አዳማ፡- በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የተለያዩ የተማሪዎች ኅብረትን ማጠናከር ለሰላም ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ። “መቻቻል እና ሰላም ለአገር እድገት ግንባታ” በሚል ርዕስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በኢፌዴሪ ሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአዘጋጁት ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው አውደ ጥናት ላይ እንደተነገረው፤ የተማሪዎች የተለያዩ ኅብረቶችን ማጠናከርና ማዘመን በተቋማቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ማድረግ ያስችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ለአካባቢ ማኅበረሰብ የሚደርስ የሰላም ትሩፋት መሆኑ ተገልጿል። በአውደ ጥናቱ ላይ የመወያየ ፅሑፉ ያቀረቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን እንዳሉት፤ የተማሪዎች የሰላም ፎረምን ጨምሮ የተማሪ ፖሊስ፣ ጊቢ ጉባኤ፣ ጀማአ፣ ፌሎሺፕ እና የመሳሰሉ የተማሪ ኅብረቶች ሲጠናከሩ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ሰላምን ለመምራት ያስፈልጋሉ። እነዚህንም የተማሪዎች ኅብረቶች ማጠናከርና ማዘመን ወሳኝ ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር አባተ ገለፃ፤ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የሰላም ፎረም ከአስር ሺ አንድ መቶ በላይ አባላት አሉት። ከዚህም በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን በሰላም ፎረሞች በማካተት፤ በመመካከርና በመወያየት ከግቢው ሰላም አልፎ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሰላምን በመጠበቅ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረሙ ስለሰላም በማቀድና በመከታተል፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሥራትና በተለይም ኪነጥበብን ለሰላም በመጠቀም አመርቂ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው ይህንን ተግባር ለማከናወን ግን በቅድሚያ ውስጣዊ ሰላምን ማስፈን የሚጠበቅ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በተለይም በተቋማቱ ለተማሪና ለሠራተኛ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማሻሻል፤ግጭትን ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ ከምግብ አዳራሽ፣ ከመገልገያ ቁሳቁሶች፣ ከሃይማኖት ቅስቀሳና ከተማሪዎች ቅበላ ጋር በተገናኘ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከትምህርት ጋር በተገናኘም የመምህራንና የተማሪ ግንኙነት እንዲሁም የየአንዳንዳቸው ሥነ ምግባር ላይ የሚታዩ ችግሮችም ሊቀረፉ ይገባል ብለዋል።
“ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ሀብት ስለሆኑ ዓለምአቀፍ አመለካከትና ፍልስፍና እንዲበለፅግባቸው መደረግ አለበት” ያሉት ዶክተር አባተ፤ ብዙ ጊዜ ግን ይህ ባለመሆኑና ተቋማቱ ባሉበት አካባቢ በመታጠራቸው ችግሮች እንደሚከሰቱ አንስተዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ ማንም ሰው በብሔሩ፣ በቋንቋው ወይም በሃይማኖቱ እንዳይገለል እየሠራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፤ መምህራኑም ተማሪዎቻቸውን እንደገዛ ልጆቻቸው በማየት የሚያጠፋውን ተማሪ እንዴት ማስተካከል እንደሚችሉ ያውቃሉና ጥንቃቄ ያደርጋሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በአውደጥናቱ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ከ54 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንና የተማሪዎች ኅብረቶች መሪ ተማሪዎች ተሳትፈዋል። በውይይቱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኩል የልምድ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊነቱ የተነሳ ሲሆን፤ በተጨማሪም ስለ ሰላም ከተባለ ለእነዚህ የተማሪዎች ኅብረቶች ትኩረት እንዲሰጥ የተማሪ ኅብረት ተወካዮች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
ሊድያ ተስፋዬ