አዲስ አበባ፡- የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በየምዕራፉ ለሚዘጋጁ የመካከለኛ ዘመን ዕቅዶች ፈር ይዘው መዘጋጀታቸውንና በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት መጓዛቸውን መቆጣጠሪያ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማሳካት ያለመ ማዕቀፍ መሆኑን የፕላን ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በኮሚሽኑ የመሪ ፕላን ዕቅድ እና ጥናት ዳይሬክቶሬት አቶ ሀብታሙ ታከለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት የአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን የማምጣት ዓላማን ለማሳካት እንዲሁም ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን በግልጽ በማስቀመጥ ውጤታማና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን የሚያስችል ነው። በሌላ በኩል ዕቅዱ የልማት ኃይሎችን በማስተባበርና በተለያዩ ደረጃዎች በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ዜጎችን እኩል ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የአስር ዓመቱ የልማት መሪ ዕቅድ በዋናነት ሀገራዊና ስትራቴጂያዊ የልማት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህ የልማት መሪ ዕቅድ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማፋጠንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንዲሁም የመዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ኢኮኖሚውን መምራት እና ማስተዳደር የሚያስችሉ ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ፣ የክፍላተ ኢኮኖሚ ልዩ የትኩረት መስኮች ላይ እንደሚመሰረት ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ለልማት መሪ ዕቅዱ የጀርባ አጥንት በሆኑ መስኮች ላይ ጥልቅና ሰፊ የጥናትና ትንተና ስራዎችን በማካሄድ ግኝቶችን ለልማት መሪ ዕቅዱ ዝግጅት እንደ ግብዓት መጠቀም የስፈልጋል ብለዋል፡፡ የዕቅዱ ሚና በዋናነት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥና በየምዕራፉ በሚኖሩ የመካከለኛ ዕቅዶች ዘመን ዕቅዶች አማካይነት ተግባ ራዊ የሚደረጉ መሰረታዊ የእድገት አቅጣጫ ዎችን፣ዓላማዎችንና ግቦችን እንዲሁም የማስፈጸሚያ ስልቶችን በማመላከት ኢኮኖሚው በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ለመምራት እና ለመከታተል የሚስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዕቅዱን ለማዘጋጀት መነሻ የሚሆኑ በተመረጡ ዋና ዋና ዘርፎች ማለትም ማክሮ ኢኮኖሚ፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማት በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ ኢነርጂ፣ መሰረተ ልማት፣ በሰው ሀብት ልማትና በትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በከተማ ልማትና ቤቶች ፣ በስነ ህዝብ ልማት ላይ ለልማት መሪ ዕቅዱ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶች እንዲካሄዱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
አብርሃም ተወልደ