አዲስ አበባ፡- የቱሪዝም ኢትዮጵያ “ምድረ ቀደምት” የሚለው አዲሱ መለዮ በተፈለገው መጠን በህብረተሰቡ ዘንድ እንዳልሰረጸ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን ትናንት በካፒታል ሆቴል በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቁት የሀገሪቱ የቱሪዝም መለዮ ስያሜ የ13 ወር ጸጋ የሚለው ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ወደ ምድረ ቀደምት መቀየሩ ይፋ ቢደረገም አዲሱን ስያሜ ህብረተሰቡም ሆነ ቱሪስቶች እንዲያውቁት በሚያስችል ደረጃ አልተሰራም። ይህም በመሆኑ የቀደመው ስያሜው የሰራውንና መለዮ የሆነውን ያህል አዲሱ መለዮ በእዛ ልክ ተጽዕኖ አለመፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን በሚገባ ይገልጻታል የተባለው አዲሱ የቱሪዝም መለዮ ኢትዮጵያ የሁሉ ነገር መነሾ እንደሆነች የማስተዋወቅ አቅም እንዳለው ጠቁመው ድርጅቱ የማስተዋወቁን ስራ በሚገባ ባለመስራቱ መለዮው በሚጠበቀው ልክ እንዳይታወቅ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አንዱ መንገድ አገራዊ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ሲሆን በቀጣይም ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመዞር እስከ ታችኛው የአገሪቱ መዋቅር ድረስ በመውረድ የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ኢትዮጵያ የገበያ ልማት ቡድን መሪ አቶ ወልደገብርኤል በርሄ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በሚገባ ያልተጠቀመች አገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ድርሻዋ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም ካላት እምቅ የቱሪዝም አማራጮች አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን በዓለም አቀፉ ቱሪዝም ድርጅት የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክት ጠቅሰው ኢትዮጵያም ያላትን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀም የአንበሳውን ድርሻ እንደምትይዝ አንስተዋል፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለትምህርት፣ ለስራ እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች ከአገር አገር ሲዘዋወር መለዮን ጨምሮ አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስተዋወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል። ድርጅቱም የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ መለዮ ምልክቱን ለማስተዋወቅ ይሰራል ብለዋል፡፡
እአአ በ2000 የአፍሪካ ጎብኚ ቱሪስቶች ቁጥር 26 ሚሊዮን ገደማ እንደነበር አስታውሰው ይሄ ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 53 ሚሊዮን ቢያድግም ከዓለም አቀፍ ያለው ድርሻ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ነው፡፡ የዕድገት መጠኑ ፈጣን የተባለለት የአፍሪካ ቱሪዝም እኤአ እስከ 2030 የቱሪስቶች ቁጥር ከዕጥፍ በላይ በማደግ ከ134 ሚሊዮን እንደሚደርስ የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ድርጅት ትንበያ ይጠቁማል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
አብርሃም ተወልደ