ለዛሬው አምዳችን የምትሆነንን ስንቅ ፍለጋ ማረፊያችንን ከ1950ዎቹ መገባደጃ ላይ አድርገናል። ሞቻለሁ ብሎ የተናዘዘው የ16 ዓመቱ ታዳጊ ድኖ ለፍርድ ቀርቧል፤ 1958 ዓ.ም ስለተጠለፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የወጣ አንድ ዘገባ፤ እንዲሁም በጳውሎስ ኞኞ ይዘጋጅ ከነበረው የወይዛዝርት ገጽ የተወሰዱ ሃሳቦችም ሰፍረዋል። “የማታውቁት ነገር ቢኖር” ከዚህኛው ደግሞ ሁለቱን እናሳውቃችኋለን።
ሞቻለው ያለው ድኖ ተቀጣ
ኃይለማሪያም ከበደ የተባለው የ16 ዓመት ወጣት ጨንቻ ከተማ በአሽከርነት ከሚኖርበት ከአቶ የማነ ብርሃን ገ/መድህን ቤት ህዳር 22 ቀን 1958 ዓ.ም ለክቡር አባቴ አቶ የማነ ብርሃን ገ/መድህን ለክብረት እናቴ ከወ/ሮ ታደለች አበበ በማለት ለጽሕፉ መግቢያ ከሰጠ በኋላ በወ/ሮ ታደለች አበበ ንዴት ውሃ ጉርጉአድ ገብቼ ሞቻለሁ፤ ለቤተሰቦቼም አትናገሩ። ብሎ ጽፎና ፈርሞ እቤት ከተወጣ በኋላ ባለቤቶቹ በሌሉበት ሳጥን ከፍቶ 120 ብርና ልዩ ልዩ ልብሶችን ሰርቆ ጠፋ። አሳዳሪው አቶ የማነ ገ/መድህን ጽሁፉን አግኝተው ሲመለከቱ ስለተጠራጠሩ ለጨንቻ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ሁኔታውን በማብራሪያ አመለከቱ። ፖሊስም ከአመልካቹ የቀረበውን ጽሁፍ መነሻ በማድረግ ምርመራውን ቀጠለ። ኃይለማሪያም ሀብት በማግኘቱ ከሞተበት ድኖ ጉዞውን በምዕራብ ዓባያ አምርቶ አዲስ አበባ ለመግባት ሲጠባበቅ የሌቦች መጋኛ የሆነው ፖሊስ ደርሶበት የሰረቀውን ልብስ ሳያጠፋ ከነማስረጃው አርባ ምንጭ ባስቻለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ በስድስት ወር እሥራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24 ቀን 1958 ዓ.ም
ጠፍቶ በነበረው አኤሮፕላን ከአየር መንገድ የተሰጠ ማብራሪያ
ባለፈው እሁድ ጥር 22 ቀን 1958 ዓ.ም ወደ ሶማሊያ ተገዶ በበረረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዲሲ ሦስት ላይ ከነበሩት ዘጠኝ ተሳፋሪዎች አንዱ በቅርቡ እስራቱን የፈጸመ ወንጀለኛ መሆኑ ታውቋል። አይሮፕላኑ ከጅማ ወደ ባኮ ሲነሣ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ፣ መለሰ ቢራራ የሚባለው ሰው መሆኑን ጅማ የነበሩ የዓይን ምስክሮች ሲያረጋግጡ። የአይሮፕላኑ መጥፋት በተገለጠ ጊዜ የዚህ ሰው ስም ማኒፌስት (የመንገደኞች ስም የሚዘረዘርበት መዝገብ) ላይ አልተገኘም።
መለሰ ስሙን ለውጦ ከሰላማዊ መንገደኞች ጋር መሳፈሩ ለተንኮል ለመነሳሳቱ በቂ ማስረጃ ሆኗል። የአይሮፕላኑ ነጂ በኢትዮጵያ አየር ኃይልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ 13 ዓመት የበረራና ሁለቱ ረዳቶቹ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የተመሰገኑና መልካም ስም ያላቸው መሆኑ ታውቋል። አውሮፕላኑና በውስጡ የነበሩት ሰዎች ሁሉ በደህና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥረቱ መቀጠሉን፤ መንገደኞቹም ምንም አይነት አደጋ እንዳልደረሰባቸው ዛሬ ተገለጠ።
አዲስ ዘመን ጥር 29 ቀን 1958 ዓ.ም
ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ
አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ
ተማሪ ችግረኛ ከመሆኑ የተነሳ ጫማዬን የምለውጠው በክረምት ትምህርት ሲዘጋ ሥራ ፈልጌ በመሥራት ነው። የክረምት ዕረፍት ከመድረሱ በፊት ጫማዬ እንዳያልቅ በማሰብ፣ እጫማዬ ሥር የጫማ ብረት (ፌሮ) አስመትቼበት በመንገድ ስሔድ፣ አንዲት የማላውቃት ወይዘሮ ጆሮዋን ይዛ ፊቷን አጨማዳ ተከፋች። እኔም አሳቧ በፍጥነት ገባኝና ምነው? ምን ሆንሽ? ብዬ ብጠይቃት ጊዜ ጋሪ ናዝሬት ነው ያለው እንጂ አዲስ አበባ ቀርቷል ብላ ዘለፈችኝ። ያን ጊዜ ብመታት ይፈረድብኛል? ወይንስ ይፈረድልኛል?
አሸናፊ መንገሻ
……. ይፈረድብሃል ወዳጄ።
++++++++
ሴቶች ለጋብቻ በተጠየቁ ጊዜ ፎርም ያላት ሸንቃጣ መኪና፣ ቪላ ቤት፣ ፎቴ ወንበር፣ ከዚህም በላይ ከውጪ የሚያገኘው ከደመወዝ ሌላ ገቢ አለ ወይ? ሲሉ ጥያቄአቸውን ያቀርባሉ። እንግዲህ ምንም ሳይሠሩ የተንደላቀቀና የሞቀ ቤት ለማግኘት ያላቸውን የተስፋ ምርኩዝ አሳባቸው እስከ መቼ ድረስ ሊቆይና ሊቀር ይችላል?
ደገፉ ፈቅ ይበሉ (ከአዲስ አበባ)
….. ጊዜው አይታወቅም። ደግሞ ሁሉም አይጠይቁም፤ ድሮም ቢሆን እኮ ኑሮውን አሟልቶ ነው ሚስት የሚያገባው። ያም ቢሆን የዛሬው የመረዳዳት ጋብቻ የተሻለ ነው።
++++++++++++
ጥር 10 ቀን 1958 ዓ.ም “ስለ ቆዳችሁ ተጠንቀቁ” በሚል አርእስት የጻፍከውን አንብቤ ምክርህን ለመፈጸም ፈልጌ ነበር። ግን ዘመዶቼ ማር ያሸብታል ስላሉኝ መቀባት ፈራሁ። ለመሆኑ አንተ ስታስበው መድሃኒቱን ስንቀባ ቅንድባችንና ሽፍላችንን አያሸብተውም?
ወይዘሪት ዓለምነሽ ኪዳኔ (አዲስ አበባ)
………ማር ያሸብታል ከተባለ ጠጉሩን አትቀቡት።
አዲስ ዘመን የካቲት 23 ቀን 1958 ዓ.ም
+++++++
መኪና ለመግዛት አስቤ ነበረ። ምን አይነት መኪና ልግዛ? እስቲ አንተ ምረጥልኝ።
እንግዳ ወርቅ አበበ
……… ስንት ብር አለዎት?….
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 1958 ዓ.ም
++++++++
ባለፉት ሳምንታት አንዱ ከአርባ ምንጭ የአለቃ ገብረ ሐና ቀልድ በጋዜጣ እንዲታተምላቸው ቢጠይቁ አንዱ ደግሞ ከገሙ ጎፋ አለቃ በቀልዱ ዘመን ቀልደዋል። አሁን አያስፈልግም ሲሉ ተቃውመዋል። እውነት ነው ለሁሉም ጊዜ አለው ተብሏል። በድሮው ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ ሴቶች እራሳቸውን ይሸፍኑ (ይከናነቡ) ብሏል። በአሁኑ ዘመን ደግሞ ጋዜጠኛው ጳውሎስ ለሴቶች አለባበስና ጸጉር አሠራር፣ የአበላል ፎርም ሁሉ ሳይቀር ያስተምራሉ። ሆኖም የአለቃ ቀልድ በዚህ ዓምድ ወረፋ ባይሰጠው ጥሩ ነው።
አያሌው ቢሻው
አዲስ ዘመን ህዳር 10 ቀን 1958 ዓ.ም
የማታውቁት ነገር ቢኖር
በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘላት መጥፎ ሾፌር ወይዘሮ ሉላ ፔቲ ናት። ዘጠና ስድስት ጊዜ ከመኪና ጋር ተጋጭታለች። በዘጠና ሰባተኛው ግጭት ግን ሞተች። የሰማንያ አንድ ዓመት አሮጊት ነበረች።
+++++++++
በቢራ አጠጣጥ የአውስትራሊያ ሰዎች ከሁሉም ይበልጣሉ። አንድ ሰው ባመት 52 ጋሎን ቢራ ይጠጣል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም