ሕገወጥነት ይቀንሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲስ ቴክኖሎጂ

ስለ ወርቅ ስናነሳ አሁን አሁን ቀድመን የምናስበው ሕገወጥነትን ነው። ምክንያቱም እንደ ሀገር ያለው ወርቅ በሕገወጦች አማካኝነት እየተወሰደ በሕገወጥ መንገድ ይቸበቸባል። ከዚያም መንግሥት በየጊዜው የወርቅ ምርታቸውን ገቢ ማምጣት አልቻለም ይላል። እንደውም በአንድ ወቅት ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ አይደለም ሲል መግለጫ ሰጥቶ ነበር። ይህ ደግሞ የሚያሳየን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ባለመግባቱና በሕገወጥ መንገድ እየወጣ መሆኑ በሀገሪቱ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና እያረፈ መሆኑን ነው።

እኤአ በ2021/2022 አምስት ወራት ውስጥ የነበረው አፈጻጸም የሀገር ውስጥ ወርቅ አቅርቦት በሕጋዊው የዶላር ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው መካከል ሰፊ ልዩነት የነበረው ሲሆን፤ በዚህ ችግር ምክንያት ደግሞ የተገኘው ገቢ ከቀደመው ዓመት ዝቅ ብሎ 180 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሆኗል። የወርቅ አቅርቦቱና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ቅናሽ እያስመዘገበ እንዲሄድም አድርጎታል። እንደውም በዓመቱ ጭምር ያለውን የወርቅ ገቢ ሳይቀር ቀንሶት እንደነበር በብሔራዊ ባንክ በኩል የወጣው መረጃ ያመላክታል።

መረጃው እንደሚያሳየው፤ በ2022/2023 አምስት ወራት ውስጥ ከወርቅ ምርት የተገኘው ገቢ ከቀደመው ዓመት በ81 በመቶ አሽቆልቁሎ 33ነጥብ2 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል። እናም አሁንም ብሔራዊ ባንክ ነገሮችን ማየትና በተሻለ መልኩ መሥራት እንዳለበት አሳምኖታል። ለዚህም አዲስ አሰራር ለመቀየስ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ተባብሯል። እንዲሻሻል ከተፈለጉት መካከል ደግሞ አንዱ ማዕድን ሚኒስቴር ላለፉት 12 ዓመታት ሲሠራበት የነበረውንና ሕገወጥ የወርቅ ንግድ እንዲስፋፋ መንስዔ ሆኗል የተባለው አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ በአዲስ የማዕድን አዋጅ እንዲተካም እየተሰራ ይገኛል።

የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተውም አዲሱ አዋጅ ሕገወጥነትን ከመከላከል አልፎ በቅንጅት መስራትን ያበረታታል። እስካሁን ድረስ እንደ ሀገር ወርቅ በባህላዊ መንገድ በጥሩ ሁኔታ ቢመረትም ባህላዊ የወርቅ አምራቾች ግን ምርቱን ወደ ብሔራዊ ባንክ እያመጡ አይደለምና ይህንን በቅንጅት ሰርቶ ለመፍታት የሚያስችል ነው ተብሎለታል። ማለትም የማዕድን ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና አምራች ኩባያው አብረው መስራት የሚችሉበት እድልን ይፈጥራል። በዚህ ደግሞ ሕገወጥነት ይገታል።

ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ወይም ኩባንያዎች የሚያመርቱት የወርቅ መጠን በቀላሉ የማይታወቀውና ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ የማይሆንበት ምክንያት ተናቦ መስራት፤ በጋራ መንቀሳቀስ ስላልተቻለ ሲሆን፤ ይህንን በማዕድን አዋጅ ማከም ያስፈልጋልና አሁን በዚህ ደረጃ ወደ ሥራ ለመግባት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውንም በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ዘንድ የወጡት መረጃዎች ያመላክታሉ። አንዱ ደግሞ የወርቅ ግብይት ሥርዓትን በአጠቃላይ ለማሻሻልና አሁን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከማዕድን ሚኒስቴር በተወጣጡ ባለሙያዎች የተዋቀረ የጥናት ቡድን መመስረቱ ነው።

ይህ ቡድን ጥናት አካሂዶ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን ማስቀመጡን ያመላከተው መረጃው፤ ከእነዚህ መካከልም በስፋት የታየውና ወደ ሥራ የተገባበት የሚመረተው የወርቅ መጠን ከዓመት ዓመት የሚፈለገውን ገቢ እያስገኘ ባለመሆኑ የአገር ውስጥ ወርቅ አምራቾች ያመረቱትን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የመሸጥ ሕጋዊ ግዴታ እንዳለባቸው የሚደነግገው ነው። ለዚህ ተግባር እንደማሳያነት የሚጠቀሰው ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ይገባል የተባለው የቱሉ ካፒ የወርቅ ፕሮጀክት ነው።

ይህ ፕሮጀክት የተያዘው በዓለምአቀፍ የወርቅ አውጪ ኩባንያ ቢሆንም በሀገር ውስጥ በአዲስ ቴክኖሎጂ ወርቅን ለማምረት የሃያ ዓመት ፈቃድ የተሰጠው ነው። ኩባንያው ለስምንት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ ቢቆይም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ አልገባም ነበር። በዚህ ምክንያትም በመንግስት በኩል ሲከሰስ ቆይቷል። ከተከሰሰበት ምክንያቶች አንዱ ‹‹ተፈላጊውን ፋይናንስ አላሟላም›› የሚል ነው። አሁን ላይ ግን ለስድስት ወራት ያህል ጠንካራ ሥራዎችን በማከናወኑ ወሳኝ የሚባሉ ለውጦችን አምጥቶ ከመንግሥት ይሁንታን አግኝቶ ፕሮጀክቱን በይፋ ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል።

ለዚህ ፕሮጀክት እድሉ የተሰጠበት ምክንያት ከላይ እንደተባለው ተቋማቱ ተናበው የሚሰሩበትን ሁኔታ ስለያዘ ነው። ማለትም ፕሮጀክቱ የተጀመረው በኢትዮጵያ መንግሥትና በኩባንያው መካከል በተደረገ ስምምነት ሲሆን፤ ነጻ ወለድ ጭምር የሚከፈልበት ነው። በዚያ ላይ የወርቅ ምርቱ በዓመት በአማካኝ 140 ሺህ አካውንት ይገኝበታል። ሁለንተናዊ የማቆየት ዋጋው ደግሞ ከ800 እስከ 900 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያስገኛል። ስለዚህም ይህ ፕሮጀክት ኢኮኖሚውን ከማሻሻል አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

ሌላው ፕሮጀክቱን በሀገር ውስጥ እንዲሰራ ያስቻለው ነገር ይዞት የመጣው አዲስ ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ ሕገወጥነትን ከመከላከል አኳያ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ታምኖበታል። እንዴት ከተባለ ከቁፋሮው እስከ ምርቱ ድረስ ያለውን ሂደት ሙሉ ለሙሉ በሚታወቅበት ሁኔታ በቴክኖሎጂ ደግፎ ይሰራል። ስራው ሲከናወንም ከአካባቢው የሚወጡ የወርቅ ምርቶች ዓለም አቀፋዊ መለያ ቁጥር እንዲኖራቸው ተደርጎ ነው። በመለያ ቁጥሩ አማካኝነት ምን ያህል ወርቅ ከወርቅ ማምረቻው ወጣ፤ ምን ያህል ወርቅ ለዓለም ገበያ ቀረበ፤ ምን ያህል ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደረገ የሚሉትን ማወቅ የሚያስችል ነው። ስለዚህም ይህ መሆኑ አሁን ሀገር እየተፈተነችበት ያለውን ሕገወጥነት በብዙ መልኩ ይፈታል።

ወርቁን ልውሰድ የሚል አካል እንኳን ቢፈጠር የሚከታተሉበት መለያ ቁጥር ስላለ እጅ ከፍንጅ የመያዝ አጋጣሚን ይፈጥራል። በቴክኖሎጂ የሚሰራ በመሆኑ ከሰዎች የእጅ ንክኪና ስርቆትም የራቀ ነው። ለመሆኑ ይህንን ሥራ እንዲሰራ የተሰጠው ኩባንያ ማን ነው፤ የእስከዛሬው ሥራዎቹ ምን ይመስላልና መሰል ጥያቄዎች መነሳታቸው ስለማይቀር ምላሽ ለመስጠት ያህል ትንሽ ስለኩባንያው እናንሳ።

ኩባንያው የእንግሊዞች ሲሆን፤ ካፊ ሚነራልስ (የቱሉ ካፒ ወርቅ ልማት ፕሮጀክት) በመባል ይጠራል። ሥራውን የሚያከናውነው በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ነው። የሚሰራው ደግሞ በካፊ ሚነራልስ ፒኤልሲ አማካይነት ነው። ቱሉ ካፒ የወርቅ ማውጫ ፕሮጀክት ስያሜውን ያገኘው በአካባቢው ከሚገኘው ቱሉ ካፊ ከተሰኘው ተራራ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ ማለት ደግሞ የአካባቢውን ሰው ሳይዙ ሥራ እንደማይታሰብ ለማሳየት የሞከረበት መሆኑንም የተቋሙ የተገኙ መረጃዎቹ ያመላክታሉ።

ኩባንያው እንዴት የአካባቢውን ሰው ያግዛል የሚል ጥያቄ ከተነሳም አንዱ የአካባቢውን ማኅበረሰብ አማክሎ የሥራ እድል ይፈጥራል። አዳዲስ የሠራተኞች ቅጥርን ሲፈጽም ከዚያው ከአካባቢው ማህበረሰብ ነው። ይህም በቁጥር ሲቀመጥ ወደ ሥራ ሲገባ ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ አዳዲስ ሠራተኞች በቋሚነት የሥራ እድል ይፈጥራል። ከአምስት እስከ አስር ሺህ ለሚሆኑ ቋሚ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን የሚያገኙ ናቸው።

በማዕድን ዘርፍ የተሰማራው የዓለም አቀፉ ኩባንያ ቱሉ ካፒ ፕሮጀክት ቱሉ ካፊ ኩባንያ ሊቀመንበር ሚስተር ሀሪ አናጎስትረስ እንደተናገሩት፣ ፕሮጀክቱ ለማህበረሰቡ የሚያደርገው ነገር የሥራ ቅጥርን ብቻ የያዘ አይደለም። ወደ ሥራ ሲገባ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በመገንባት፣ ሆስፒታል በመገንባትና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቶችን ለማቅረብ ድጋፉን ያደርጋል። በተጨማሪም እንደ ሀገርም ቢሆን ከፍተኛ አስተዋፅጾ ይኖረዋል። ለምሳሌ፡- ኩባንያው ሥራ ጀምሮ ወርቅን ለገበያ ሲያቀርብ እ.ኤ.አ.በ2025 አገሪቱ ወርቅን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ገቢ ከምታገኝባቸው የገቢ ምንጮች አንዱ ይሆናል። በተጠቀሰው ዓመት ብቻ ከሚቀርበው ወርቅ 250 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘትም ጥረት ያደርጋል።

ይህ ኩባንያ ለወርቅ ማምረቻ ፕሮጀክቱ 500 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ይዞ መነሳቱን የሚጠቅሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ እስካሁን ድረስ ለወርቅ ክምችት ጥናትና ለተያያዙ ሥራዎች 80 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። ስለዚህም ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ በማስገባት ጥሩ እድል ይፈጥራል። በህገወጥ መንገድ የሚወጣውን የሃገርን ሀብት ለመታደግ ያስችላል።

በአሻጥር በሕገወጥ የወርቅ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን አስቁሞ ሕጋዊ መንገድን እንዲከተሉ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ የወርቅ ግብይቱን በተሻለ መንገድ እንዲጓዝና ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ከፍ እንድታደርግ ያስችላታል። ‹‹ለእኛም ቢሆን የሚሰጠው ጥቅም ቀላል አይደለም። ስማችንን እንድንተክልና ትርፋማ እንድንሆን ያግዘናል። ስለዚህም ሀገሪቱ ላይ በመስራታችን ደስተኞች ነን ››ሲሉ ያላቸውን ስሜት አጋርተዋል።

ይህ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት በቅድመ ሁኔታ ሲጠይቀው የነበረው የፋይናንስ ጉዳይን በመፍታቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ በተለይ ኢትዮጵያ ‹‹የአፍሪካ ፋይናንስ ትብብር ድርጅት›› አባል መሆኗ በብዙ መልኩ አግዞታል። እንዴት ከተባለም የፕሮጀክቱ አበዳሪ ባንኮች የዚህ የአፍሪካ ፋይናንስ ትብብር ድርጅት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ናቸው። እነዚህም የአፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ (Trade and Development Bank – TDB) እና የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (Africa Finance Corporation–AFC) ሲሆኑ፤ መጀመሪያ ብድር እንዳይሰጡ ያደረጋቸው ሁኔታ በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር ነው። አሁን ግን በመንግሥት በኩል ነገሮቹ ስለተስተካከሉ አበዳሪዎቹ ይሁንታቸውን ሰጥተውታል።

ባንኮቹን ያሳመናቸው ሁለት መሰረታዊ ነገሮች እንደሆኑ የሚያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ አንደኛው ኢትዮጵያ አባል መሆኗ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ በተለያየ መልኩ የተረጋጋ መሆኑ ነው። እናም አሁን ላይ ከባንኮቹ ጋር የቱሉ ካፒ ወርቅ ልማት ፕሮጀክት ስምምነት ላይ ደርሷል። አስፈላጊ የሆነውን የፋይናንስ ድጋፍም አግኝቷል። ይህ ደግሞ በስምምነቱ የፕሮጀክቱ ችግር እንዲፈታ ሆኗል። መንግሥትም መተማመኛ ሰጥቶ ወደ ሥራ እንድንገባ ፈቅዷል ይላሉ።

አሁን ከጸጥታ ጋር ተያይዞ በመንግሥት እየተሰራ ያለውን ሥራ እጅግ የሚያስደንቅና እነርሱንም በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሰሩ ያደረጋቸው መሆኑን የሚናገሩት ሚስተር ሃሪ፤ በተለይም ከሚያዚያ ወር ጀምሮ መንግሥት በቱሉ ካፒ ማዕድን ማውጫው አካባቢ ቋሚ የፀጥታ ኃይል ማስፈሩ ለኩባንያውንም ሆነ ለአበዳሪው አካል እፎይታ ፈጥሯል። ኩባንያው በልበ ሙሉነት ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ያስቻለውም ይኸው ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።

ኩባንያው ከባንኮቹ ጋር ያደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲና መርህ መሠረት የተከናወነ እንደነበር የሚያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህ መሆኑ ለኩባንያው ሥራ ብዙ እድል ሰጥቷል። አንዱ ኩባንያው ባለፈው ወር ለሦስት ቀናት የቆየ ዓውደ ጥናት እንዲያካሂድ አስችሎታል። ከመንግሥት ተወካዮች ጋር በመሆን የድርጊት ዕቅድ ማዘጋጀት እንዲችልም እድል ሰጥቶታል። በተጨማሪም በቀጣይ ወራት ውስጥ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚያስችል ፈጣን እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል። አሁንም ቅርቡ በዚህ መልክ ቢቀጥል ምኞታችን ነውም ሲሉ ያለውን ሁኔታ አብራርተዋል።

‹‹በእርግጥ እነዚህ ችግሮች ባይፈጠሩ ኖሮ ኩባንያው ቀድሞ ሥራውን መከወን ይችል ነበር። ፕሮጀክቱን ለመጀመር እንደኩባንያ ዳተኛ አልነበርንም። ምክንያቱም ለፕሮጀክቱ 80 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ አውጥተናል። እናም ማንም ቢሆን ይህንን ከፍተኛ ወጪ ትቶ መሄድ አይቻልም። ስለዚህም አቋማችን ነገሮች ሲረጋጉ ወደ ሥራ እንገባለን ነው። እናም ሁሌም ቢሆን የኩባንያው አቋም ቦታውን አልምቶ፤ ወርቁን አውጥቶ መጥቀም፤ መጠቀምም ነው›› ሲሉ ያለፉበትን ውጣውረድና አሁን የመጣውን መልካም እድል ያስረዳሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *