ተደራሽ ያልሆነው የወር አበባ ጤናና ንፅህና ጉዳይ

እ.ኤ.አ በ2017 በወጣ ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ 63 ከመቶ የሚሆኑ ለአቅመ ሄዋን የደረሱ እንስቶች ስለ የወር አበባ ከሌሎች ሰዎች ጋር አያወሩም፤ አይወያዩም። 22 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች ወይም እናቶች ብቻ ሴት ልጆቻቸው የወር አበባ ከማየታቸው በፊት ስለ ወር አበባ አውርተዋቸዋል፡፡ 68 ነጥብ 1 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ በሃፍረት ምክንያት ስለ ወር አበባ ተወያይተው አያውቁም፡፡

ይህ ሪፖርት በተለያዩ ተፅእኖዎች ምክንያት ሴቶች እርስ በርስ እንኳን ተፈጥሯዊ ኡደት ስለሆነው የወር አበባ እንደማይነጋገሩና እንደማይወያዩ ይጠቁማል። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ እናቶችም ለሴት ልጆቻቸው ስለወር አበባ አስቀድመው ጥቂት ነገር ቢሉ እንጂ የወር አበባ ማየት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ልጆቻቸው ይህ ክስተት ተፈጥሯዊና ምንም የሚያሳፍር ነገር እንዳልሆነ ተረድተው ክስተቱን እንዲቀበሉ የማድረግ ልምድ እንደሌላቸው ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሴቶች በተለያዩ የባህል ተፅእኖዎችና የተዛቡ አመለካከቶች ምክንያት ሀፍረት ሸብቧቸው ስለ የወር አበባ እርስ በርሳቸው እንደማይነጋገሩ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ሪፖርቱ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ በጥቅሉ ያለውን መረጃ አሳየ እንጂ በኢትዮጵያ በወር አበባ ጤናና ስነ-ንፅህና ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ እጅግ ደካማ ስለመሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡ በሀገሪቱ አሁንም ድረስ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ማግኘት ለሴቶች ብርቅ የሆኑባቸው አካባዎች አሉ፡፡ በሴቶች በኩል በሚታዩ የግንዛቤ እጥረቶች ምክንያት የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ የመጠቀም ሁኔታም በከተማ ካልሆነ በቀር በገጠር አካባቢዎች ላይ በእጅጉ ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ለሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት አመቺና የንፅህና መጠበቂያዎችን ያሟሉ የመታጠቢያ ክፍሎች እንደልብ አይገኙም፡፡ አካል ጉዳተኛ ሴት ተማሪዎች ደግሞ በዚህ ችግር ምክንያት ምን ያህል ሊጎዱ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡ በርግጥ በከተሞች ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከወር አበባ ንፅህና ጤና ጋር በተያያዝ አንዳንድ ስራዎች የተጀመሩ ቢሆንም በገጠር ግን ገና ብዙ ስራ ይቀራል፡፡

ለወር አበባ ጤናና ስነ-ንፅህና ትኩረት መሰጠት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ የወር አበባ ጤናና ንፅህናን ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረትም ያን ያህል አይደለም፡፡ ለዛም ነው የዘንድሮው የወር አበባ ቀን ‹‹የወር አበባ ንፅህና ጤናን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን›› በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የወር አበባ ንፅህናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን መሰረት አድርጎ በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት የተከበረው፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራምና ጥራት ማሻሻያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮሐንስ ዋጌሶ እንደሚናገሩት፤ ትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የመጡ እዳዎችን ለመክፈል የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ተማሪዎች የሚማሩት ትምህርት ከሃያ አንደኛው ከፍለ ዘመን ጋር ተስማሚና አብሮ እንዲሄድ ማድረግ፣ የሚማሩበት የትምህርት ተቋማት ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ ማስቻልና መምህራኖቻቸውና የትምህርት አመራሮቻቸው በቂ ክህሎትና እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን የሪፎርም ስራዎች የሚያከናውነው በዋናነት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ቢሆንም ይህ ሥራ የሚከናወነውና ውጤት የሚመጣው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መጥተውና ቆይተው ሲማሩ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መጥተው መቆየት ካልቻሉ ተፈላጊውን እውቀትና ክህሎት መጨበጥ አይችሉም፡፡ ለተማሪዎች በክፍል ውስጥ የመገኘት፣ የመቆየትና የመዝለቅ ምጣኔ፤ በተለይ ደግሞ ለሴት ተማሪዎች ፈታኝ በሆኑባቸው ወይም የትምህርትን ጥራት ከሚገዳደሩ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ከትምህርት ቤት የመቅረት ምጣኔ ነው፡፡

ይህ የመቅረት ምጣኔ፣ በወንድና በሴት ሲነፃፀር ሴቶች ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ ከወር አበባ ጋር በተገናኙ ችግሮች 20 ከመቶ የሚሆኑ የትምህርት ቀናት ይባክናሉ፡፡ ይህን ያህል መጠን የትምህርት ቀናት ባከኑ ማለት ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ባለመገኘታቸው የተነሳ ተፈላጊውን እውቀትና ክህሎት አይጨብጡም፡፡ በዚህ ምክንያት በትምህርት ወደ ኋላ ይቀራሉ፡፡ ወደ ኋላ ሲቀሩ ደግሞ ተስፋ ቆርጠው ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፡፡ ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ፊት እየሄዱም ከሆነ ክፍል መድገማቸው አይቀርም፡፡ ክፍል ያልደገሙም ቢሆኑ እንኳን ከሌሎች አቻዎቻቸው እኩል በትምህርት መግፋት እድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት ይህን ችግር ለመቅረፍ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።

ነገር ግን ደግሞ ጥረቶቹ በቂ ናቸው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ እንደ ሀገር 51ሺህ እና ከዛ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ምቹ የትምህርት ከባቢ ሁኔታ፤ በተለይ ለሴት ተማሪዎች ምቹ ሁኔታ ያላቸው ትምህርት ቤቶች በጣም ዝቅተኛ ናቸው፡፡ ከ20 በመቶ የሚዘሉም አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል 80 ከመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን እንኳን አላሟሉም፡፡

በቅርቡ ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻል ዘመቻ ትምህርት ሚኒስቴር ጀምሯል፡፡ የዘመቻው አካል ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ የትምህርት ቆይታቸው ምቹ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ለዚህም የወር አበባ ጤናና ስነ-ንፅህና ድጋፎች እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ አካታችና ተደራሽ የሆነ የውሃ፣ መፀዳጃ ቤትና የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ክፍሎች ግንባታ የሚውሉ ልዩና ደረጃቸውን የጠበቁ ዲዛይኖች በማዘጋጀት የወር አበባ ጤናና ስነ ባህሪ ስራዎች ከዚሁ ጎን ለጎን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ እቃዎችን ለተማሪዎች ለማቅረብና የስነ ልቦና ድጋፎችን ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለወላጆች፤ እንዲሁም ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ተጨማሪም እነዚህን አገልግሎቶች፣ በተለይም ሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚደርሱባቸውን ተደራራቢ ችግሮች ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ይህንን ሥራ እየሰራ ነው፡፡

በሁሉም ትምህርት ቤቶች የስነ ፆታ፣ የውሃና ንፅህና ክበባትንና ሚኒ ሚዲያዎችን በማጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ተገቢው የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎት እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ ተጨማሪም ከጤና ሚኒስቴርና የተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን አካታች የሆኑ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ፣ መቀየሪያና ማረፊያ ክፍሎችን በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ500 የማያንሱ ትምህርት ቤቶች የዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ይሁንና 500 ትምህርት ቤት ከ51ሺህ ትምህርት ቤቶች ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ይህም በዚህ ረገድ በርካታ ጥረትና ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ ተደራሽ ሊሆኑ የሚገቡ በርካታ ሴት ህፃናትና ታዳጊ ተማሪዎች አሁንም አገልግሎቱን እያገኙ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ28 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ተማሪዎች ውስጥ ግማሾቹ ሴቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ከእነዚህ ውስጥ የወር አበባ ንፅህናና ጤና አገልግሎት የሚያገኙት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለመፍትሄው መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወይዘሮ ዘቢደር ቦጋለ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የወር አበባ ጉዳይ በማህበረሰቡ እንደ እርግማን የሚቆጠር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሴቶች በአፍላ እድሜያቸው የወር አበባ ማየት በሚጀምሩበት ወቅት መሸማቀቅና ማፈር ይታይባቸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የተለያዩ ችግሮች ይገጥሟቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ስለወር አበባ አመጣጥ ቀድሞ ከቤተሰብ ግንዛቤ ስለማይሰጣቸው የወር አበባ ሲመጣ የመደንገጥና የመሸማቀቅ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የወር አበባ በሚመጣበት ወቅት ንፅህናቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ከቤተሰብ ተመሳሳይ ግንዛቤ ስለማያገኙ፤ በትምህርት ቤቶችም በዚሁ ልክ ስለ ወር አበባ አመጣጥና የንፅህና አጠባበቅ በቂ ግንዛቤ ስለማይሰጥ የመሸማቀቅ፣ ከትምህርት ቤት የመቅረትና ትምህርታቸውን የማቋረጥ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡

በተለይ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የወር አበባ መጥቶባቸው ልብሳቸው ከተበላሸ በኋላ በእፍረት ወደ ትምህርት ቤት የማይመጡበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ህብረተሰቡም አንዲት ታዳጊ ወጣት የወር አበባ አየች ማለት ለጋብቻ ደርሳለች በሚል የተዛባ አመለካከት በተለይ በገጠራማዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለ እድሜ ጋብቻ የሚገጥምበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ከዚህ አንፃር ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ናቸው የሚታዩት፡፡

አማካሪዋ እንደሚያብራሩት፤ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የሚታየውን የተዛባ አመለካክት ለማስተካከል ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች ብሎም አዋቂዎች ስለ የወር አበባ እንዲያውቁ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ችግር የሆነው የወር አበባ ጤናና ንፅህና ተደራሽነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በቀጥታ ከኑሮ ውድነትና ይህን ተከትሎ በእቃዎች ላይ ከጨመረው ዋጋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚታጠቡና ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያዎች /ሞዴሶች/ ከአምራቾችና አስመጪዎች ጋር በመነጋገር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንዲገኙ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በግዢም ጭምር በተለይ ለትምህርት ቤቶች እንዲወርዱም እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም በሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ላይ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡

በገጠር አካባቢም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የወር አበባ ጤናና ንፅህና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በተለይ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች በተጨማሪ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያዎችም አብረው እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ፤ በተለይ የሴቶችን ተጠቃሚነትና የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚሰሩ አካላት የወር አበባ ጤናና ንፅህና ጉዳይ እንደ አንድ ሥራ ቆጥረው እንዲሰሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግንዛቤ እያስጨበጠ ይገኛል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እንደሚናገሩት፤ በወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ ከችግሩ ስፋት አኳያ ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም በትምህርት ቤቶች አካባቢ መልካም ጅምር ስራዎች አሉ፡፡ የወር አበባ ንፅህና ጉዳይ በውሃና ንፅህና ፕሮግራም ውስጥ ተካቶ እንዲሰራ ጥረቶች እየተደረጉ በመሆናቸው ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ስራውን የእቅዳቸው አካል አድርገው ሊሰሩና ድጋፍም ሊያደርጉ ይገባል፡፡

በሀገሪቱ እስከ 18 በመቶ የሚጠጉት ህብረተሰብ ክፍሎች የአካል ጉዳተኞች እንደመሆናቸውና ማንኛውም ሰው ደግሞ መቼ የአካል ጉዳት ሊያጋጥመው እንደሚችል ስለማይታወቅ በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች የበለጠ ለወር አበባ ንፅህና አገልግሎት ችግር ስለሚጋለጡ በትምህርት ቤቶች አካባቢ እነሱን ታሳቢ ያደረገ ምቹ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

የ2015 ዓ.ም የወር አበባ ጤናና ንፅህና ቀንን ታሳቢ በማድረግ በማህበረሰብ ውስጥ በወር አበባ ዙሪያ ያሉ የጤና ችግሮችን፣ የተዛቡ አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን በማረም በሴቶችና ልጃገረዶች በኩል የሚደርሱ መገለሎችንና እንግልቶችን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል፡፡

የወር አበባ ጤናና ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ማግኘት ከአቅማቸው በላይ የሆነና የቅንጦት እቃ የሆነባቸው በርካታ ልጃገረዶችና ሴቶች በገጠርም፤ በከተማም አሉ። በተለይ ደግሞ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይህ ችግር አስከፊ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ተደራሽነት ላይ ሰፊ ስራዎችን በጋራ መስራት ይገባል፡፡ በተመሳሳይ በወር አበባ ጤናና ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ ሴቶችና ልጅ አገረዶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማስተማር ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *