አዲስ አበባ፡- በህብረተሰቡ ዘንድ አሳሳቢ የሆነው አፍላቶክሲን በጤና እና በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል የሚያስችል የምርምር ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት አፍላቶክሲን በአይን የማይታይ፣ በፈንገስ የሚመነጭና በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መርዛማ ህዋስ ሲሆን ከማሳ እስከ ገበታ የሚዘልቅ የእዝ ሰንሰለቱን ተከትሎ ከፍተኛ የጤና እና የኢኮኖሚ ችግር እያስከተለ ይገኛል። ይህንን ችግር ለመከላከልም እየተሰራ ያለው የምርምር ቴክኖሎጂ በ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ስራ ላይ ይውላል። ”የአፍላቶክሲን አደጋ እንደ ህብረተሰቡ እኛንም ያስጨነቀ ነበር “ያሉት ዶክተር ካሳሁን መንግስት ለጉዳዩ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠትና የተለያዩ የዝግጅቶች ከማድረግ አልፎ ወደ ምርመራ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።
አፍላቶክሲን የሚያመጡ እንዲሁም አፍላቶክሲን እንዳይመጣ የሚቆጣጠሩትን ህዋሳትን ከመስክ ጀምሮ የመለየት ስራ መሰራቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ለወደፊት ደግሞ እንደባዮሎጂካል ኮንትሮል የሚያገለግሉ 50 የሚሆኑ ጥቃቅን ነብሳትን (ማይክሮብስ) ለመለየት ተችሏል። እነዚህ ነገሮች ለባዮሎጂካል ቁጥጥር ብቁ ናቸው ወይ? በሚል የተለያዩ ጥናቶች ከተ ጠኑና በሳይንስ ከተረጋገጠ በኋላ የሚለቀቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ በሀገራችን አፈር ውስጥ ከሰብል ጋር ያሉ የፈንገስ ዝርያዎች ሲሆኑ መርዝ የሚያመነጨውን አፍላቶክሲን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ናቸው።
አፍላቶክሲንን ከመስክ ጀምሮ ለመቆጣጠር መርዙን የሚመጡ ማዕድናት እና ቴክኖሎጂ ለማውጣትም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው አሁን ማዕድኑን የመለየትና ምን ያክል መምጠጥ ይችላል የሚለው ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸ ዋል። ዶክተር ካሳሁን እንዳሉት አፍላቶክሲን በአይን የማይታይ ስለሆነ በሴንሰር የመለየት ስራ በተለያዩ ተመራማሪዎች እየተሰራ ነው። የተለያየ ኬሚካል ውህድ ያላቸውን ምግቦች በአፍላቶክሲን የሚጠረጠሩ ከሆነ እነሱን በማጠብና በመዘፍዘፍ የአፍላቶክሲኑን መጠን የመቀነስ ተጨማሪ ስራዎችም በመሰራት ላይ ናቸው። የዚህ ሁሉ ጥናት ቴክኖሎጂ በቀጣይ ስራ ላይ የሚውል መሆኑን ጠቅሰው በዋናነት ግን መሰራት ያለበት በማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና ላይ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ አፍላቶክሲንን ለመከላከል ሰብል ሲሰበሰብና ሲቀመጥ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚረዳ የስልጠና ማንዋል ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱን አስረድተዋል። “ሰዎች ለትርፍ ወይም በተለያየ ምክንያት በበርበሬ ዛላ ላይ ውሃ ይጨምራሉ” ያሉት ዶክተር ካሳሁን ይሄ የአፍላቶክሲኑን መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል። በርበሬ፣ ለውዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላ… ሲቀመጡ በቂ አየር እንዲኖር ማድረግና ለፈንገስ እድገት የሚረዱ እርጥበቶችን መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል። በሰብሎች ክምችትና በማጓጓዝ ወቅት ሊደረጉ የሚገባው ጥንቃቄ በስልጠናው ማንዋል ውስጥ የተካተተ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ከማሳ እስከ ገበታ አፍላቶክሲንን በተለያየ ደረጃ መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መሆኑን ገልጸዋል። እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ አፍላቶክሲን በቅንጣት መልክ በሰብሎች ፣ በሰብሎች እና በእንስሳት ተዋጽኦ ላይ ይገኛል። ይሄ በብዛት ወደ ሰውነት ሲገባ በሰውነት አካል ላይ የጤና እክል የሚያጋጥም ሲሆን ችግሩ በብዛት ጉዳት የሚያደርሰው በጉበት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል። አፍላቶክሲን በወተት ላይ በዋናነት የሚከሰተው ከእንስሳቱ መኖ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ የእንስሳት መኖ ደግሞ ከሰብል ጋር የተገናኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመስክ የእንስሳትን መኖ መቆጣጠር ከተቻለ በአፍላቶክሲን እንዳይበከል ያደርጋል፤ ሌላው ደግሞ መኖውን በመጣጭ ማዕድኖች በማሸት ያለውን የአፍላቶክሲን መጠን መቀነስ የሚቻል መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይነት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት አፍላቶክሲንን በቤት ውስጥ መቆጣጠር የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሰራ ሲሆን ግቡም በቤት ወይም በኩባንያ ደረጃ የአፍላቶክሲንን ደረጃ መቀነስ ነው ።
“አሁን ባለው ሂደት ምርምሩ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ሆኖም ግን በሚፈለገው ደረጃ መሄድ እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ሁሉም የምርምር ስራ የሚሰራው በኢንስቲትዩቱ ባሉ ቤተሙከራዎች ባለመሆኑና ለሌሎች ተቋማት ከፍሎ ለማሰራትም የመንግስት የግዥ ሂደት መከተል በምርምር ስራው ላይ መጓተት እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል። ያም ሆኖ እስከ 2012 በጀት ዓመት መጨረሻ ቴክኖሎጂዎች ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ አለ። የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ሰኔ 2008 ዓ.ም የተቋቋመ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
አልማዝ አያሌው