የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ ማሕበረሰባዊነት

 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎ አድራጊዎች ሌሎችን ከመርዳት አኳያ በጎ ምኞትንና ተስፋን ተላብሰውና ከማህበረሰቡ ጎን ሆነው የሚያውቁትን የሚያስተምሩበትና ከሌሎችም የህይወት ክህሎት የሚቀስሙበት ዋነኛ የህይወት መንገድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነትና በመልካም ፍቃደኝነት ላይ ተመስርተው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ያልተዳሰሱ ስራዎችን በማየት በጎነትን የሚያበረክቱበት ተግባርም ነው።ይህ አገልግሎት ታዲያ እድሜ፣ ጾታ፣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ አይገድበውም፡፡

በኢትዮጵያም በጎነት የነበረ ባህል ነው፡፡ ለችግር የተጋለጡና ችግር የደረሰባቸውን ዜጎች ቀስቃሽ ሳያስፈልግ መርዳትም የተለመደ ነው፡፡ በየዓመቱ በተለይ የክረምት ወቅትን ጠብቀው ከሚከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥም የአቅመ ደካሞችንና የአረጋውያንን መኖሪያ ቤት መገንባትና ማደስ፣ የአካባቢ ጽዳት፣ ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ስነልቦና መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ እንደሚሉት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በጎ አድራጊው ከሰብአዊነት፣ ከአስተዳደግና እምነት በመነጨ መልኩ ከተለያዩ ጥቅሞች ነጻ ሆኖ ለህሊናው እርካታና ለማህበረሰቡ እፎይታን ለመስጠት የሚያከናውነው ተግባር ነው፡፡ ተግባሩም ዜጎች በአወንታዊ አስተሳሰብ ስብዕናቸው እንዲገነባ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በዚህ መንገድ ያለፉ የህብረተሰብ ክፍሎችም የተሻለ ስብዕና ኖራቸው ስለሰውና ስለሀገር እንዲያስቡ ያስችላቸዋል፡፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማሳለጥ አመቺው የህብረተሰብ ክፍል ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት እግረመንገዱን ስለ ማህበረሰቡ ኑሮና ችግር የበለጠ እንዲያውቅ ያስችለዋል፡፡ በአንድነትና በፍቅር አብሮ የመኖር እሴቶችንም ያዳብራል፡፡ እውቀትና ባልህልንም ይቀስማል፡፡ ከዚህ አንፃር የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ለህብረተሰቡ ከሚያበረክቱት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ በተጨማሪ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስን እንዲያሳድጉ ያግዛል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የሶሻል ወርክ መምህር ጋሻነው ወርቁ እንደሚናገሩት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መደበኛና ተለምዷዊ በሆነ መልኩ ይከናወናል፡ ፡ መደበኛው የተለያዩ አገልግሎቶችን ለተለያዩ የማህበረሰብ

 ክፍሎች ለመስጠት በጎ ፍቃደኛ ዜጎች በተቋም በመደራጀት ድጋፍ የሚሰጡበት መንገድ ሲሆን፤ ተልምዷዊው ደግሞ ማንኛውም ሰው የየእለት የህይወት ጉዞውን በሚያከናውንበት ወቅት በመንገዱ የሚያገኛቸውንና የሱን ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች የሚያደርገው እገዛ ነው፡፡

በጎነት የኢትዮጵያውያን መለያ ተግባር ቢሆንም ኢኮኖሚውና ፖለቲካው በሚቀየርበት ወቅት የበጎነት ማህበራዊ ስሪቶቹ እየጠፉ መጥተዋል፡፡ በየጎዳናው አረጋውያንና ህጻናት መበራከታቸውም ለነዚህ ማህበረሰባዊ ስሪቶች መጥፋት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በተለይ ፖለቲካው ከዚህ ቀደም የነበረውን የበጎነት ታሪክና እሳቤ በመሸርሸሩ አብዛኛው ሰው ወደ ግላዊነት ህይወት ሄዷል፡፡ በዚህም ታሪካዊ የሆነው በጎነት ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡ ስለዚህ በተደራጀና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መተግበር ይኖርበታል፡፡

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ በጎ ተግባራት በመንግስት መሪነት የሚተገበሩ በመሆናቸው ማህበራዊ መሰረት አልያዙም፡፡ ለዚህም የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን በዘርፉ ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ ሰጭ ጥናቶችን በማከናወን የራሳቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡

ፕሮፌሰር ሀብታሙ እንደሚያብራሩት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሶስት መንገድ ይከፈላል፡፡ ይህም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት

 ባለው እውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት የራሱን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚጥር፣ በሌላው አካል ግፊት እና ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ የሚሳተፍ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው፡፡

በአሁን ወቅት ዜጎች የእረፍት ግዜያቸውን ጠብቀው ባላቸው ሞያ በተለያየ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የጤና ባለሙያዎች በጤና ተቋማት፣ በተለያየ የሙያ መስኮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ደግሞ በአንድ ላይ በመሆን የደም ልገሳና የአካባቢ ፅዳት ዘመቻዎችን ያከናውናሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እንደነዚህ አይነት መልካም ተግባራት ባህል ሊሆኑ ይገባል፡፡

መምህር ጋሻነው በበኩላቸው፣ በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊየን በላይ ዜጎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ያስረዳሉ፡፡ ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችም በመላው ዓለም እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች የራሳቸውን አመለካከትና ባህል መሰረት አድርገው አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉ በመሆናቸው ይህን ተከትሎ ሊጣረሱ የሚችሉ ማህበረሰባዊ መገለጫዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህንን ሊያስታርቅ የሚችል አሰራር በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራት የሚፈልጉ ወጣቶችና  ባለሞያዎች መፈጠናራቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳትፎ ማድረጋቸው የአገልግሎቱ ጠንካራ ጎኖች በመሆናቸው አገልግሎቱን ሀገር አቀፍ ለማድረግ የሰላም ሚኒስቴር የወሰደው መነሳሳት እንደ ትልቅ ተግባር መወሰድ ይኖርበታል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰባዊ ኃላፊነት እንደሆነ የሚገነዘበው የማህበረሰብ ክፍል ቁጥሩ አነስተኛ መሆን ደግሞ በአገልግሎቱ የሚታይ ደካማ ጎን ሲሆን ከዚህ ባለፈ አገልግሎት ሰጭዎች ከሞያቸው ጋር በተጣጣመ መልኩ አገልግሎቱን አለመስጠት በውጤታማነቱ ላይ ጫና ፈጥሯል። ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ ግለሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ማስገንዘብና አገልግሎቱን ለተማሪዎች በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማካተት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ፕሮፌሰር ሀብታሙ እንደሚገልፁት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያበረታታ ቢሆንም ከሌሎች ዓለም ሀገራት ተሞክሮዎች አንፃር ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች በሞያቸው ዘርፉ በመስራት ሞያቸውን የሚያዳብሩበትና ተቀባዩም ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አሁን ካለበት የተሻለ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡

አገልግሎቱ የሚሰጣቸው ዘርፎች ማህበረሰቡ ካለው የኑሮ ሁኔታ አንፃር ጥናት ተደርጎ ቢጨመርበትና ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ጉዳዮች ተለይተው በቅደም ተከተል መከናውን ቢችሉ ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፈ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለፖለቲካ ፍጆታና ለታይታ መከናወን ያለበት ተግባር አይደለም፡፡

በሌላ በኩል መምህር ጋሻነው እንደሚናገሩት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው መነሳሳት ከፖለቲካዊ አንድምታ በመውጣት ማህበረሰባዊ ሊሆን ይገባል፡፡ በጎነት ወቅትን መሰረት በማድረግና በተወሰነ የስራ ዘርፍ ላይ ብቻ እንዲከናወን ኃላፊነት ወስዶ ተግባራዊ እያደረገ ያለው አካል ግፊት እያደረገ በመሆኑ አገልግሎቱ በክረምት ወቅትና ቤት ከማደስ በተጨማሪ ሌሎች ዘርፎችንም በማከል ቀጣይነት ያለው ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

አብዛኛው ማህበረሰብ በጦርነትና በግጭት ከመኖሪያ አካባቢው የተፈናቀለ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ መቀየር የሚያስችል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባራዊ ሲደረግ እየታየ ባለመሆኑ በእነኝህ ስፍራዎችና በአካል ጉዳተኞ ላይ ትኩረት ያደረገ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊኖር ይገባል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *