እኛና ሥነምግባር . . .

የሰው ልጅ መኖር እስካላቆመ ድረስ መንቀሳቀሱ ግድ ነው። እንደኔ ሀሳብ እንቅስቃሴ የሚያቆመው የሰው ልጅ እስተንፋስ ሲያቆም ብቻ ነው። ታዲያ ይህንን፣ የሕይወታችን አካል የሆነውን እንቅስቃሴያችንን ስናስብ ብዙ የመጓጓዣ አማራጮች ትዝ ይሉናል። ለዛሬ ግን ወደ አእምሮዬ የመጣው የአውቶቡስ እና የባቡር ትራንስፖርቶቻችን ሁኔታ ነው።

ዛሬም እንደተለመደው በማለዳ ተዘጋጅቼ እና ፀሎቴን አድርሼ ወደ አራት ኪሎ ለመሄድ ከቤት ወጥቻለሁ። የምነሳው ከሲኤምሲ ነው። በነገራችን ላይ አውቶቡስ ባይኖር የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ማለትም የኔ ብጤው ደሃ ምን እንደሚውጠው አላቅም። የታክሲ ሰልፉ ብዛት ከፌርማታ ፌርማታ አልፎ ሰው ሰልፍ ለመሰለፍ ብሎ ሳያውቀው አንዳንዱ ቤቱ ሳይደርስ ይቀራል ብላችሁ ነው? መልሱን ለእናንተ። ድንገት ግን በሀሳቤ ብልጭ ያለብኝ ነገር አውቶቡሶቻችን እና ባቡሮቻችን እንደዚህ የሚጭኑት ቲማቲም ቢሆን የሚል ነበር።

ሊፈጠር የሚችለውን ሁኔታ በአእምሮዬ ስስለው ፈገግ አልኩ። ወዲያው ግን “አሁንስ ያለሁበት በምን ይለያል?” ብዬ ፈገግታዬ ባንዴ ወደ ንዴት ተቀየረ። ሰው እኮ ከመጠቅጠቁ ብዛት በቦንዳ ያለ ሰልባጅ ልብስ ነው የሚመስለው። ሰልባጅ ልብስ ራሱ በቦንዳ ሆኖ “እንደኔ ፈታ አይሉም?” ብሎ የምፀት ሳቅ የሚስቅ መሰለኝ። ታዲያ በዚህ ሁኔታ እየተጓዝኩ ሳለ ድንገት ከጀርባዬ በጣም በእድሜ የደከሙ ሰው የመውደቅ ያህል ተላተሙብኝ።

በድንጋጤ ዘወር ብዬ ሳያቸው አዛውንቱ ዓይናቸው ላይ “ደክሞኛል፤ ልቀመጥ” የሚል ጥልቅ ስሜት ይነበባል። በመሀል እሳቸው ከቆሙበት ጎን ወደ ተቀመጠው ወጣት በዓይኔ አማተርኩ። እሱ የጆሮ ማዳመጫ ሰክቶ አንገቱን እየነቀነቀ በመስኮት አሻግሮ ከተማዋን እየቃኘ ነበር ዓይኔ እሱ ላይ ያረፈው። አጠገቡ እኚህ አያቱ የሚሆኑ ሰውዬ በእጅ የሚያዘውን ይዘው ቆመው መኪናው ፍሬን ያዝ ባደረገ ቁጥር ዥዋዥዌ ይመስል ወዲያ ወዲህ እያደረጋቸው የሱ ኤርፎን ሰክቶ አንገት መነቅነቅ በጣም አበሳጨኝ።

በርግጥ ወጣት የሆነ ሁሉ ቦታ ለቆ ቆሞ ይሂድ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ወጣትም ሆኖ ብዙ የጤና ችግር ያለበት ሰው ይኖራልና። ነገር ግን ዘወር ዘወር ብዬ ሳይ ከወጣቱ በተጨማሪ በርካታ ወንበር ይዘው የተቀመጡ፤ በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ተመለከትኩ። አንዳቸውም እንኳን ተጠግተው እኚህን አዛውንት ለማስቀመጥ አለማሰባቸው አስገረመኝ።

“እኛ ኢትዮጵያውያን እንረዳዳለን፤ እንከባበራለን የሚለው ትምህርታችን እንደዚህ ዓይነት ቦታ ላይ አይሰራም ይሆን?” ስልም አሰብኩ። “ነው ወይስ፣ የተማርነው የሥነ ዜጋም ሆነ የሥነ ምግባር ትምህርት ህሊናችን ካላዘዘን ግዴታ የለብንም ማለት ነው?” የሚለውን አስቦ ይሆን? ይህ ካልሆነ ደግሞ የኛ ትውልድ “እናት እና አባትህን፤ እንዲሁም፣ ታላቅህን አክብር” የሚለውን ገልብጦ ማንበብ ጀምሯል ማለት ነው?

አንዳንዴ ደግሞ በተቃራኒው መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ወጣቶች ለታላላቆቻቸው ቦታ ሲለቁ “ዞር በል ከዚህ ልትዘርፈኝ ነው?” የሚሉና ለአክብሮት ምላሻቸው ቁጣ የሆነ ታላላቆች ይኖራሉ። ምናልባትም ይህ እየተባባሰ የመጣው የስርቆት ወንጀል የፈጠረባቸው ስጋት ነው ብዬ አስባለሁ። በርግጥ ታላቅን ማክበሩ በግለሰቡ መልካም ፈቃድ ላይ የሚመሰረት እና ቢደረግ መልካም የሚሆን ጉዳይ ቢሆንም፤ አንዳንዴ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ የሚታዩ እጅግ አስነዋሪ ድርጊቶችም አሉ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ከገጠሙኝ መሀል በቦታ ጥበት የሚፈጠረውን መጨናነቅ እና ግፊያ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሴት እህቶቻቸው ላይም ፆታዊ ትንኮሳ የሚፈፅሙ ህሊና ቢስ ግለሰቦችን መመልከትም የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

አንዳንዴ እንደውም ለዚሁ አላማ የገቡ በሚመስል መልኩ ይህንን አፀያፊ ተግባር የለምንም ይሉኝታ የሚፈፅሙ ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። በእርግጥ የኛ ማህበረሰብ እና ያደግንበት ባህል በይሉኝታ የታጠረ በመሆኑ እንዲህ አይነት አጸያፊ ተግባራትን ለመቃወም አቅም የለውም። የጥቃቱ ሰለባዎችም ቢሆኑ የደረሰባቸውን መናገሩ ሊያደርስባቸው የሚችለውን የህብረተሰብ ምላሽ በመፍራት ነገሩን ለራሳቸው መያዝን ይመርጣሉ። ይህ ደግሞ ለድርጊቱ ፈፃሚዎች ይበልጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በእነዚህ መጓጓዣዎች ውስጥ በየቀኑ እየተዘረፈ ወደ ቤቱ የሚገባውንማ ቤት ይቁጠረው። አንዳንዴ እንደውም በትራንስፖርት ውስጥ እየገቡ የሰውን ኪስ ማውለቅን እንደ መተዳደሪያ ሥራ የሚገለገሉበት ግለሰቦች ያሉ ይመስላል። ለነገሩ በእነዚህ መጓጓዣዎች ውስጥ ያለው መጨናነቅ እና ግፊያ ስርቆትን መተዳደሪያቸው ላደረጉ ግለሰቦች ምቹ የሥራ አካባቢ እንደሚፈጥር ግልፅ ነው። በዚህ ምክንያት የትኛውም ተሳፋሪ ከአውቶቡስ ወይም ከባቡር እንደወረደ የመጀመሪያ ተግባሩ ኪሱንና ቦርሳውን መፈተሽ እንደሚሆን መጠራጠር አይቻልም።

የሆነው ሆነና የሕዝብ መጓጓዣዎቻችን የብዙ ሰዎችን ጊዜና ገንዘብ የመቆጠባቸውን ያህል፤ በእነዚሁ ትራንስፖርቶች ውስጥ ግብረ ገብነታችን እና ሞራላችን ምን ያህል እንደወረደ የሚያሳዩ በርካታ አስነዋሪ ተግባራት ይፈፀማሉ። በርግጥ ይህ ማለት ሌሎች እንደ ሚኒባስ ታክሲ ያሉ መጓጓዣዎች ከችግር የፀዱ ናቸው ማለት አይደለም። ችግር ያለባቸው ብዙ ናቸው። ለየት የሚለው፣ በባቡር እና አውቶቡስ ትራንስፖርቶች ላይ ያለው የተጠቃሚ ብዛት እና መጨናነቅ ችግሩ እንዲጎላ ማድረጉ ብቻ ነው።

ለኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሀገርን ሀገር አድርጎ የሚያቆማት ከምንም እና ከማንም በፊት በሕዝቦቿ መካከል ያለው መስተጋብር ነው። ተራራ፣ ወንዝ፣ ሸለቆ ውበት እንጂ ሕመምህን፣ ቁስልን አይካፈልም። ታዲያ እንደዚህ በጋራ ሊያገናኙን በሚችሉ እና የጋራ መገልገያዎቻችን በሆኑ ቦታዎች ላይ አንዳችን የሌላችንን ችግር እና ሕመም ከመካፈል እና ከማቅለል ይልቅ ጭራሹን የችግሩ እና የሕመሙ ምክንያት የሆነው ለምን ይሆን?

 እየሩሳሌም ምትኩ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *