንደር ልጆች ፈንጠዝያቸው ነው፡፡ እነሱ ጭቃውን፣ የመንገድ ላይ ጎርፉን አይጠየፉም፡፡ ባሻቸው ጊዜ ከልንቁጡ፣ እያቦኩ ፣ እያዳለጡ በውሃው እየተራጩ፣ መንቦራጨቅ መብታቸው ይሆናል፡፡

ይህ ወቅት በምድር ለሚገኝ ተፈጥሮ ሁሉ ጸጋን ያላብሳል፡፡ ዛፍ ቅጠሉ፣ ጋራ ሸንተተሩ መልኩን የሚቀይረው፣ አረንጓዴ ስጋጃ የሚጎናጸፈው ይህን ጊዜ ነው፡፡ የክረምቱ በረከት ሁሌም ከበጋው ጊዜ ይለያል። ቅዝቃዜው ቢኖርም አካል አይኮሰኩስም፡፡ ዝናብ፣ ዳመናው ብቅ ባለጊዜ አንደበት ቃል ያለው ምስጋናን ይቸራል፡፡ በደስታ ይሞላል፡፡

በጭንቅ የሚገኘው የክረምት ሙቀት ከሰውነት ሲደርስ ሀሴትን ያለብሳል፡፡ መልሶ ውስጠት በብርድ ሲያዝ ደግሞ ማዘን፣ መማረር አይኖርም፡፡ ሁሉም ጊዜውን ያውቀዋል፡፡ ተፈጥሮውን ያስበዋል፡፡ በዚህ ወቅት ማልዶ የሚነቃ አካል፣ ዕንቅልፍ ያልጠገበ ዓይን፣ ከሙቀቱ ወጥቶ ከዝናብ ከውርጩ ቢገባ አይደንቅም። የክረምቱ ልማድ የወቅቱ መገለጫ ነውና፡፡

በእኔ እይታ ክረምት ከነችግሩ ውብ ነው፡፡ ከነሰንኮፉ ጣፋጭ ነው፡፡ አዎ! የክረምት ትዝታዎች አይረሴ ናቸው። በዚህ ውቅት የሚሰሙ ሙዚቃዎች፤ የሚደመጡ ግጥሞች፣ የሚነበቡ መጽሐፎች ለአይምሮ ደማቅ ዐሻራ ያትማሉ። እፍ… እያሉ የሚገምጡት ትኩስ ድንች፣ ከፍም እሳቱ የሚያገላብጡት እሸት በቆሎ፣ ከምድጃ ዳር የሚያወጉት ደማቅ ጨዋታ ሁሉ በክረምት ትርጉሙ ይለያል፡፡ ትውስታው ያይላል፡፡

አንዳንዴ ግን ሰዎች በሚፈጥሩት ክፉ ድርጊት ክረምት ይሉት ጉዳይ እንዲጠላ ይሆናል፡፡ ወቅቱ በታወሰ ጊዜ ፍርሃት፣ ንዴት ያጭራል፡፡ ጊዜው በደረሰ አጋጣሚ ‹‹ባልመጣ፣ ባልሆነ›› ያሰኛል፡፡ እንዲህ መሆኑ የክረምት ስምን በእጅጉ ያጎድፋል፣ በረከት፣ ጸጋውን ያጎድላል፡፡

ወዳጆቼ! እንዲህ ማለቴ በአንዳች ምክንያት ነው፡፡ አንዳንዶች ክረምትን ለክፋት ይጠቀሙታል፡፡ ለተንኮል ያስቡታል፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ጊዜውን የሚሹት ለበጎነት አይደለም፡፡ ለእነሱ ዝናቡ ሙቀታቸው፣ ጨለማው ብርሃናቸው ነው፡፡ ብርዱን እንደ ፀሐይ ይሞቁታል፣ ጭቃ ድጡን፣ ዶፍ በረዶውን አብዝተው ይሹታል፡፡

ጨለማን ተተግነው የወቅቱን ዝናብ ተጠቅመው ማጅራት የሚመቱ ዘራፊዎች የጨረቃዋ መድመቅ፣ ተመችቷቸው አያውቅም፡፡ ሁሌም ሥራቸው በሽፍንፍንፍ ነው፡፡ ለእነሱ የክረምቱ መግፋት ‹‹በበሶ ላይ ቅቤ›› ይሉት አይነት ይሆናል፡፡ ዘወትር ዝናቡ ያግዛቸዋል፡፡ ዳመናው ጥላና ዳስ ሆኖ ይሸፍናቸዋል፡፡

እንዲህ አይነቶቹ ቀማኞች የክረምቱን መምጣት የሚጠብቁት በታላቅ ናፍቆትና ጉጉት ነው፡፡ ይህ ወቅት በበጋው ዓመቱን ሙሉ ያላገኙትን በረከት ያሳፍሳቸዋል። በረከታቸው በሥራ ድካም የተባረከ አይደለም፡፡ ይህ እውነትም አስጨንቋቸው አያውቅም፡፡ ጠብ ሲል ጥግ ይይዛሉ፣ ዳመና ከጨለማው፣ ዝናቡ ከድጡ ተባብረው ያግዟቸዋል፡፡ ያሻቸውን ይመታሉ፣ ያገኙትን ይዘርፋሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ በክረምቱ መምጣት የራሳቸውን ዓለም የሚፈጥሩ ክፉዎች ናቸው፡፡ እነዚህኞቹ ደስታቸው የሚደራው ሌሎችን በማስቀየምና በማስከፋት ይሆናል። እጃቸው የመኪናቸውን መሪ በያዘ ቁጥር አዕምሯቸው ተንኮል ለማፍለቅ ይዘጋጃል፡፡

በእነሱ ዘንድ ዝግ ብሎ ማሽከርከር ይሉት እውነት እንደ ነውር ይቆጠራል፡፡ ሆን ብለው ጎርፍ ባቋተው መንገድ እየከነፉ ያልፋሉ፡፡ ሁኔታዎች ለመለወጥ አፍታ አይፈጁም፡፡ የጎማ ሀይል የረገጠው ለጥ ያለ ውሀ ዘይት እንዳየው ፈንድሻ በየአቅጣጫው ይረጫል፡፡

ይሄኔ በመንገድ የሚልፉ እግረኞችን አለማየት ነው፡፡ ጭቃ ያዘለውን ቆሻሻ ውሃ ሊከናነቡት ግድ ይሆናል፡፡ ወዲያውኑ ከእያንዳንዱ አንደበት ሀዘንና ብሽቀት የወለደው እርግማን ይዥጎደጎዳል፡፡ ‹‹ይድፋህ፣ ይገልብጥህ፣ ሞትህን ያቅርበው›› ሌሎችም ከባድ እርግማኖች ጎልተው ይሰማሉ፡፡

በሆነው ሁሉ አንዳች የማይመስለው ሾፌር በመኪናው መስታወት ሁኔታውን እንደዋዛ አየት አድርጎ በፍጥነቱ ይቀጥላል፡፡ እንደውም አንዳንዱ ድርጊቱ ላይ ሞቅ ያለ ፈገግታና ሳቅ ያክልበታል፡፡ ሁኔታውን ከመጤፍ ባለመቁጠርም አሳፋሪ ሥራውን ሊዝናነበት ይሞክራል።

ይህ አይነቱ አጋጣሚ ባብዛኛው በግዴለሽነት፣ ሆን ብሎ በማድረግና በስህተት ጭምር ይፈጸማል። በክፉ ምግባራቸው የሚረኩ እንዳሉ ሁሉ ባደረሱት ሞራላዊ ጉዳት ከልብ የሚጸጸቱ ልበ መልካሞችም አይታጡም። እነሱን በይቅርታ እናልፋቸዋለን፡፡

ወደ ምስኪኖቹ መንገደኞች ስናቀና ግን ችግራቸውን ከብዙ አቅጣጫ መቃኘት ይቻላል፡፡ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ ለልዩ ዝግጅት በክት ልብሳቸው ዘንጠው፣ ተውበው ይሆናል፡፡ የምንለው ይህ ልብስም ነጭ የሀገር ልብስ፣ አልያም በቀላሉ ውሃ አጥቦ የማይጸዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ እውነት ደግሞ ካላሰቡት የሚያውል፣ ካለቀዱት የሚያደርስ ነው። ሰዎችን ከጉዳያቸው፣ ጉዳዮችን ከግባቸው ያናጥባል፡፡

የክረምቱ መልከ ብዙ ገጽታ በብዙ አጋጣሚዎች፣ በክፉና ደግ ትውስታዎች ይገለጣል፡፡ ክረምት ብቅ ሲል በመልካም ጎኑ እንደሚታይ ሁሉ ወቅቱን ተከትለው የሚመጡ ክፉ አጋጣሚዎች ጥቁር ዐሻራቸውን አሳርፈውበት ያልፋሉ፡፡ ክረምት በእኛ ዘንድ በዥንጉርጉር ገጽታው፣ በአይነት ብዙ መገለጫው ይታወቃል። ክረምቱን ክረምት ላይ ሆነን ስናስብም በጎነቱን አስታውሰን፣ ክፉ አጋጣሚውን ወቅሰን እንሸኘዋለን። ለከርሞ ለመልካሞቹ መልካሙን ተመኝተን፣ ለክፉዎቹም ጥሩ ልቦናን አስበን፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *