አዲስ አበባ፡- ሲፒዩ ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚካሄደው የምርምር ስራ ውጤታማ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገለፀ፡፡
በምርምር ስራዎች ላይ ከዓለም አቀፍ የእውቀት ልውውጥ ትስስር ድርጅት (ጂኬን) ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡ የሲፒዩ ኮሌጅ አካዳሚክ ዲን አቶ ብሩ ደስታ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ሰአት ኮሌጁ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡ ተማሪዎቹ ውጤታማ የሆነ ትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ከጂኬን ጋር የምርምር ስራዎችን በትብብር በመስራት ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት እየሰራ ነው፡፡ ኮሌጁ በተለያዩ ጊዜያት የምርምር ስራዎች ኮንፈረንስ አዘጋጅቶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ብሩ፤ ኮንፍረንሶችንም ከጂኬን ጋር በትብብር ማዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡ በተደረገው ትብብርም ተጋባዥ መምህራን መጥተው በምርምር አሰራር ዘዴዎች ላይ ለኮሌጁ ተማሪዎች ስልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ብሩ ማብራሪያ፤ ኮሌጁ በራሱ አገር አቀፍ ኮንፍረስ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በተዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን፤ ጥናቶቹ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁኔታ፣ ባህላዊ ትምህርቶች እንዲሁም በሳይበር ጥቃት ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ጂኬን የሚያዘጋጀውን የምርምር ኮንፍረንስ ኮሌጁ በቀዳሚነት ለመምራት ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ዲኑ የጠቀሱ ሲሆን በዚህ ኮንፍረንስ ላይም የሲፒዩ ኮሌጅ መምህራን የተለያዩ ጥናቶችን እንደሚያቀርቡ ገልፀው።
እዚህ ከሚመጡት የጂኬን አባላት መካከል የተወሰኑት መምህራን እዚህ ቆይተው በኮሌጁ እንዲያስተምሩ እድል እንደሚመቻችላቸው አስረድተዋል፡፡ ሲፒዩ ኮሌጅ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን በአገሪቱ ለማስፋፋትና በዘርፉ ምሁራንን ለማፍራት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1992 መመስረቱ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011
በመርድ ክፍሉ