“ከወቅቱ አኳያ ተልዕኮን በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ፤ አዳዲስ አደረጃጀቶችን እየፈጠርን ነው”ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ ዘመናዊ ፖሊስ ማደራጀት ከተጀመረ አራት ዓመት በኋላ ከ1939 ዓ.ም የተቋቋመ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ ነው። የመጀመሪያ መቀመጫው አዲስ አበባ ከተማ አባዲና አካባቢ ነበር። በ1967 ዓ.ም ደግሞ አሁን ወደሚገኝበት ሰንዳፋ ተዘዋወረ። በ2007 ዓ.ም ከኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አደገ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ሆኗል።

ተቋሙ በሰርተፍኬት፣ ዲፕሎማ እና የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተማሪዎችን እያሰለጠነ ሲሆን፤ ሦስተኛ ዲግሪም ሊጀምር ነው። በዛሬው ዕትማችን ተቋሙ ከአገሪቱ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ምን እየሰራ ነው? ስንል ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ጋር ዘለግ ያለ ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ከሪፎሩሙ ወዲህ ምን የተለየ ኃላፊነቶች ተሰጡት ? ምን እየሠራስ ነው?

ኮሚሽነር መስፍን፡- በፖሊስ ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ተቋሙ ውስጥ ፖሊስ ተኮር የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት መስጠት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን፤ በፀጥታና ደህንነት ላይና በፖሊስ ሙያ ዙሪያ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥናቶች በማድረግ ለፀጥታ ዘርፉም ሆነ ለባለድርሻ አካላት የጥናት ውጤቶችን መሰረት በማድረግ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት መስጠት የመሳሰሉትን ይሰራል።

ከሪፎርም ወዲህ ሁሉም የፖሊስ ትምህርት ሥልጠና ጥናት ምርምር ማዕከል በአንድ ማዕከል ተደራጅተው እንዲመሩ በተወሰነው መሠረት ከዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ በተጨማሪ ሁሉም የሥልጠና አውዶች ከምልምል ፖሊስ ጀምሮ በየደረጃው የሚደረጉ የማዕረግ ሽግግር ሥልጠናዎች፤ የተለያዩ የፖሊስ ተዛማጅ ሙያዎች አጫጭርና ረጃጅም ሥልጠናዎች በሙሉ በእኛ ስር የሚመሩ ናቸው። ከሪፎርም ወደዚህ የሥልጠና ፍላጎቶች የፖሊስ አገልግሎትን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። የፖሊስ አገልግሎት ደግሞ በፖሊስ ዶክትሪን የሚመራ ነው። ይህ ደግሞ የፖሊስን ምንነት፣ አደረጃጀት፣ አሠራር፣ ሥነ ምግባር፣ እሴትና የመሳሰሉትን የያዘ ነው።

አንድ ፖሊስ ከተመደበበት ቦታና የሥራ ዘርፍ ወይም አመራርነት ዘርፍ ላይ ሊኖረው የሚገባው ቅርጽ፣ የሥራ ባህሪ፣ የአገልግሎት ባህሪ በደንብ የሚቃኝበት ዶክትሪን ነው። ይህንን በደንብ አሳድገነዋል። ፖሊስ ተኮር ግልጽ መስፈርቶችንም አስቀምጠናል። በዚህ ዶክትሪንና መስፈርት መሠረት የሚመራ ነው። ስለዚህ ያስቀመጥናቸው ነገሮች የፖሊስ አገልግሎት በፖሊስ ዶክትሪን የሚመራና የሚመለስ መሆኑንም ማረጋገጥ ነው።

ሌላው እኛ የተዋቀርንበት አዋጅ አለ። በዚህም መሠረት የፖሊስ ኃይል በፌደራል እና በክልል ይደራጃል። የህዝቡንና የአገርን ጥቅምና ደህንነት ያስከብራል። የዜጎች መብትና ጥበቃና ከለላ የሚደረግለት ሲሆን፤ የዜጎች መብት እንዳይገፋም ይሰራል። ይህን መሠረት አድርገን የፖሊስ ተቋማትና የሰው ሃይልም በዚህ ደረጃ ብቃት እንዲኖረውና የሚፈለገው እንዲረጋግጥ ሥልጠና ይሰጣል። በዚህም ከታች ጀምሮ እስከ ላይኛው እርከን ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። ልዩ ክህሎት ወይም ሥልጠና የሚፈልጉም አሉ። እነዚህ ሥልጠናዎችም በረጅም፤ መካከለኛና ረጅም ጊዜ የትምህርት ሥርዓት ተካተው የሚሰጡ ናቸው። ይህም ከሰርተፍኬት ጀምሮ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጡ ናቸው። በዚህ አግባብ ራሳችንን አደራጅተናል። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው በዲፕሎማ በዋናነት ደግሞ በዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን፤ በቀጣይ በዶክትሬት ለማሠልጠን የሚያስችል ቁመና ላይ ነው።

ለፖሊስ ሙያ አስፈላጊ ናቸው በምንላቸው ሙያዎች ላይ ኮሌጆችን እያደራጀን ነው። ኮልፌ ላይ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እያደራጀን ነው። አዋሽ ላይ የወንጀል መካላከልና ሙያዎችና የወንጀል መከላከል የአመራር ሥልጠና የምንሰጥበት ኢንስቲትዩት አለ። እነዚህ ከዲግሪ በታች ያሉትን የሙያ ክህሎት ለማስጨበጥ ሥልጠና የምንሰጥባቸው ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ ሪፎረም ቢደረግም ግጭቶች አልፎ አልፎ ይታያሉ። ይህ ከፖሊስ ተልዕኮ መፈፀም፣ አደረጃጀትና መዘመን ጋር ጥያቄ ውስጥ አይገባም?

ኮሚሽነር መስፍን፡– አገራችን አጋጥሟት ከነበረው ሁኔታ አኳያ ትኩረቱ ጦርነት ማርገብ ላይ ነበር። በየቦታው ሕግን የመተላለፍ፤ ጥፋትን የመፈፀምና ዜጎችን ማሸበር ላይ የተሰማሩትን መከታተል ላይ ከሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመናበብ እየተሠራ ነው። ከዚህ አኳያ የፖሊስ ኃይላችን በክልልም ይሁን በፌዴራል ደረጃ ትኩረት ማድረግ የሚገባንን አደረጃጀት በመለየት፤ የክልል እና የፌዴራል ፖሊስ ምን ማሟላትና ምን ላይ ማተኮር አለበት? በሚለው ላይ በኮሚሽነሮች የጋራ ጉባዔ ግልፅ አሠራር አስቀምጠናል።

በዚህም የፌዴራል ፖሊስን እያደራጀን ነው። ክልሎችም በራሳቸው መንገድ እየተደራጁ ነው። ቀድሞ በክልሎች የነበረው የክልል ልዩ ኃይል ተልዕኮ ከሕግም ከአሰራርም አኳያ ልዩ ኃይል የሚባለው አደረጃጀት በመደበኛ ፖሊስ ኃይል ውስጥ መኖር ስለሌበት ወደ መደበኛ አደረጃጀት እንዲገባ ተደርጓል። ከዚህ ውጭ ያለው ደግሞ በመደበኛ ፖሊስ፣ የከተማ አድማ ፖሊስ በታኝና ኮሚዩኒቲ ፖሊስ በክልሎችና ከተሞች ነባራዊ ሁኔታ እንዲደራጁ ተደርጓል። ቀደም ሲል በልዩ ኃይል ሲሰራ የነበረውን በፌዴራል ፖሊስ መሠራት ያለበት በመሆኑ፤ የፖሊስ ኃይላችን ፈጥኖ ደራሽና የፀረ ሽብር ብቃት እንዲኖረው በደንብ ተጠንቶ በፌዴራል ፖሊስ እንዲተካ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የነበረው ልዩ ኃይሎች የሚሸፍኑት ተልዕኮ አሁንም በምን ተሸፈነ?

ኮሚሽነር መስፍን፡– ቀደም ሲል በክልል ልዩ ኃይሎች ይሸፈን የነበረው ተልዕኮ እና የፀጥታ ማስከበር ሚና በአሁኑ ወቅት በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንዲሸፈን ተደርጓል። የፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በመላ አገሪቱ ስምሪት የተሰጠው መሆኑም ይታወቃል። በመሆኑም ስምሪቱ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፌዴራል ፖሊስ ተተክቷል።

በአሁኑ ወቅት በተሰጠው ተልዕኮም ሆነ የሚሸፍነው ቦታ ቀደም ብሎ ከነበረው በብዙ እጥፍ አድጓል። ይሁንና በመላ አገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ሥምሪቱ እስሚጠናቀቅ ድረስ የአገር መከላከያ ሠራዊት የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ሽፋን እየሰጠ ነው። በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ በፌዴራል ፖሊስ የሚተካ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የፖሊስ አደረጃጀት ሪፎርም ተደርጎ ከሆነ ለምን ግጭቶች ተበራከቱ?

ኮሚሽነር መስፍን፡– አገራዊ ሁኔታ የፈጠረው ነገር አለ። ማህበረሰቡ ላይ የሚፈጠሩና በተለያዩ ወቅቶች የተፈጠሩት ችግሮች በወቅቱ አለመፈታታቸው በራሳቸው የሚፈጥረው ቅሬታ አለ። በዚህ መሃል ደግሞ ችግሩን የሚፈጥሩ ኃይላት አሉ። ለውጡን የወለደውም አንዱ የማህበረሰቡን ጥያቄ አዳምጦ በአግባቡ አለመመለስ ነው። የህዝብ አመጽም ተፈጥሯል። ይህ ለውጥ ሲደረግ፤ በሌላ ጎኑ በለውጡ ተጎጂ የሚሆን አለ። በዚህ ወቅት ለውጡ የማይዋጥላቸውና ከለውጡ በተፃራሪ የሚቆሙ አሉ። እስከ ጦርነት የደረሱና አገር እስከ ማፍረስ የዳዳቸው ሃይላት አሉ። እነዚህ አካላት እነርሱን የሚያግዙ አካላትንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መደራጀታቸው ይታወቃል። አሁንም በአማራ፣ ኦሮሚያ እና አንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የምናያቸው የጥፋት ሃይላት የልብ ልብ አግኝተዋል።

በአሁኑ ወቅት በተግባር የሚታየውም ይህ ነው። ሽብር እየፈጸሙ ነው። ይህ በአገሪቱ የፀጥታ ካውንስልም ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ፤ ከሥር መሠረቱ ለማጥፋት እየተሠራ ነው። በዚህ ላይ የክልል ፀጥታ ኃይሎች፣ፌዴራል ፖሊስ እና የአገር መከላከያ ሠራዊትም ሰፊ ሥምሪት ወስደው እየሰሩ ናቸው። አጥፊዎችም የሚያደርሱትን እያየን አይደለም፤ እየተቆጣጠርንና እየደመሰስናቸው ነው። ሆኖም በአንድ ጊዜ አይጠፉም፤ የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል። በተቻለ መጠን ጥፋትን በሚቀንስ መጠን እነዚህን አካላት ለማምከን የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በእኛ እምነት ይህ ትርምስ ጊዜያዊ ነው፤ ይጠፋል። እነዚህን የሽብር ሃይሎችን በመከላከል ነገ በምንፈጥረው ጠንካራ ሰላም የልማትና ዕድገት መሠረት መጣል እንችላለን። በዚህ ሂደት ውስጥ ጠንካራ የፖሊስ ሃይል እያበጀን የምንሄድ ሲሆን፤ የአገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እቅስቃሴ ብሎም ዋስትና ያለው ሠላምና ጠንካራ ሥርዓት ይፈጠራል።

አዲስ ዘመን፡- ፈተናዎችን ህዝቡ እንዲገነዘበውና እንዲተባበር ብሎም ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ እንዲሰጥ በቂ ሥራ ተሰርቷል ብለው ያምናሉ ?

ኮሚሽነር መስፍን፡- ህዝብና ፖሊስ ይናበባል። ህዝቡ በፖሊስ ላይ እምነት አለው። ከጥንት ጀምሮ ከማንም በላይ ፖሊስን ያምናል። አሁን አሳሳች የሆነው እነዚህ የጥፋት ሃይሎች በስስ መንገዶች ገብተው የሚጥሉት አደጋ ተበትኖ ለሚኖረው ህዝብ በራስ መተማመንን ይከለክለዋል። በተለያዩ ቦታዎች አጋጣሚዎችን በመጠቀም አደጋ ያደርሳሉ። ገጠር እና ትንንሽ መንደሮች ደግሞ የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ሁሉንም ቦታዎች ደግሞ በጸጥታ ሃይሎች የማይጠበቅበት አጋጣሚ ይኖራል። አጥፊ ኃይሎች ደግሞ የሚጠቀሙት ህዝብን በደንብ ያስደነግጣል ወይንም ይጎዳል ብለው የሚያስቡት ቦታ ላይ ጥቃት በማድረስ ሌላውን ለማስፈራራት ያስባሉ። ለአብነት ገጠር ውስጥ አምራች የሆነውን እና በግብርና ተምሳሌት የሆነው አርሶ አደር ሄደው ይጎዳሉ፤ የከመረው ምርት ላይ ጭምር ሳይቀር ጉዳት ያደርሳሉ።

ያደለበውን ከብት ይወስዳሉ፤ ከቤተሰቡ አንድ አባል ይወስዱና በሚያመው መንገድ ገንዘብ እንዲከፍል ያደርጋሉ፣ በአሳቻ ሰዓት መንደር ወርረው ጉዳት አድርሰው ይሰወራሉ። ይህ ሰው እንዲሰጋ ያደርገዋል። ይህ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ እንዳይከላከል ሊያደርገው ይችላል። የእኛ ትኩረት የነበረው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ስለነበር፤ የተወሰኑ ክፍተቶችን በመጠቀም ችግሮችን ሊፈጥሩ ችለዋል። አሁን ግን መፍትሄ ያገኛል።

አዲስ ዘመን፡- የአጥፊ ኃይሎች ሁኔታ በዚህ ደረጃ ከታወቀ፤ ፖሊስ ቴክኖሎጂን ጭምር በመጠቀም ለምን ማክሸፍ አልቻለም ?

ኮሚሽነር መስፍን፡- ችግሮችን ችግሮች ናቸው ብለን አንተዋቸውም። መሰል ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ልናጠፋቸው ይገባል የሚል ሥርዓት እንተክላለን። እየገነባን ያለውም ይህንኑ ሥርዓት ነው። እንደአገር እየተደረገ ያለው ይህ ነው። በቅርቡ በተደረጉ ኦፕሬሽኖችም ጥሩ ውጤቶች እየተገኙ ናቸው። ይህን በብቃት መከላከል የሚያስችል የውስጥ አደረጃጀት፤ ግንባታ ብሎም የሰው ኃይል ሥምሪት የመስጠት ሥራ ላይ ነን። ከወቅቱ አኳያ ተልዕኮን በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ አዳዲስ አደረጃጀቶችን እየፈጠርን ነው ። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የፈጥኖ ደራሽ ስምሪት ማዕከሎችን በስፋት በማስፋፋት ላይ ነን። ቀደም ሲል አራት ቦታዎች ብቻ የነበረው ከእጥፍ በላይ አድጎ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በውስን የቆዳ ስፋት ስምሪት እንዲወስዱ የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥረናል።

በከተሞች ሊኖሩ የሚችሉ የጥፋት ኃይሎችን መከላከል የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን ፈጥረናል። በማዕከል የሚፈለገውንና የፖሊስ ተልዕኮ መወጣት የሚችሉ አደረጃጀቶችን ፈጥረን ወደ ሥራ ገብተናል። በግብዓት ደረጃ በተለይም በመሳሪያ፣ ቴክኖሎጂ፣ ማሽነሪ ግብዓት በብዙ እጥፍ የተለወጠ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁና ትልቅ አገራት ጭምር የሚጠቀሙባቸውን ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሙ፤ ከፖሊስ ተልዕኮ ጋር የሚሄዱ ዘመናዊ መሣሪዎችን በመጠቀም ሥራችንን እያሰፋንና እያደረጀን ነው። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማን ከማዕከል ሆኖ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር፣ መከታተል፣ መምራትና መረጃ ወዲያው ማግኘት የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥረናል።

በግብዓትም ለአድማ ብተና፣ ወንጀል መከላከል፣ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችና ሌሎችም የሚጠቅሙትን አሟልተን ለፖሊስ ኃይላችን አከፋፍለን አሰማርተናል። ይህን የሚያከናውነው የሰው ኃይላችን በሥልጠና በተከታታይ የማብቃት ሥራዎችን ሠርተናል፤ በመሥራትም ላይ እንገኛለን። ነባሩን ኃይል በሥራ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ሥልጠና እንሰጣለን፤ አዳዲስ ኃይል በማሠልጠን ክፍቶችን እንሞላለን፤ ይህ በውስጥ የምንሰራው ሥራ ነው። ከውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር ደግሞ ለእኛ የፀጥታ ሥራ አስፈላጊ ከሆኑት ጋር ሰፊ ግንኙነቶችን በማድረግና በማጠናከር በጋራ እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ካላት ቀጣናዊ ሁኔታ እና ሥጋቶች አኳያ በአገር ውስጥ ካሉ የደህንነት ተቋማት ጋር ያለው መናበብ እንዴት ይገለፃል ?

ኮሚሽነር መስፍን፡- አሁን ላይ የብሄራዊ ፀጥታ አካላት አስተባባሪ ግብረ ኃይል አለ። ይህ ግብረ ኃይል የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ኢንሳ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና አዲስ አበባ ፖሊስ ብሎም እንደ ስምሪት ሁኔታም የክልል ፖሊሶችን ያካተተ ነው። ይህ ከሪፎርም ወዲህ የተከናወነ ነው። ቀደም ሲል አለመናበብ ወይንም ደግሞ ውድድር ዓይነት ባህሪ ነበር። አሁን ግን በሚገርም ሁኔታ እንደ አንድ ማዕከል ወይንም ተቋም ሆነው በጋራ ተደራጅተው አንዱ ለሌላው መረጃ እየተመጋገቡ በጋራ እየሰሩ ነው።

ለተልዕኮቻችን እንደ አስፈላጊነቱ በመደጋገፍ እየተሰራ ነው። ይህ ቀድሞ ከነበረው በተለየ ሁኔታ ተቀናጅተው በመስራታቸው ለውጥ የመጣበት ነው። ይህም በመሠራቱ አገሪቱ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች። በርካታ የአገሪቱን ፀጥታ የሚያደፈርሱ አካላት እያሉ አልፎም አልፎ ችግሮች ቢኖሩም፤ አገር በተረጋጋ ሁኔታ መሄድ መቻሏ በብሄራዊ ፀጥታ አካላት አስተባባሪ ግብረ ኃይል ሥምሪትና ቅንጅት በብልሃትና በሥርዓት ተልዕኮ መወጣት በመቻሉ ነው። ስለዚህ አሁን የሚታይ ለውጥ ባለው መደጋገፍ የመጣ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ፌዴራል ፖሊስ ከአገራዊ ሁኔታ በመነሳት ምን ምን ስጋቶች አሉ? ምን መሆንስ ይኖርበታል?

ኮሚሽነር መስፍን፡– ሥጋቶች የተልዕኮ የቀጣይ እቅድና ሥምሪት አካል ናቸው። ወደ ስምሪት ስንሄድ ስምሪታችን ምንድን ነው ተብሎ ይታሰባል። በመሆኑም ለተልዕኳችንና ስምሪታችን ዝግጁነትን መፍጠር ነው። ወደ ስምሪት ስንሄድ የሚኖሩ ስጋቶች ይተነተናሉ። ምርመራ ሲታቀድ ምን ዓይነት ወንጀሎች ይፈፃማል ተብሎ ይታሰባል። አሁን ያለው ወንጀል ምንድን ነው? በቀጣይስ ምን ይሆናል? እያደገ የመሄድ አዝማሚያስ የትኛው ጉዳይ ነው? ተብሎ ይተነተናል። ከጉዳት አንፃርም በጥልቀት ይመረመራል፤ ይተነተናል። ይህም በእቅድ ቅድሚያ በመስጠት የመከላከል ሥራው ይሰራል።

አሁን በውስጣዊ ሁኔታ በግልጽ የሚታየው በየክልሉ የተደራጁና እያጎጠጎጡ ያሉ የጥፋት ኃይሎች አሉ። ተደራጅተውና ከሕግ አፈንግጠው ወንጀል የሚፈጽሙና ራሳቸው ከሕግና ሥርዓት በላይ የሚመለከቱ አሉ። ትጥቅ በመታጠቅና ለሕግ ተገዥ ያልሆኑ በህዝብ ላይ አደጋ የሚያደርሱ ኃይሎች በወንጀል መከላከል ሥራችን በትኩረት የምንሰራበት ነው።

አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ግጭቶች አሉ። በተደራጁ አካሄዶች በተለይም በከተሞች አካባቢ የተደራጁ ዝርፊያዎች፣ ሰው መግደልና ማገት፣ መኪና፣ ቤት እና ንብረቶችን መዝረፍና በተደራጀ መንገድ የሚከናወኑ ወንጀሎች አሉ። እነዚህ እያደጉ በመምጣታቸው በጉዳዮቹ ላይ ትኩረት ይሰጣል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርም እያደገ የመጣ ጉዳይ ነው። አደገኛ ዕፅዋት ዝውውርም እያደገ በመሆኑ አሳሳቢ ነው። መሬት ወረራ እና የፋይናንስ ወንጀል፤ በተለይም ኤሌክትሮኒክስና ቴክኖሎጂ ተኮር ወንጀሎች እየተበራከቱ የመሄድ አዝማሚያዎች እየታዩ ናቸው።

በመሆኑም ቴክኖሎጂን ለኢኮኖሚ የምንጠቀመውን ያህል፤ ቴክኖሎጂ የሚወልዳቸውና ለወንጀለኞች መጠቀሚያ የሚሆኑ ዕድሎች አሉ። ብዙ ጊዜ የግለሰቦች አካውንት በመስበር፤ በማጭበርበር የመሳሰሉት ወንጀሎች እየተደረጉ ናቸው። ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ የገበያ ሥርዓትን ማዛባትና ማናጋት፤ ሰው ሰራሽ የገበያ ውድነት፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ መገደብና የተደራጁ ወንጀለኞች የመሳሰሉ እየታዩ ነው። ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወደ ወንጀል እየገቡ መሆኑን ያሳያል። እነዚህና የመሳሰሉት እያደጉ የመጡ በመሆናቸው ፖሊስ እነዚህን የሚከላከልበት አግባብ እየፈጠረ እንደሚሄድ ይታየኛል። እኛም እንደ ሥልጠና እና ጥናት ተቋም በዚህ ላይ መሥራት እንዳለብን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡- ድንበር ተሻጋሪ ከሆኑ ወንጀሎች አኳያስ ምን እየተከናወነ ነው ?

ኮሚሽነር መስፍን፡- ድንበር ዘለል የሆኑና በተደራጀ መንገድ የሚከናወኑ ብዙ የወንጀል ዓይነቶች አሉ። ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ አደገኛ ዕጽ ዝውውር፣ ኮንትሮባንዶች፣ ሕገ ወጥ የማዕድን ዝውውር፣ የእንስሳት ዝርፊያ፣ ደረጃ ያልጠበቁ መድኃኒቶችና ምግቦች፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና የመሳሰሉትን የያዘ ነው። የእነዚህን ወንጀሎች ባህሪ ትልቅ አደረጃጀትና ዓለም አቀፍ ባህሪ ያለው ነው። በዓለም አቀፍ የሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ትልልቆቹ አትራፊዎቹ ያሉበት ነው። ስለዚህ በዚህ ውስጥ በጣም የተደራጀ ሴል ያለበትና ውስብስብ ነው። መሰል ጉዳዮች ላይ በአንድ ከተማ ወይም አገር ታጥሮ የሚሰራ ሥራ አይደለም። ስለዚህ ከሌሎች አገራትና ተቋማት ጋር በሚገባ ተቀናጅቶ መሥራትን ይጠይቃል።

ዓለም አቀፍ ፖሊስ ማህበር (ኢንተር ፖል)፣ በየቀጣናው የሚገኙ የኢንተር ፖል ቅርንጫፎች ጋር መሥራት ይገባል። እኛም አስራ አራት አገራትን ያቀፈው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ማህበር አባል ነን። የእነዚህ ማህበራት ዋነኛ ተልዕኮ ድንበር ዘለልና የተደራጁ ወንጀሎችን መከላከል ነው። በመሆኑም በጋራ እንነጋገራለን፣ እንወያያለን፣ በጋራ እንወስናለን። የጋራ ኦፕሬሽኖችን እናከናውናለን፤ ወንጀለኞችን እንለዋወጣለን። በጋራ ወንጀለኞችን የመከታተልና የመከላከል ሥራዎችን እናከናውናለን። በዚህም ትልቅ ውጤት እየተመዘገበ ነው። ከአውሮፓና ከአረብ አገራትም እንዲሁ ትልቅ ትብብር እናደርጋለን።

ወደ አውሮፓ የሚደረግ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎችን ላይ ትልቅ ወንጀል ከሚፈፀምባቸው ክስተቶች አንዱ ነው። ይህ ከሥሩ ጀምሮ ረጅም መንገድ በመሆኑ ከመነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ከሆኑ አገራት ጋርም በጋራ ቅንጅታዊ ሥራዎችን እናከናውናለን። እነዚህን ለመከላከል ብዙ አደረጃጀቶች አሉ። በተመሳሳይም በእነዚህ አደረጃጀቶች የጋራ ሥራ እንዳለ ሁሉ ሥልጠናዎችንና ድጋፎችንም የማግኘት አግባብ አለ።

አዲስ ዘመን፡- የሰው ኃይል ከማዘመን ጎን ለጎን ተቋሙን ለማዘመን የሚሰራው ሥራስ ምን ይመስላል?

ኮሚሽር መስፍን፡- ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራትም በአንክሮ እየተሠራ ነው። በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ባለሙያዎችን እያሠለጠነ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ተልዕኮዎችን ለመፈፀም የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች እየተሟሉ ናቸው። የምርመራ እና ፎረንሲክ ኢንስቲትዩት ግንባታ እንዲከናወን በመፈቀዱ በአሁኑ ወቅት ሥራው 36 ከመቶ ደርሷል፤ ለግንባታም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ተበጅቷል። በዚህ ዓመት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠውና በአሁኑ ወቅት መሬት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ የሚገኘው የከፍተኛ አመራር ኢንስቲትዩት ግንባታም በሂደት ላይ ሲሆን፤ ለግንባታው 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል።

መሠረተ ልማት የማሟላት ሥራው የፖሊስን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የፀጥታ መዋቅር ብሎም የሲቪል ተቋማት አመራሮችን ጭምር ለማሠልጠን የሚያስችል ነው። በቀጣይም በምስራቅ አፍሪካ የትምህርትና ሥልጠና የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየተሠራ ነው፤ በአፍሪካ ደረጃም አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ይሆናል። በተጨማሪም በማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የፖሊስ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች የሚያሰለጥኑበት ይሆናል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በቀጣይ የምልምል ማሠልጠኛ ማዕከል ለመገንባት የጥናት ሥራው ተጠናቋል። የሠላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል ግንባታ ለማከናወንም የዲዛይን ሥራው የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ ግንባታው ይጀመራል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ። የሚጨምሩት ሃሳብ ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?

ኮሚሽር መስፍን፡- አመሰግናለሁ። በአሁኑ ወቅት ለፖሊሶቻችን ሁሉንም ሙያ ያማከለ ሥልጠና እየተሰጠ ነው። አገራዊና ቀጣናዊ ተልዕኮዎችን መቀበልና መፈፀም የሚችል ኃይል እየገነባን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመገንንዘብ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ እየተደራጀ ነው። ይሁንና ወንጀልን ለመከላከል ሙሉ ለሙሉ ሥራው ለፖሊስ ብቻ የሚተው አይደለም። በመሆኑም ህብረተሰቡ ቀዳሚ ተሳታፊና ተባባሪ መሆን አለበት። ፖሊስ ለህዝብ አገልግሎት ይተጋል፤ ህዝብም ሊያግዝ ያስፈልጋል።

ቀደም ሲል በኮሚቴ አሊያም ደግሞ በልምድ የሚሠራ የነበረው ሥራ በአሁኑ ወቅት ባለሙያዎች የሚያቀርቡትን የጥናት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ችግሮችን መፍታት ሲሆን፤ ምክረ ሃሳቦችንም የመከተልና የመጠቀም ብሎም ወደ ትግበራ የመቀየር ሁኔታዎች ሥራ ላይ እየዋሉ ነው። ችግሮችን በጥናት የመለየትና ማስቀመጥ እንዲሁም ለችግሩ እልባት የሚሰጥበት አሠራርም ተዘርግቷል።

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *