የጋዜጠኛዋ ሠረገላ

ባለሁለት መዘውር የተዋበ የሕይወት ሠረገላ፤ በሁለት ግዙፍ ባለጋሜ ፈረሶች እየተገፋ መጥቶ ከመዓዛ ፊት ቆመ። ያኔ! እንቁዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የሕልም ጉዞዋን የጀመረች እለት። መዓዛ ሌሎችን መጠየቅን እንጂ እምብዛም ስለራሷ መናገርም ሆነ መጠየቅን የምትወድ አይደለችም። በኩራት ሳይሆን በታላቅነት። ታዲያ እኛም ዛሬ የጠያቂዋን ባሕረ መዝገብ አገላብጠንና ቆፍረን ያገኘነውን ወርቃማውን እሷነትዋን በብዕራችን ከትበን በዓምዳችን ልናስነብባችሁ ወደናል።

መዓዛ ብሩ ከዛሬ 63 አመት በፊት 1951 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደች። መዓዛ በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ቢሆንም የጣፋጩ የልጅነት ትዝታዎቿ ሐረግ የሚመዘዘው ግን ከወደ ሐረር ነው። ደግሞም አባቷ አቶ ብሩ በወቅቱ የታወቁና የተዋጣላቸው ሲራራ ነጋዴ ነበሩ። ከዚህም የተነሳ መዓዛ በተወለደች ገና በሦስት ዓመቷ መላው ቤተሰቡ አዲስ አበባን ለቆ ወደ ሐረር ሒርና ከተማ ገባ። ልጅነትና መዓዛ፣ መዓዛና ሒርና የተለየ ትዝታና መሳሳብ አላቸው።

የእርሷ የልጅነት ግዜ ሴቶችና ትምህርት በቅጡ የማይተዋወቁበት ነበር። የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወላጅም ልጁን ለወግ ማዕረግና ለቁም ነገር የሚያበቃው ልጁን አስተምሮ ሳይሆን ድሮ በትዳር በማስተሳሰር ነበር። የመዓዛ ወላጅ አባት አቶ ብሩ ግን እንደግዜው አልነበሩም። ልጆቻቸው ሁሉ እንዲማሩላቸውና የእውቀትን ፈለግ እንዲከተሉላቸው ይፈልጋሉ።

እሳቸውም ቢሆን የታወቁ ነጋዴ ብቻ ሳይሆኑ አዳዲስ መጽሐፍትንና የወቅቱን ጋዜጦች በየእለቱ እያደኑ የሚያነቡ ሰው ነበሩ። ለዚህም ነው የእወቀት ብርሃንን ኃያልነት ጠንቅቀው የሚያውቁት። ለዛም ነው ልጃቸውን መዓዛን ገና ትንሽ ልጅ ሳለች እጇን ይዘው ወደ ትምህርት ቤት የወሰዷት።

ስለ መዓዛ እያወሩ ስለ አባቷ አለማንሳት የሙሉ ማንነቷን ገሚስ አካል ቆርሶ እንደመጣል ነው። ምክንያቱም የዛሬውን ማንነቷና እርሷ እራሱ ሳታውቀው ረቂቅ በሆነ መንገድ ዛሬዋን ሠርተውት ነበር። እንዲህ ሁኚ ብለው ባይነግሯትም የልጃቸውን የወደፊት የሕይወት መስመር ግን ከእግሯ በታች አስምረውት ነበር። ጋዜጠኛ የመሆን ሕልም ባይኖራትም፤ አባቷ ግን አንዲት ጎበዝ ጋዜጠኛን በመሥራት ላይ ነበሩ። ይህን ታዲያ እርሷም አታውቅም፤ እርሳቸውም አይነገሯትም። ነገር ግን ከሠረገላዋ ላይ የነበረው የትዝታ መስታወቷ ዛሬ ላይ ቁልጭ አድርጎ ያሳያታል።

የመዓዛ አባት በየእለቱ ለሥራ ወጥተው ወደ ቤታቸው በተመለሱ ቁጥር ከእጃቸው ላይ መጽሐፍ አሊያም ጋዜጣ አይታጣም። እየገዙ ከሚያመጡላት የተረት ተረት መጽሐፍት በተጨማሪ ጋዜጦቹን ካነበቡ በኋላ ልጃቸውን መዓዛን ጠርተው ይሰጧታል። በወቅቱ እንዲህ ነበር የሚሏት.. ‹‹የእጅ ጽሑፍሽ ያማረ ይሆን ዘንድ ከጋዜጣው፣ ከዚህች ገጽ ላይ ያለችውን ጽሑፍ በወረቀት ገልብጠሽ አምጪ›› የሚል ትዕዛዝ ይሰጧታል። መዓዛም የአባቷን ትዕዛዝ እየተከተለች አዘውትራ ጽሑፉን በወረቀት ላይ እያሰፈረች በመጣች ቁጥር ጋዜጣውን የማንበብ ልምዷ ከእለት እለት እየዳበረ መጣ።

አዲስ ዘመን ጋዜጣና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ለመዓዛ ከአባቷ የተበረከቱ የእድሜ ዘመን ስጦታዎች ነበሩ። እነዚህን ጋዜጦች ሳታነብ ውላ አታድርም ነበር። ብዙ ነገሮችን የማወቅና የመፈለግ አይኖችን ከልብና አዕምሮዋ ውስጥ አሰረፁባት። ጋዜጠኛ ማን እንደሆነ ጋዜጠኝነትም ምን እንደሆነ ፈጽሞ አይገባትም ግን ደግሞ ሳታውቀው በደመነብስ ጋዜጠኝነት ከውስጧ ላይ ረብቦ ነበር። ለዓመታትም ከሕይወቷ ማማ ላይ ቤቱን በመሥራት ላይ ነበር። የተዋበ ሠረገላም ሠርቶና ልጓሙን በሁለት ያማሩ ፈረሶች ላይ አድርጎ ትንሽየዋን ልጅ መዓዛን አስቀመጣት።

በሥነ ጽሑፍና በጋዜጠኝነት ፈረስ… እንግዲህ ነገሩ ፈረስ ያደርሳል ነው። የመዓዛ ትኩረትና ሃሳብ ከኪነ ጥበቡ ፈረስ ላይ ቢሆንም የሕይወት ሠረገላዋን ጉዞ ያለምንም ድካም ዳገትና ቁልቁለቱን እየወጣና እየወረደ ሲመራ የነበረው ግን፣ ምንም ያልተመለከተችው ጉልበታሙ የጋዜጠኝነት ፈረስ ነበር። በአንድ ሠረገላ ሁለት ፈረሶች..ጋዜጠኝነትና ኪነ ጥበብ። ሁለቱም በባሕሪም ሆነ በግብር ተመሳስሎ ያላቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ነገር ግን የሠረገላውን ቁልፍ ቦታ ለመስጠት ዘውድ አሊያም ጎፈር ማለት አይቀሬ ነው።

መዓዛ ብሩና ቤተሰቧ ከስድስት ዓመታት የሐረር ቆይታ በኋላ በዘጠኝ ዓመቷ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ገባ። ከዚህ በኋላ መዓዛ የተሻለና የተረጋጋ የትምህርት ሕይወት እንዲኖራት በማሰብ አባቷ ወደ ቅድስተ ማሪያም የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቧት። ይህ ግን በቤተሰቦችዋ ተከባ በጣም ከምትወደው አባትዋ ጥላ ስር ለኖረችው መዓዛ በተለይም ደግሞ የመጀመሪያዎቹ አካባቢ በእጅጉን ከባድ ነበር። ከሞቀበት የአባቷ ቤት ወጥታ የገባችው ምንም ወደ ማታውቀው አዲስ ማኅበረሰብና እንግዳ ወደሆነ የኑሮ ዘዬ ነበርና ብቸኝነት እየዋጣት ድብርቱ ይጫጫናት ጀመር።

ሁሉም አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ቀርባ የምትጫወተው ሰው ባለመኖሩ አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው በተመስጦ ከራሷ ጋር በማውራትና ልዩ ልዩ መጽሐፍትን በማንበብ ሆነ። ቀናቶች እየገፉ ሲሄዱም የመጽሐፉ ዓለም ምቾትና ነፃነትን እየሰጣት መጣ። መጽሐፍቱን ጓደኞቿ፣ ጨዋታዋንም ንባብ አደረገችው። በአዳሪ ትምህርት ቤቱ በነበራት ቆይታ የኋላ ኋላ ማኅበራዊ ኑሮዋን እየመሠረተች በዚያ ያለው ሕይወትም እየቆየ እንደ ወይን እየጣፈጠላት ሄደ።

የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ በ1971 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ቋንቋ ጥናት ተቋም ውስጥ በሥነ -ልሣን ትምህርት ክፍል ተመደበች። መዓዛ እዚህ ስትመደብ ፍላጎቷ አልነበረምና ነገሩ አልጥም አልዋጥ አላት። ፍላጎቷ ባሟላም ግን አንዲት መካሻ የሆነቻት ነገር ነበረቻት። ማር ለሚወድ ሰው ማር የነካው ማንኪያም መድኃኒቱ ነውና በተመደበችበት ዘርፍ እንደሁለተኛ የምትወስደው የውጭ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ በመሆኑ በትንሹም ቢሆን የሥነ ጽሑፍን ማር እንደምትቀምስ ስታውቅ ግን ተጽናናች።

ታዲያ እዚህ ጋር ጋዜጠኝነትና መዓዛ ብሩ መቼና እንዴት ተዋወቁ? የሚለውን ማወቁ ተገቢ ነው። ጊዜው መዓዛ ብሩ የሦስተኛ ዓመት ወይንም የመጨረሻ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረችበት ነበር። መንበረ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትርና ኪነ ጥበባት ክፍል ተማሪ ስትሆን የመዓዛ ጓደኛ እንዲሁም የመኝታ ክፍሏ ደባልም ጭምር ነበረች። ተፈሪ ዓለሙና የቲያትር አዘጋጅ የሆነው አስታጥቄ ደግሞ ከመዓዛ ጓደኛ መንበረ ጋር በቲያትር ትምህርት ቤቱ ውስጥ አብረው ይማራሉ።

ታዲያ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አንድ አጋጣሚ ተከሰተ። መንበረና ጓደኞችዋ እነ ተፈሪ አለሙ አንድ የሬዲዮ ድራማ ዝግጅት ነበራቸውና ለድምጽ ቀረጻ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው ለመሄድ ሁለቱ ወንዶች መንበረ ወደምትገኝበት የተማሪዎች መኝታ ክፍል በመጠጋት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጣራሉ። ድምፁን የሰማችው መዓዛም በሩን ከፍታ ብቅ በማለት የመንበረን አለመኖር ትነግራቸዋለች። የፈለጓት በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ መዝናኛ ላይ ለሚያቀርቡት ድራማ ወደዚያው ለመጓዝ ነበር። የቀጠሮው ሰዓት እየተቃረበ በመሆኑ ግራ የተጋቡት እነ ተፈሪ ዓለሙም በመንበረ ቦታ አብራቸው እንድትሄድ መዓዛን ያግባቡዋት ጀመሩ። እርሷ ግን ከነበረው የትምህርት ውጥረትና በሌሎች ምክንያቶች አልሄድም ስትል መለሰችላቸው።

ከዚያ በኋላ ግን እንደምንም አግባብተው ይዘዋት ሄዱ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ኃላፊ ለነበሩት ታደሰ ሙሉነህ ለሙከራ ያህል የመዓዛ ድምፅ ተቀድቶ ቀረበላቸው። ድምጿን ደጋግመው ደጋግመው አደመጡት። የሚፈልጉት አይነት ማራኪ ድምፅ ነበር። የተለየ እድል ነበር፤ በሌሎች የጣቢያው ፕሮግራሞች ላይም ሥራዎቿን እንድታቀርብ በራቸውን ክፍት አደረጉላት። የተቀመጠችበት የሕይወት ሠረገላ ሳታውቅ በድንገት እየገሰገሰ ከኢትዮጵያ ራዲዮ ቅጥር ግቢ ዘልቆ ገባ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መዓዛና ሬዲዮ እንዲሁም መዓዛና ጋዜጠኝነት ትስስራቸው የጠበቀ ሆነ። ሬዲዮ ጣቢያው ያመቻቸላትን እድል በመጠቀምም ልዩ ልዩ የሥነ-ጽሑፍና ሥራዎችንና ጭውውቶችንም በግልና በቡድን በማዘጋጀት ተወዳጅነትን አተረፈች። ካቀረበቻቸው ድራማዎች መሐልም የራሷ የፈጠራ ሥራ የነበረው “የአዲሱ ቤተሰብ” የተሰኘው ሥራዋ በኢትዮጵያ ሬዲዮ በተወዳጅነቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተከታትሎታል።

የመዓዛ ሠረገላ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ደጅ በዝግታ ወጥቶ ለ 13 ዓመታት ያህል በዚያው ሳይመለስ የቀረበት ሌላ የሕይወት ምዕራፍ ነበራት። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኃላ ያመራችው ወደ ራዲዮ ጣቢያው ሳይሆን ወደ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ነበር። በዚያም የመርሐ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢ ሆና መሥራት ጀመረች። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ከዚያ ወጥታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርሐዊ ጋዜጣ አዘጋጅ በመሆን መሥራት ቀጠለች። በዚያም እምብዛም ሳትቆይ ለቃ ከወጣች በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥራ ለ4 ዓመታት ያህል የፕሬስና መረጃ ዋና ዳይሬክተር ሆና አገልግላለች።

ዳግም ወደ ሬዲዮ እንድትመለስ ያደረጋትን ምክንያት ያገኘችውም እዚህ ነበር። ቀደም ሲል በሬዲዮ የሚያውቋት ሰዎች ‹‹አንቺ እኮ የተፈጠርሽው ለሬዲዮ እንጂ ለቢሮ ሥራ አትሆኚም›› ሲሉ በተደጋጋሚ ይነግሯታል። ይሄኔ አንድ ነገር ብልጭ አለላት። ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ በመመለስ በኤፍ ኤም 97.1 የአየር ሰዓት ወስዳ ጨዋታ የተሰኘ ፕሮግራም ከተፈሪ ዓለሙ ጋር በጋራ በመሆን ማቅረብ ጀመሩ።

ከዓመታት በኋላ መዓዛ ብሩ የግልዋን የሬዲዮ ጣቢያ የምታቋቁመበትን ሌላ ወርቃማ እድል አገኘች። 1996 ዓ.ም መንግሥት ለሁለት የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ እንደሚሰጥ ይፋ አደረገ። ይህን የሰሙ የቅርብ ወዳጆችዋም ለምን ፈቃድ አትጠይቂም ሲሉ ነገሯት። እርስዋ ግን ፈጽሞ የራሴ የሆነ ሚዲያ ይኖረኛል ብላ አስባበት ስለማታውቅ ሃሳባቸውን ለመቀበል ከበዳት። ጉትጎታው ሲበዛባት ግን ስለጉዳዩ ማጤን ጀመረች። በኋላም ብዙ አውጥታና አውርዳ ፈቃድ መጠየቅ እንዳለባት ወሰነች።

ለእርሷ ወደ ግል ሬዲዮ ጣቢያ መግባት ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ብቻውን ከነገሰው የኢትዮጵያ ራዲዮ ጋር መወዳደሩ በእጅጉ አስፈሪ ነበር። በጉዳዩ ፈራ ተባ ስትል ሰንብታለች። በስተመጨረሻም ተሳክቶላት መስከረም 25 ቀን 1997 ዓ.ም ‹‹ሸገር›› የተሰኘውን የመጀመሪያውን የግል የራዲዮ ጣቢያ በመክፈት ስርጭት ጀመረ። መዓዛ የግልዋን የደስታ ወሰን የሰበረችበት እለት ይሄው ስለመሆኑ ትናገራለች። የራዲዮ ጣቢያዋም ይዞ በቀረበው ለየት ያለ አቀራረብ ተደማጭነትን በማትረፍ ስኬታማ የሚባሉ ጊዜያትን በማሳለፍ ላይ ይገኛል።

በቃለ መጠይቆቿ የልብ አውቃ ናት ይሏታል። ቃለ መጠይቆቿ ከራዲዮ ሞገድ ላይ እየተወነጨፉ ከወደ ጆሮዋቸው የዘለቀ ሁሉ ይህን ይመሰክራሉ። መዓዛ ብሩ በጋዜጠኝነት ሙያዋ በብዙዎች ዘንድ የምትደነቅበት አንደኛው ችሎታዋ ብዙ ጊዜ የሚወስዱና እልፍ ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን በአጭር የቃላት ውቅር ገንብታ የተዋበና ግልጽ እይታ እንዲኖረው አድርጋ ማቅረብ መቻሏ ነው ሲሉም ብዙዎች ይመሰክሩላታል።

መዓዛ ብሩ በዚህ የጋዜጠኝነት ሠረገላ እንደተቀመጠች ለ30 ዓመታት ያህል በሜዳ ሸንተረሩ፣ በመውጣትና መውረድ ስትጓዝ ዛሬ ካለችበት የስኬት ማማ ላይ ደርሳለች። በስኬት ላይ ስኬትን የደረበላት ሌላኛው የሰሞንኛ ጉዳይ ደግሞ ከቀናት በፊት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በጥበብና በጋዜጠኝነት ወርቃማ ሠረገላ ታጅባ ወርቃማውን የክብር ዶክትሬት አጎናጽፎዋታል። ይህ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በእውነትም በጋዜጠኝነት ሕይወቷ ላበረከተችው አስተዋፅዖ የሚገባት ስለመሆኑ ሁሉንም በጋራ ያስማማል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *