“ልዩነትን በማጥበብ የአንድነትን ድልድይ ለመገንባት ይሰራል” – አቶ አህመድ ሃሰን የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
ከሚሴ፡- በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አካባቢ የተፈጠረው ችግር ሁሉንም ያሳዘነ ነው:: ችግሩ ዳግም እንዳይደገም ራስን ለሰላምና ለፍቅር አሳልፎ መስጠት ትልቁ መፍትሄ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን ተናገሩ።
ትናንት በከሚሴ አባገዳ አዳራሽ በተደረገው በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሸዋ አጎራባች ወረዳዎችና ህዝቦች የሰላምና የእህትማማችነት ጉባኤ ላይ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን እንደተናገሩት፤ በአካባቢው የተፈጠረው ችግር የዜጎችን ህይወት የቀጠፈና በርካታ ንብረትን ያወደመ በመሆኑ ሁሉንም ያሳዘነ ነው። ይሁንና ችግሩን እያሰቡ ከመብሰልሰል ይልቅ ለፍቅርና ለሰላም እራሱን በመስጠት በይቅርታና ችግሩ እንዳይደገም መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
‹‹ኢትዮጵያ በመቻቻልና በመተሳሰብ አቻ የሌላት ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ተቻችለው በሰላም የሚኖሩባት ቅድስትና ታላቅ ሀገር ነበረች። ሆኖም ባለፉት ዓመታት የተሰራውን መልካም የልማት ስራን ያህል የጎሰኝነት ትርክት በተለያየ መልኩ መሰራቱ ይህንን መልካም ገፅታ በሚያበላሽ መልኩ በህዝቦች መካከል መጠራጠርንና መከፋፈልን ፈጥሮ አልፏል። ለዚህም በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደርና በሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች አካባቢዎች የነበረው ችግር አንድ ማሳያ ነው። ዶክተር አምባቸው ይህን መሰል ችግር በመፈጠሩና በደረሰው ጉዳት ሁሉም ያዘነ መሆንኑ ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ችግሩን እያሰቡ ከመብሰልሰል ይልቅ በይቅርታ ጉዳቱ ዳግም ችግር እንዳይፈጠር መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል። ዶክተር አምባቸው አክለውም ክረምት አንድ ጊዜ ቤትን በጎርፍ አንገላቶ ካለፈ በኋላ ቤት አይሰራለትም። ይልቁን በቀጣዩ ክረምት ድጋሚ ላለመጎዳት ዝግጅት ይደረጋል። በአካባቢው ለተፈጠረው ችግርም እንደዚሁ መስራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በችግሩ ወጥተው እስኪገቡ የሚናፈቁ ህፃናት እንደወጡ ቀርተ ዋል። እናቶች፣ አባቶችና አቅመ ደካሞች በማያውቁት ጉዳይ ተጎድተዋል።
ስለዚህም ሁሉም ብቻውን ይህንን እያሰበ ከመብሰልሰልና ከአቅም በላይ ለሆነ ችግር ከመጋለጥ ይልቅ እራስን ለፍቅር አሳልፎ በመስጠት በይቅርታ ችግሩ ድጋሚ እንዳይፈጠር መስራት ይገባል። ይህንን ማድረግ ለግል ሳይሆን ሀገርን፣ አረጋውያንን፣ እናቶችንና ህፃናትን የመታደግ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ “ችግሮች እንዳይፈጠሩ… የሆኑት አቶ አህመድ ሃሰን በበኩላቸው የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች አንድ የዘር ምንጭና የጋራ ስነልቦናና ታሪክ ያላቸው ናቸው።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርዋ ከሚሴ የሁለቱ ህዝቦች የአብሮነት መገለጫ ናት። ህዝቦቿ ሀዘንና ደስታን አብረው ያሳለፉ ችግሮቻቸውንም በጋራ መክረው የተወጡ ናቸው። በቅርቡ በአካባቢው የተፈጠው ችግር መፈጠር የማይገባው ቢሆንም በቀጣይ እንዳይፈጠር መስራት እንደሚገባ ትምህርት ጥሎ ያለፈ ነው። አጥፊዎችንም ለህግ ለማቅረብ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስና የተጎዱ አካላትን ለመካስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና ልዩነትን በማጥበብ የአንድነትን ድልድይ ለመገንባት ይሰራል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2011
በወንደሰን ሽመልስ