የቱሪዝም ዘርፍ የትኩረት አቅጣጫዎችና አፈጻጸሙ

የኢትዮጵያ መንግሥት የብዝኃ ኢኮኖሚው ምሰሶ ከሆኑት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና የአይሲቲ ዘርፎች መካከል ቱሪዝምን አካቶታል። በዘርፉ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት መገንባት እንደሚቻልም ታምኖበት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰፋፊ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል። ከዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መገንባት፣ ነባሮቹን ማልማትና መጠበቅ እንዲሁም የዓለም የቱሪዝም ገበያን ሰብሮ በመግባት ከኢንዱስትሪው ድርሻ መቋደስ የሚሉት ናቸው፡፡ በተለይ በገበያና ፕሮሞሽን ኢትዮጵያን በስፋት በማስተዋወቅ የቱሪዝም ፍሰቱን መጨመር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ነው።

የቱሪዝም ዘርፍ ከባህል ተነጥሎ በሚኒስቴር ደረጃ እንዲዋቀር ከመደረጉም ባሻገር በሰው ኃይል እንዲሁም በቴክኖሎጂ እንዲደራጅ የማድረግ ተግባር መከናወኑን መረጃዎች ያሳያሉ። አዲስ የተቋቋመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም በብቁ ቁመና ዘርፉን ለመምራት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንና መሬት የወረደ ሥራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። የዝግጅት ክፍላችንም በአዲስ መልክ የተደራጀው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አቅዶ የፈፀማቸውን ተግባራትን እና በዘርፉ የሚታዩትን ተግዳሮቶች በተመለከተ ከህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ክፍል ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ጋር ቆይታ በማድረግ የሚከተለውን ዳሰሳ ይዞላችሁ ቀርቧል።

ሥራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ ጌታቸው የቱሪዝም ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የያዛቸው የቱሪዝም ሀብቶች ጥበቃና ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻና ምርት ልማት፣ የቱሪዝም ገበያ ልማት፣ የቱሪስት አገልግሎቶች ልህቀትና ተቋማዊ አቅም ግንባታ እንደሆኑ ይናገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀዳሚነት ተቋሙ አዲስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንደመሆኑ መጠን ራሱን በባለሙያ፣ በቢሮ እና በልዩ ልዩ መልኩ ሲያደራጅ መቆየቱን ይገልፃሉ። ይህንን በተሳካ ሁኔታ አጠናቆም ወደ ዋና ተግባርና ኃላፊነቱ መግባቱን ይናገራሉ።

“በቀዳሚነት በ2015 ዓ.ም ከቱሪዝም ሀብቶች ጥበቃና መዳረሻ ምርት ልማት አንፃር በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል” የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ የመጀመሪያው ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እሴት መጨመርና አዳዲስ መዳረሻዎችን ማልማት ነው። በተለይ ከአዳዲስ መዳረሻዎች ጋር በተያያዘ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የሚተገበሩ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገር እና ለትውልድ ፕሮጀክቶች ላይ መስሪያ ቤቱ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል። የበጀት ምንጩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የሚሰባሰብ ቢሆንም ከባለሙያ ድጋፍ እና ሙያዊ ጉዳይ አንፃር የድርሻውን ወስዶ እየሰራ ይገኛል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እሴት መጨመርና ማልማት ላይ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀው፤ ሶስት መዳረሻዎች ላይ ጥገና ለማከናወን ታቅዶ በተለይ በሁለቱ ላይ መልካም አፈፃፀም መታየቱን ይናገራሉ። አንደኛው የጅማ አባጅፋር ቤተመንግሥት ጥገና ሲሆን፤ የአባጅፋር ቤተመንግሥት ከቱሪዝም መዳረሻ ስፍራነት አንፃር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ውስጡንና ቅጥር ግቢውን ለማልማት ጥናት ተደርጎ፣ ቁሳቁስ ልየታ ተከናውኖ ወደ ጥገና መገባቱን ይናገራሉ። ይህ ሥራ በሂደት ከመጠናቀቁ አኳያ የዓመቱ አፈፃፀም መልካም የሚባል ደረጃ ላይ ነው።

ሌላው የስንቅሌ ፓርክ ነው። ከስንቅሌ ጋር በተያያዘ ወደ ስፍራው መድረሻ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የእደ ጥበብ ማምረቻና መሸጫ ማእከል ግንባታ ሥራ ተከናውኗል፡፡ የፓርኩ አፈፃፀም በተናጠል ሲታይ 90 በመቶ ድርሻ ይወስዳል። ስራው መቶ በመቶ ሲጠናቀቅ በፓርኩ የሚገኙ ቱሪስቶች ማህበረሰቡ የሚያመርተውን እደ ጥበብና የአካባቢው መገለጫ የሆኑትን ባህላዊ ሀብቶች በቀላሉ ሸምቶ እንዲሄድ ያስችላል። በተያያዘም ማህበረሰቡ የሥራ እድልና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ያገኛል። ስለዚህም በእነዚህ ቦታዎች ላይ 65 በመቶ በሚሆን ድርሻ በዓመቱ አፈፃፀም ውጤት ተገኝቷል።

“እሴትን ከመጨመር አንፃር በተጨማሪ በሀረርና በድሬዳዋ ላንድ ማርክ ‘ምልክት’ ተሰርቷል። በላሊበላ ለቱሪስቶች ምቹ አገልግሎት የሚሰጡ የንፅህና መጠበቂያዎች ተሰርተዋል” የሚሉት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ በዋናነት የዚህ ምልክት አላማ ወደ ከተማውና ወደ ክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገቡ ቱሪስቶች ዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ መሆናቸውን በቀላሉ እንዲረዱና ሙሉ መረጃ የሚሰጡ ናቸው።

ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጋር በተያያዘ ጎብኚዎች ከዚህ ቀደም በስፍራው ሲገኙ መፀዳጃ ይቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ በስፍራው ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥና የቱሪስቶችን ምቾት የሚጠብቅ ንፅህና መጠበቂያ ስፍራ ተዘጋጅቶ ርክክብ ተደርጓል። በነባር መዳረሻዎች የተሰራው ሥራ በዚህ ሳያበቃ በብሄራዊ ሙዚየም የስነ ህንፃውን ውበት እና ቅርፅ በጠበቀ ደረጃ እንዲታደስና ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆን መደረጉን ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪዝም መረጃ ለመስጠትና የመስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስፈፃሚው፤ በዋናነት የመረጃ አሰጣጥ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል። በተለይ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ላይ “የቱሪስቶች የመረጃ ማእከል” ግንባታ ተጠናቋል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተመርቆ ክፍት ይሆናል። ይህ ዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ጎብኚዎች በቂ መረጃ አግኝተው ካቀዱት በላይ የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ አማራጭ እድል የሚሰጥ ነው። በተጨማሪ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መኖሩን ገልፀው፣ በመስቀል አደባባይና በክልሎች አካባቢ ተመሳሳይ የዲጂታል መረጃ መስጫ ሥርዓት ለመገንባት ጅምር ስራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በ2015 ዓ.ም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእቅድ ይዞ ካከናወናቸው ተግባራቶች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የንግድ ለንግድ አውደ ርእይ፣ ኮንፍረንሶችና መድረኮች ላይ ማስተዋወቅ ነው። የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ክፍል ሥራ አስፈፃሚው ይህንን አስመልክቶ በዓመቱ በርካታ ተሳትፎዎች እንደነበሩ ገልፀዋል። በተለይ የቱር ኦፕሬተሮችን፣ ማህበራትን እና ባለድርሻ አካላትን አሳትፈው የእንግሊዝ ዋና ከተማ ሎንዶን፣ ጀርመን፣ ስፔንን ጨምሮ ከ15 ያላነሱ ቦታዎች ላይ ተሳትፎ ተደርጓል። ይህም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን አቅም ማስተዋወቅ ከመቻሉም በላይ የጉዞ ወኪሎች፣ ክልሎችና መሰል ባለድርሻዎችን በእነዚህ መድረኮች ላይ ማሳተፍ ያስቻለ ነበር።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2015 ዓ.ም ካከናወናቸው ተግባራቶች ውስጥ አንዱ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር እና የጉብኝት ባህልን ማሳደግ መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስፈፃሚው አቶ ዓለማየሁ፤ በዓመቱ “የልወቅሽ ኢትዮጵያ” ንቅናቄን በመፍጠር ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል። በተለይ ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን በአግባቡ እንዲያውቁ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮችን በመጠቀም የማስተዋወቅና ወደ ስፍራው አቅንተው ጉብኝት እንዲያደርጉ የመቀስቀስ ሥራ ይገኝበታል።

የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት እና ዜጎችን ተሳታፊ ለማድረግም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በትብብር በአርሲ በቆጂ፣ በአዋሳና በአዲስ አበባ ሁነቶችን ከመዘጋጀታቸውም ባሻገር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን “ የጉብኝት ቁጠባ” ፕሮጀክት አስተዋውቀዋል። የተራራ መውጣት (ሀይኪንግ)፣ የካምፒንግ፣ ጀልባ ቀዘፋ (ራፍቲነግ) እና መሰል አዳዲስ ስፖርታዊ ተሳትፎዎች ላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማበረታታት ተሞክሯል። በየትምህርት ቤቱና በየተቋማቱ የጉዞ ማህበራት እንዲመሰረቱና ዜጎች ሀገራቸውን በሚገባ የሚያውቁበት አማራጭ እንዲኖርም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጉዞ ወኪሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች መሰል የዘርፉ ማህበራት የሚነሱ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር ልዩ ልዩ ስራዎች እንደሚሰራ የሚያነሱት ሥራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ፤ በተለይ ለጎብኚዎች የቪዛ አሰጣጥ ቅልጥፍናና ፍጥነት ጋር በተያያዘ፣ ለጉብኝት አላማ የሚውሉ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቁሳቁሶች (ካሜራና መሰል ኤሌክትሮኒክሶች) ጋር በተገናኘ የሚነሱትን ቅሬታዎች ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ይናገራሉ። ይህን መሰልና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ለሚነሱ ቅሬታዎች መፍትሄ እንዲሆንም ከባለድርሻ አካላት፤ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ጋር ምክክር ለማድረግና መፍትሄ ለማስቀመጥ በቅርብ ጊዜ ውስጥ “የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ኮንፍረንስ” ለማዘጋጀት መታሰቡንም ያብራራሉ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2015 ዓ.ም ካከናወናቸው ተግባራቶች መካከል በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት የወደሙ መዳረሻዎችን ጥገና የተመለከተ ነው። ይህንን በሚመለከት ሥራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ እንደሚሉት፤ በጦርነቱ ወቅት የተጎዱና ጥገና የሚያስፈልጋቸው ቅርሶችን በዳሰሳዊ ጥናት ለመለየት ተችሏል። ከዚህ ባሻገር በጥገና ወቅት ቅርሶቹ የሚወስዱት በጀትና የሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅም “በግምታዊ ስሌት” ተለይቶ ታውቋል። ሌላው የፋይናንስ ምንጮችን የማፈላለግና የመጠቆም ተግባርም ለሚመለከተው አካል ቀርቧል።

“በጦርነቱ አማካኝነት የወደሙ ቅርሶችን ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት አቅም መልሶ ለማልማት አስቸጋሪ ነው” የሚሉት ሥራ አስፈፃሚው፤ የቅርሱን ባህሪ፣ የቅርሱን እድሜ እና ያንን እንደነበረ መልሶ ለመጠገን የሚያስችል የተለየ ሙያ ስለሚጠይቅ የሚወስደው የፋይናንስ አቅምም ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህ የተነሳ የሚፈለገው በጀት ሲገኝ በቅደም ተከተል (ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በማስቀደም) የቅርስ ጥገናና መልሶ ግንባታ ሥራ እንደሚከናወንም ይናገራሉ፡፡

ቱሪዝም ራሱን ችሎ በሚኒስቴር ደረጃ መዋቀሩ ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን የሚያመላክት ጅምር ነው የሚሉት ሥራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ፤ ውሳኔው እንደ መልካም እድል የሚታይ መሆኑን ይገልፃሉ። በ2015 ዓ.ም ሌላው ወሳኝ መልካም አጋጣሚ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በተሻለ ደረጃ ለማስተዋወቅና የጉብኝት ባህልን ለመፍጠር የተሰራው ሥራ ድርሻ እንዳለው ይገልፃሉ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድና የጉዞ ትርኢቶች ላይ የማስተዋወቅ ተግባሩም በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ አመርቂ አፈፃፀሞች ውስጥ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወስድ የሚናገሩት አቶ አለማየሁ፤ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ እክሎች መኖራቸውን ይገልፃሉ። ከዚህ ውስጥ አዳዲስና ነባር መዳረሻዎችን ለማልማት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ከፍተኛ የሀብት አቅርቦት ችግር እንዳለም ይናገራሉ። በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ መስህብን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በበቂ ሁኔታ በታዋቂ መገናኛ ብዙኃን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የገፅታ ግንባታ ስራን ለማከናወን በተመሳሳይ የአቅምና የሀብት ችግር መኖሩን ያነሳሉ፡፡

ሌላው ችግር ጎብኚዎች ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ከቪዛ አሰጣጥ አንፃር ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ችግር እንደሚስተዋል ያነሱ ሲሆን፤ ከላይ የጠቀሷቸውን የሀብት እጥረት የመሰሉ ተግዳሮቶች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ለመፍታት እየሞከሩ መሆኑን ተናግረው፤ ከቪዛና መሰል ቅሬታ የሚፈጥሩ ችግሮች ጋር በተያያዘ ደግሞ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ሥራ አስፈፃሚ አካላት ጋር በመምከር መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ በተያዘው የበጀት ዓመትም ቁልፍ ተግባራትን ለይቶ በቱሪዝም ዘርፉ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *