የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው።
ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ተግባር ነው። ይህ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ሌላኛው ተግባር ነው።
መንግሥታትን ከከፍተኛ የገንዘብ ወጪ በማዳን የሀገራትን ኢኮኖሚ ማጎልበትም ከሚሰጠው ፋይዳ ጋር ይደመራል። በዚህ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በበርካታ ሚሊዮን ብር ሊሰራ የማይችል ተግባር በየዓመቱ ሲከናወን ይስተዋላል።
የበጎ አድራጎት ሥራ በእርስ በእርስ ትስስር አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚሰጠው ማህበራዊ መስተጋብር የጎላ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር)የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከግንዛቤ በማስገባት በተለይ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ መልካም ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ እውነታ ነው።
ይህንኑ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ዘርፎች ለመሳተፍ ችለዋል። አንዳንዶቹ በአካባቢያቸው ሌሎቹ ደግሞ ከአካባቢያቸው ርቀው ድንበር ዘለል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በተለይም ወጣቶች ከተወለዱበትና ከአደጉበት አካባቢ ርቀው በመሄድ የሚያደርጉት ድንበር ተሸጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ወጣቶቹ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች በመዘዋወር እግረ መንገዳቸውን አንድነታቸውንና የባህል እሴቶቻቸውን የሚያጋሩበትና የሚያጎለብቱበት ስለሆነ በዚህ ሁኔታ ቢሳተፉ መልካም ነው በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ በአፅንዖት የሚወሰድ ከመሆኑም በሻገር ከዚህ መልካም ተግባር ጎን ለጎን ቋንቋ፣ ባህል፣ የአሰራር ዘይቤ እንዲሁም የተለያዩ የባህል እሴቶችንና አንድነትን የሚያጠናከር አንዱ መንገድ መሆኑንም መረዳት ይቻላል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት 20 ሚሊየን ወጣቶች እንዲሳተፉ ዝግጅት ስለማድረጉ የገለጸው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጎ ፈቃደኞቹ በ13 የሥምሪት መስኮች እንደሚሰማሩና በዚህም 51 ሚሊየን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የአረንጓዴ ዐሻራ፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት፣ የትራፊክና የመንገድ ደኅንነት አገልግሎትና የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶክተር) በተገኙበት ሰኔ 18/2015 ዓ.ም በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ ነበረ ጅማሮውን ያደረገው። በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን ያካተተው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ሁለት” በሚል መሪ ሀሳብ አምና ተሳታፊ ያልነበሩት የትግራይ ክልል ወጣቶችንም ተሳታፊ ያደረገ ነው።
ወጣት በኃይሉ ማቲዎስ ከዘንድሮው የክረምት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች መካከል አንዱ ነው። የመጣውም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን አባላት ከአዲስ አበባ በመነሳት የመጀመሪያ ጉዞውን ያደረገው ወደ ኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ነበር። በመቀጠል በተመረጡ ክልሎች አንዳንድ ከተሞች ላይ በጋራ በመሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ስለመከወናቸው ይናገራል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ወደ ኦሮሚያ ክልል፣ ጋምቤላ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ ሀረሪ ክልል፣ ሶማሌ ክልል፣ አፋር ክልል፣ ትግራይ ክልል፣ አማራ ክልል እና ድሬዳዋ ተጉዘናል የሚለው ወጣት በሃይሉ በመጨረሻም አዲስ አበባን ማሳረጊያ ስለማድረጋቸው ይናገራል።
“ምሳሌ በመሆን የተለያዩ ቦታ ያሉ ወጣቶችን ማንቃት ከዓላማችን አንዱ ነው፤ በሄድንበት ቦታ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ሰርተናል” ለአብነትም የአረጋውያን ቤት ማደስ፣ ደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላ፣ ወላይታ ዞን አካባቢ ደግሞ ከትምህርት ገበታቸው እርቀው በጎዳና ላይ ያሉ እና ለሀገር ውስጥ ስደት የተዳረጉ ህፃናትን ለመታደግ ለአካባቢው ማህበረሰብ እና ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ስለመከወናቸው ተነግሯል።
በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ክፍል አጋጥሞ በነበረው ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖች ነበሩ የሚለው ወጣት በሃይሉ፤ በጦርነትና ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመረዳት ጥረት ስለማድረጋቸው እና በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እንዳደረጉ ይናገራል።
የዚህ ትውልድ ወጣቶች ‹‹ኢትዮጵያን አናውቃትም›› የሚለው ወጣት በሃይሉ፤ በድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ምክንያት አሁን ሀገራችንን የማወቅ ዕድሉን አግኝተናል ሲል ይገልጻል።
“የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተለያየ ባህል፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ አለባበስ ተመልክተናል። እኛ ደግሞ ከመጣንበት አካባቢ ውጭ ያለውን የሌሎች ኢትዮጵያውያንን አኗኗር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት እና አንድነት እንድናውቅ እና እንድንረዳ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናል” ሲል ተነግሯል።
ወጣት በኃይሉ እንደሚለው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በባህሪው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በጥብቅ የሚያቆራኝ እና የሚያስተሳስር ተግባር ነው። በመሆኑም በመማር ማስተማር፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ከተማ ግብርና፣ በደም እጦት ለሚሞቱ ለሚሰቃዩና ሕፃናትና ወላድ እናቶችን ለመታደግ የደም ልገሳ የተከናወነበት ነበረ። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በመሥራትና በመጠገን ለብርድ፣ ለዝናብ፣ ለአውሬ ለመሳሰሉት አደጋዎች እንዳይጋለጡ በማድረግ በስጋት ውስጥ ለሚኖሩት እፎይታን በመስጠት ድንቅ ተግባር አከናውነዋል፤ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ወጣቶቹ “ሀገሬ ለእኔ ምን ሰራችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁላት” የሚለውን መርህ መፈክር በማድረግ ለሀገራቸው ያላቸውን ሀገራዊ ፍቅር ስለገለፁ ነው ብሏል።
የዚህ የመልካም ተግባር ባለቤት የሆኑት ወጣቶች የሚያከናውኑት ማህበረሰብ ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው። ስለሆነም ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች አቅማቸው በፈቀደ መጠን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመጠቀም እንደ ልብስ፣ ምግብና መሰል መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ጀምሮ ሌሎች ድጋፎችን ስለማድረጋቸው ወጣቱ ይገልፃል።
ወጣት በኃይሉ እንደሚናገረው፤ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ አሁን በሀገራችን ላይ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሚናውን መጫወት ይኖርበታል። ከነዚህ ሚናዎች መካከል በዋናነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተጓዳኝ በማህበራዊ ሚዲያ ድህረ ገፆች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ዕድገቱን ወደኋላ ለመቀልበስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሀይ ልንላቸው ይገባል ይላል።
እንደ ወጣት በኃይሉ እምነት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚናፈሱ ሀሰተኛና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጫረስ የሚደረጉ እኩይ ተግባራት የጥቂቶች ፍላጎት መሆኑን መረዳት ይገባል። ስለሆነም ወጣቱ እኩይ ተግባሩን ተቀብሎ ለማራገብ ከመሞከር ይልቅ ትክክለኛውን ሀገራዊ የፍቅር መስመር እንዲይዙ ሰህተታቸውን ነቅሶ በማውጣት ማረም ሲቻል ነው።
ስለሆነም ከግጭት፣ ከትርምስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው በአንክሮ መምከር እና ማስተካከል እንዲሁም በመረጃዎቹ ዙሪያ እውነተኛውን ነገር በማውጣት ማጋለጥ ከወጣቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው። “የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዞሬ እንደተመለከትኩት መሬት ላይ ያለው ፍቅር እና መተሳሰብ እንጂ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳለው ጥላቻ እና ፅንፈኝነት አይደለም” ብሏል።
ይሳቅ ሳሙኤል ሌላኛው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊና ከሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ የመጣ ወጣት ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዞረባቸው ጊዜያት በጎ ተግባርን ከማድረግ ባለፈ ከሕዝቡ ጥሩ አቀባበልና ፍቅርን አግኝቷል፤
ወጣቱ የሀገር ባለቤትና ተረካቢ እንደመሆኑ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ወጣቱ እንደሚለውም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር እና መሳል የማህበረሰብን ኑሮ በሚያሻሽሉ ተግባራት በንቃት ሊሳተፍ ይገባል፤ የ2015 የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ እንቅስቃሴም እንደ ሀገር ብሎም በዓለም ላይ እያጋጠመ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ቀድሞ ለመከላከልና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል አቅም መኖሩን የተረዳንበት ነው ይላል።
ወደ መጣበት አካባቢ ሲመለስ ከሕዝቡ ያገኘውን መልካም ነገር ለህብረተሰቡ እንደሚያካፍል የተናገረው ወጣት ይሳቅ፤ ወጣቱ በአረንጓዴ አሻራ እንዲሳተፍ ኃላፊነቴን እወጣለሁ ብሏል። ቡድኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለ21 ቀናት በአራቱም የሀገሪቱ ጫፍ በመጓዝ በጎነትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ወደ ህብረተሰቡ ለማስረጽና በዘርፉ ንቅናቄ እንዲፈጠር አድርጓል።
ከ8 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በሸፈነው ቆይታቸው÷ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች እድሳት ጨምሮ በ13 የሥራ ዘርፎች ለዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወናቸውንም ገልጾ፤ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃደ አገልግሎት አላማው የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ማጠናክር በመሆኑ በዚህም ቡድኑ በተንቀሳቀሰበት አካባቢ የሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ሥራን ስለመስራቱ ተነግሯል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአንድ ጊዜ ተግባር ብቻ አይደለም የሚለው ወጣት ይሳቅ፤ ወጣቶች ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ በጎ ተግባራቸውን በስፋት ሊተገብሩ ይገባል ይላል፤ በተለይም ወጣቶች በደረሱበት ቦታ ሁሉ ስለሰላምና የሕዝቦች አብሮነት በመሥራት ለሀገር ግንባታ በሚረዱ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቆም እንደሚያስፈልግ ይናገራል።
ወጣት ይሳቅ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ይዋደዳሉ፣ ይከባበራሉ ወይ? የሚለውን በአካል የማየት አጋጣሚ ማግኘቱ እንዳስደሰተው ይናገራል፤ “በማህበራዊ በሚዲያ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ እና እኔ መሬት ያየኋት ኢትዮጵያ ለየቅል ሆነ ነው ያገኘኋት” ይላል። “ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደሚዋደዱ በተግባር አይቻለሁ፤ ከተለያየ አካባቢ ለመጣን ወጣቶች በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ፍቅር እና እንክብካቤ በሄድንበት አካባቢ ሁሉ አግኝተናል” ይላል።
ያለችን አንድ ሀገር ናት ቁጭ ብለን በሕዝቦች መካከል ጥላቻ እና መቃቃርን ከመስበክ ይልቅ ያለንን አቅም ለበጎ ነገር በመጠቀም ሀገራችንን ከድህነት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ መትጋት መቻል አለብን የሚለው ወጣቱ፤ በርካታ ሃብት ያላቸው ግለሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። እነዚህ ግለሰቦች ወጣቱን በማስተባበር ቢሰሩ እራሳቸውንም ወጣቶቹንም ሀገራቸውንም ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ይናገራል።
“በጉዟችን የታዘብነው ሌላው ጉዳይ የኢትዮጵያን የመሬት ስፋት እና ሃብት ነው” የሚለው ወጣት ይሳቅ፤ ይህን ሁሉ ሃብት ይዘን ቁጭ ብለናል ወይም ጥቂት ባለሀብቶች ይዘው እየመዘበሩት እንጂ ወደ ምርታማነት ቀይረን መጠቀም አልቻልንም ሲል ጸጸቱን ይገልጻል። ይህንን ሀብት ለመጠቀም እና ሰርተን ለመለወጥ መንግሥትና የግል ባለሀብቱ በጋራ በመሆን ወጣቱን በማስተባበር ማልማት ከቻልን በምግብ እራሳችንን የምንችልበት እና ከድህነት የምንላቀቅበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም ሲል ይናገራል።
ወጣቶቹ እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር በሕግና ደንብ የሚመራ አይደለም። ምክንያቱም “በጎ ፈቃድ” የሚለው ቃል ትርጉሙ እንደሚያመለክተው የሰው ልጆች ማንም ሳያስገድዳቸውና ሳያነሳሳቸው በራሳቸው ህሊና ቀስቃሽነት ከውስጣቸው በሚመነጭ መልካም ስሜት ተነሳስተው ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ አገልግሎቶችን የሚሰሩበት ተግባር፣ እንዲሁም በጊዜና በሁኔታዎች የማይገደብ አገልግሎት መሆኑ ከሌሎች አገልግሎቶች በዓይነቱ የተለየ ነው።
በተለይም ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስተሳስርና እውነተኛዋንም ኢትዮጵያ ለማወቅ የሚረዳ በመሆኑ ወጣቶች በስፋት ሊሳተፉበት እንደሚገባ ወጣት ኃይሉና ወጣት ይሳቅ መልዕክታቸውን ለወጣቱ አስተላልፈዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015