አዲስ አበባ፡- በያዝነው ዓመት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ እንደገለፁት፤ በዚህ ዓመት አሳሳቢና መንግስትም መፍትሄ ለማምጣት ሌት ተቀን እየሰራ የሚገኘው በብዙ ክልሎች ብሔርን መሰረት አድርገው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት በተፈናቀሉ ዜጎች ላይ ነው፡፡ ብዙ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ብዙ ችግርም ደርሶባቸዋል፡፡ እንደምክትል ዋና ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ ብዙ ዜጎች ስራቸውን ትተው፤ ብዙ ወጣቶች ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠው በመጠለያ በመቆየታቸው ብዙ ሰርተው ማግኘትና ሀገርንም መጥቀም ሲችሉ ተመፅዋች ሆነዋል፡፡
መንግስትም በተጠለሉባቸው አካባቢዎች የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። መንግስት ብዙ ጥረት ቢያደርግም በመጠለያና በማረሚያ ቤት ባሉ ዜጎች ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደሚደርሱባቸው ተናግረዋል፡፡ ”በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የመፈናቀል ችግር ለመፍታት መንግስት ቆርጦ ተነስቷል” ያሉት አቶ እሸት ዜጎችን በማፈናቀል ብዙ ችግር ያደረሱ አካላትን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ ቆራጥ ውሳኔ ወስኖ ተፈናቅለው ቀያቸውን የለቀቁ ዜጎች ወደ ቦታቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሮ እንዲጀምሩ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ነው ብለዋል፡፡ ተፈናቅለው በመጠለያ ካሉ ዜጎች ባሻገር በማረሚያ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎች የታራሚዎችን አያያዝ በተመለከተ በአራት ክልሎች ወደ 40 የሚጠጉ ማረሚያ ቤቶች ላይ በተደረገው ክትትል ከባለፈው ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር ብዙ ለውጥ እንዳለው ጠቅሰው ይሁን እንጂ አሁንም በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በርካታ ችግሮችም መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
በደቡብ ክልል በማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩን የተናገሩት አቶ እሸት ታራሚን መደብደብ፣ ማሰቃየትና የሰውን ክብር የሚነኩ ተግባራት በስፋት እንደሚፈፀም አስታውቀዋል፡፡ የፖሊስ ጣቢያዎችን አያያዝ በተመለከተ መንግስት ለማሻሻል ባደረገው ሙከራ ብዙ ለውጦች መጥተዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያዎች የበጀትና የተሸከርካሪ ችግር በስፋት ስለሚስተዋልባቸው በፖሊስ ተጠርጥረው በፖሊስ ጣቢያ ያሉ ዜጎች በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳልተቻለም ተናግረዋል፡፡ ”
ማረሚያ ቤት ሰው የሚታረምበት፣ ብዙ ሙያ የሚያዳብርበትና ሲወጣ ጥሩ ዜጋ ሆኖ አገሩን የሚያገልግልበት ቦታ ነው እንጅ ክብሩና አካሉ የሚጎልበት ቦታ መሆን የለበትም” ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሩ ማረሚያ ቤቶች የታሰበላቸውን ሆነው እንዲገኙም መንግስት በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታራሚዎች እንደ ማንኛውም ዜጋ ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው መሰረታዊ ፍላጐት ተሟልቶ እንዲኖሩ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011
በሞገስ ፀጋዬ
ፎቶ፡- ፀሀይ ንጉሴ
Do you take Suboxone and Tamoxifen citrate buy priligy paypal Clifton ZvmKEVzKXRzEcufg 6 16 2022