ፖሊስ ለምን እንፈራለን?

የሰለጠነ ተቋምን የሚፈጥረው የሰለጠነ ዜጋ ነው። እንዳለመታደል ሆኖ የሰለጠነ ዜጋም የሰለጠነ ተቋምም የለንም። የሰለጠነ ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ ብልሹ ነገሮች ይታያሉ። አገልግሎቱን የሚሰጡ አገልጋዮችም ሆኑ ተገልጋዮች ላይ ያልሰለጠኑ ምልክቶች ይታያሉ።

ነገሩን ያስታወሰኝ የሰሞኑ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ነው። የፈተና ሥርቆትን ለማስቀረት (ይህም በብልሹ ዜጋና ብልሹ ተቋም የመጣ ችግር ነው) ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ ወስዶ መፈተን አስገዳጅ ሆነ። ይህ አሰራር ባለፈው ዓመት የተጀመረ ሲሆን እነሆ ዘንድሮም በዚያው ቀጠለ። የትምህርት ነገር የአንዲትን ሀገር ዕጣ ፋንታ የሚወስን ነውና የትኛውም ርምጃ መወሰድ ስላለበት የትምህርት ሚኒስቴር ቆራጥ ውሳኔ የሚበረታታ ነው።

በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ነገሮች ግን የሀገራችንን የሥልጣኔ ደረጃ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። ተማሪዎች ወደሚፈተኑበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲገቡ (በተለይ ባለፈው ዓመት) ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ኃይል ይታያል። እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው። በወቅቱ ‹‹ይሄ ነገር በተማሪዎች ሥነ ልቦና ላይ ምን ይፈጥራል?›› የሚሉ ክርክሮች ነበሩ። ነገሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነ ብዙ አከራካሪ ነገሮች እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ያ እንዲሆን ያስገደደው ግን የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ነው፤ አለመሰልጠናችን ነው።

እነሆ ዘንድሮም ይሄ አሰራር ቀጠለ። ተማሪዎች አሁንም በአካባቢያቸው የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎችን እያዩ ነው የሚገቡት። በሰለጠነው ዓለም፣ እንኳን ትምህርት ቤት አካባቢ ከተማ ውስጥ ራሱ ፖሊስ የጦር መሳሪያ አይዝም፤ አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ነው ከመጋዘን የሚወጣው። እኛ ግን ይህን አልታደልንም። እንደ ዜጋ ይህ ሊቆጨን ይገባል።

 እዚያ ሥልጣኔ ላይ እስከምንደርስ ግን አስገዳጅ መሆኑ አልቀረም። እዚህ ላይ ክርክር ይነሳል። በአንድ በኩል፤ ተማሪዎች ወደ ፈተና እየገቡ የታጠቁ የፀጥታ አካላትን ሲያዩ ምን አልባት ‹‹ምን ይፈጠር ይሆን?›› የሚል ጭንቀት ይፈጠርባቸው ይሆናል። ልጆች ናቸውና ለደህንነት ሲባል ብቻ የተያዘ መሆኑን ቶሎ አይረዱ ይሆናል።

በሌላ በኩል ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ደህንነትና ነፃነት ሊሰማቸው ይችላል። ምክንያቱም እነዚያ ፖሊሶች በዙሪያቸው የቆሙት ለተማሪዎች ደህንነት ነው። ደህንነት ሲባል የግድ ከሽብር ጋር ብቻ አይደለም፤ ድንገተኛ አደጋ (የተፈጥሮም ሆነ የትራፊክ አደጋ) ቢያጋጥም ከማንምና ከምንም በፊት ቀድሞ የሚገኘው የፀጥታ አካል ነው። ስለዚህ በብዙ ምክንያቶች በፖሊስ መታጀባቸው ትልቅ ደህንነትና ነፃነት እንዲሰማቸው ያደርጋል።

በሌላ በኩል በሀገራቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታም ያውቃሉ። ወቅቱ የመንደር ሽፍቶች የበዙበት ነው። እነዚህ የመንደር ሽፍቶች ፖሊስ ባለበት አካባቢ ዝር አይሉም። ይህን ደግሞ ልጆች ያውቃሉ። ስለዚህ በፖሊስ መታጀባቸው ከእነዚህ ሁሉ ስጋቶች ነፃ ያደርጋቸዋል።

በዚሁ እግረ መንገድ ግን ስለ ፖሊስና ሕብረተሰብ (ፕሮግራሙን ማለቴ አይደለም) እንተዛዘብ። ይህን ትዝብት ጥሩ ለማድረግ በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ገጠመኝ ማሳያ ይሆነኛል።

ለአንድ የሞባይል ሽያጭና ጥገና ቤት የሚጠገን ስልክ ሰጥቶ እስከሚሰራ ድረስ እዚያው አካባቢ ዘወር ዘወር እያለ ነው። ፖሊሶቹ ምን እንደመሰላቸው አላውቅም (ክስተቶቹን ራሱ ነው የተረከልኝ) አናገሩት። ‹‹ምንድነው?›› ሲላቸው፤ ለረጅም ደቂቃዎች እዚህ አካባቢ ቆመሃል፤ ምን ለማድረግ አስበህ ነው? ይሉታል። እሱም ሞባይል እያስጠገነ መሆኑን ሲነግራቸው አላመኑትም። ሞባይል ቤቱ ጋ ሄደው ስልክ እያሰራ መሆኑን አረጋገጡ።

 በእነዚህ እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ መታወቂያ ጠይቀውት የመንጃ ፈቃድ አሳይቷል። ሞባይል እያስጠገነ መሆኑን ሲያረጋግጡ ‹‹ተገላገልኩ›› ብሎ ነበር። አረጋግጠው እንደጨረሱ ‹‹መንጃ ፈቃድ መታወቂያ አይሆንም›› አለው መታወቂያውን የያዘው ፖሊስ። ይሄኔ ነው የልጁ ብልግና ነጥሮ የወጣው። ‹‹መንጃ ፈቃድ መታወቂያ አይሆንም›› ሲለው፤ ፖሊሱን አጸያፊ ስድብ ተሳደበ። ይሄኔ ፖሊሱ ልጁን በጥፊ መታው። ሌሎች ፖሊሶች መጡ። ተይዞ ጣቢያ ሄደ። እዚያ የሆነውን ሁሉ ተናግሮ የፖሊሶች አለቃ ነገሩን ቀለል አድርጎ ለቀቀው። ልጁ ደግሞ ‹‹ፖሊስ ጣቢያ ስደርስ ያላልኩትንና ያላደረኩትን ነገር እንዳደረኩ አድርገው ዋሽተዋል›› በሚል ካልከሰስኩ አለ። በመጨረሻም ጥፋተኝነቱን ነግሬው ነገሩ ተቋጨ።

ይህ የቅርብ ጊዜ ገጠመኝ እና እኔም ክስተቱን በቅርበት የሰማሁት ስለሆነ እንጂ እንዲህ አይነት አግባብነት የሌላቸው የፖሊስና ግለሰቦች ግጭቶች አሉ።

በመጀመሪያ የልጁን አለመሰልጠን ልብ በሉ። ፖሊስ አጠራጣሪ ነው ብሎ የገመተውን ነገር ማረጋገጥ ሥራው ነው። ፖሊሰ ፀሐይና ዝናብ የሚፈራረቅበት የሕብረተሰብን ደህንነት ለማረጋገጥ ነው። ይህን የሚያደርገው ደግሞ ነገሮች ከሆኑ በኋላ ብቻ ሳይሆን ያጠራጥራል ያለውን ነገር ሁሉ በመጠየቅ ነው። እንዲያውም በብዛት የሚወቀሱት እኮ አንድ ነገር ከተፈጸመ በኋላ ነው የሚደርሱ በሚል ነው። የልጁ አላዋቂነት የፖሊስ ሥራ ይሄ መሆኑን አለማስተዋሉ ነው። በራሱ ንጽህና እርግጠኛ ቢሆንም ለምን ተጠረጠርኩ ብሎ መደንፋት አለመሰልጠን ነው።

ሲቀጥል፤ ፖሊሶች ስህተት ቢሆኑ እንኳን በንግግርና በውይይት ስህተታቸውን መንገር እንጂ ‹‹ሌባ ቢሆን ኖሮ አትይዙትም ነበር›› እያሉ እልህ ማስገባት አላዋቂነት ነው። ከዚህም ሲያልፍ በሙያና ብቃታቸው ላይ፣ በትምህርት ደረጃቸው ላይ (ለዚያውም ሳያውቀው) ፀያፍ ስድብ መሳደብ አለመሰልጠን ነው።

የአንዳንድ ፖሊሶችም ነገር ያስተዛዝባል። ልጁ የነገረኝን አምኜ ሳይሆን ሌሎች እንዲህ አይነት ገጠመኞችም በብዛት ስለሚሰሙ ነው። ሲደበድቡ ስለማይ ነው። የተጠራጠሩትን ሰው በሥነ ሥርዓት ማናገር እየተቻለ ከስድብና ግልምጫ የሚጀምሩ አሉ። ከማመናጨቅና ከማደነባበር የሚጀምሩ አሉ። ልክ እንደ ድሮ ወላጆች የልጅ አቀጣጥ፤ ሲናገር ‹‹ዝም በል!››፣ ዝም ሲል ‹‹ተናገር!›› አይነት ማደነባበር አለ።

የነበረበት አካባቢ ለፀጥታ የሚያሰጋ ከሆነ ‹‹ከዚህ ዘወር በል›› ማለት ይቻላል። የሚጠራጠሩት ነገር ካለ መፈተሽም ያለ ነው። በየትኛውም ቦታ ላይ እንደ መታወቂያ የሚያገለግልን መንጃ ፈቃድ (ማንነትን እስከገለጸ ድረስ) አይሆንም ማለት ልክ አይደለም፤ ምክንያቱም ያ ቦታ ያን ያህል የፀጥታ ስጋት ያለበት አይደለም። ወጭ ወራጅ የሚመላለስበት ማንኛውም መስመር ነው። ስልክ እያሰራ መሆኑን ካረጋገጡ ‹‹ለወደፊቱ መታወቂያ ሊኖርህ ይገባል›› ብሎ ቀለል አድርጎ ማሰናበት እየተቻለ በቀላል ነገር እልህ መጋባት ከፖሊስ ሥነ ምግባርና አስተዋይነት ጋር አብሮ አይሄድም።

‹‹ፖሊስ ለምን እንፈራለን?›› ከተባለ በእንዲህ አይነት ጥቃቅን ምክንያቶችና በአንዳንድ ከፖሊስ ሥነ ምግባር ውጭ በሚሰሩ ፖሊሶች ምክንያት ነው። ሲደበድቡ፣ ሲገፈታትሩ፣ ሲገላምጡ… የሚያይ ሕጻን ልጅ ምናልባትም የፖሊስ ሥራ ይህ ሊመስለው ይችላል። ፖሊሶች ደግሞ ያንን የሚያደርጉት (ድርጊቱ ትክክል ባይሆንም) አንዳንድ ግለሰቦች አለመሰልጠን ብቻ ሳይሆን በጣም መረን የለቀቀ ነውረኞች ስለሚሆኑ ነው።

በአጠቃላይ፤ የሰለጠነ ዜጋ ሲፈጠር የሰለጠነ ተቋም ይኖረናል። ፖሊስ ስናይ ደህንነትና ነፃነት እንጂ ፍርሃትና ጭንቀት ሊሰማን አይገባም!

 ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 24/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *