አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ቀዳሚ ዓላማው የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ፓርቲው እስኪመሰረት ድረስ ቃል አቀባይ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ናትናኤል ፈለቀ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ናትናኤል ገለጻ ፓርቲው ፅህፈት ቤቱን የማደራጀት ስራ እና በተለያዩ እርከኖች እና ኃላፊነቶች ከሚያዋቅራቸው ኮሜቴዎች ጎን ለጎን የሰከነ ፖለቲካዊ አካሄድ እንዲኖር እንዲሁም የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ፓርቲውን አርበኞች ግንቦት 7ን ጨምሮ ሰባት ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው የመሰረቱት እንደሆነ ይታወቃል።
ራሳቸውን አክሰመው አንድ ፓርቲ ለመመስረት የተሰባሰቡት ፓርቲዎችም ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ የአርበኞች ግንቦት 7፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄና የቀድሞ አንድነት ለፍትህ ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት የነበሩ መሆናቸውን አቶ ናትናኤል ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዱአለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ መሪና ምክትል መሪ በመሆን ተመርጠዋል።
በምርጫው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ 912 ድምፅ በማግኘት የፓርቲው መሪ በመሆን የተመረጡ ሲሆን አቶ አንዱአለም አራጌ ደግሞ የፓርቲው ምክትል መሪ በመሆን ተመርጠዋል። እንደዚሁም አቶ የሸዋስ አሰፋ 722 ደምፅ በማግኘት ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፥ ዶክተር ጫኔ ከበደ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠዋል። ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከምርጫው በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የአዲሱ ፓርቲ ተቀዳሚ ዓላማ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።
የተረጋጋ ዴሞክራሲ እና የተገራ ፖለቲካ መፍጠር ወሳኝ ነው ያሉት የፓርቲው መሪ፥ ገዢው ፓርቲ ሀገርን ለማረጋጋቱ ስራ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል። በዚህ ስራ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ዋስትና ፓርቲም ገዢውን ፓርቲ ያግዛል ብለዋል። በብሄር ለተደራጁ ፓርቲዎች ባስተላለፋት መልእክትም “እኛን እንደ ጠላት አትዩን አትፍሩንም” ብለዋል።
“ሁላችንም የአንድ ሀገር ዜጎች ነን የሃሳብ ልዩነታችንን በሰለጠነ መንገድ በውይይት እንፍታ። ወደ ክልላችን አትምጡ ወደ ወረዳችን አትድረሱ ከሚል ለዚህ ዘመን የማይመጥን ፖለቲካ ውጡ። የህዝቡን አማራጭ ሀሳብ የማግኘት እና የመምረጥ መብት አትንፈጉ” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
አብርሃም ተወልደ