አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሚኒባስ ታክሲዎች ያለአግባብ ታሪፍ ስለሚጨምሩ ተገልጋዮች እየተጎዱና ህገወጥነት እየተንሰራፋ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የታክሲ ትራንስፖርት ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ሰለሞን የማታው ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገረው፤ በስራ ምክንያት ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ፤ ከቦሌ ወደ አራት ኪሎ በቋሚነት ሲመላለስ ለአንድ ጉዞ አምስት ብር መክፈል ሲገባው 10 ብር እየከፈለ ለመጓዝ ተገድዷል፡፡ የታክሲ ስምሪት ተቆጣጣሪዎች ባሉበት ስፍራ ታክሲው መቀመጫ መያዝ ከሚችለው በላይ ተጨማሪ ሰው የመጫን ህገወጥ ተግባር እንደሚፈፀም፤ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ሰአት ከስራ ውጭ በመሆን ሆን ብለው ሰው ሲበዛ ጠብቀው አስር ብር ሲያስከፍሉ ህግ ለማስከበር የሚሞክር ተቆጣጣሪ አለመኖሩ፤ ሸገር አውቶቡስና አንበሳ አውቶቡስ ለአገልግሎት የሚሰማሩበት ሰዓት አመቺ ያለመሆኑ ህብረተሰቡን ለእንግልት እንደዳረገው ወጣት ሰለሞን ይናገራል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ እፀገነት አበበ ችግሩ እንዳለ ይታወቃ። እስካሁን ባለው ሂደት ከታሪፍ በላይ የሆነ ህገ-ወጥ ክፍያ የሚፈፀምባቸው 78 መስመሮች ተለይተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ስድስት መስመሮች ተለይተው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ተደርጓል። ችግሮቹም ባብዛኛው የሚስተዋሉት በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) አካባቢ በመሆኑ መፍትሄ ለመስጠት ጥናት እየተደረገ በመሆኑ በቅርቡ መፍትሄ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ እፀገነት ገለፃ፤ ህዝቡ ዝም ብሎ መክፈል የለበትም።
መብቱን መጠየቅና ማስከበር አለበት። በ888 ነፃ የስልክ መስመር ቢያሳውቅ እርምጃ ይወሰዳል። በተለይ ታፔላውን፣ ኮዱን፣ ታርጋውንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን ፅፎ ቢያሳውቅ ጥሩ ነው። ተርሚናል አካባቢ ላሉ አስተባባሪዎች ማሳወቅም ይችላል፡፡ ይህ ቶሎ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል። ይህን ሁሉ ችግር ለመፍታት መመሪያ እየተዘጋጀ ሲሆን፤ ፀድቆ ስራ ላይ ሲውል ችግሩን ይፈታዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የታክሲ ተቆጣጣሪዎች ግንኙነታቸው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ሳይሆን ከአነስተኛና ጥቃቅን ኤጀንሲ ጋር ቢሆንም ስራው በመመካከር እንደሚከናወን ገልፀው፤ ህብረተሰቡ የብዙሃን ትራንስፖትርን ማለትም ሀይገር፣ ሸገርና የከተማ ኦውቶቡስን የመሳሰሉትን መጠቀም እንደሚገባው፤ የእነሱን አገልግሎት ለማስፋፋትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ እፀገነት አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ መስተዳድር ትራንስፖርት ቢሮ በተወሰነውና ስራ ላይ በዋለው አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ መሰረት ሚኒባስ ታክሲዎች እስከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት 1 ብር ከ50 ሳንቲም፤ ከ2 ነጥብ 6 እስከ 5 ኪሎ ሜትር 3 ብር፤ ከ5 ነጥብ 1 እስከ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ደግሞ 4 ብር ከ50 ሳንቲም ነው እንዲከፍሉ መመሪያ መውጣቱ የታወሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011
በግርማ መንግሥቴ