-የገዳማት ደን መመናመን አሳሳቢ ሆኗል
አዲስ አበባ፡- 19 ገዳማትና ቤተክርስ ቲያናት የራሳቸው ሳይት ፕላንና የባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲኖራቸው ሥራዎች መጀመራቸውን ተገለጸ። በገዳማትና ቤተክርስቲያናት ደን እየተመናመነ መሄዱ አሳሳቢ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክር ስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ምክትል ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገብረስላሴ አፅብሃ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ አብዛኞቹ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት ሳይት ፕላንና የመሬት የይዞታ ባለቤትነት የላቸውም።
ይህም ደን እንዲወድም ብሎም ኅብረተሰቡን ለግጭቶች እየዳረገ ነው። በመሆኑም የገዳማትና ቤተክርስቲያናት ደኖች የራሳቸው ሳይት ፕላን እንዲኖራቸው እንዲሁም የባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣቸው በየደረጃውም ኮሚቴ እየተዋቀረና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመናበብና ሕዝቡን በማሳተፍ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
እንደ አቶ ገብረስላሴ ገለጻ፣ በሚቀጥሉ አምስት ዓመታት ውስጥ 19 ቤተክርስቲያናትና ገዳማት የባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠቱ ይጠናቀቃል። መንግሥት ከሚኖረው ከፍተኛ ይሁንታና ከሚያደርገው እገዛ ብሎም አጋር አካላት በሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በርካታ ሥራዎች ይከናወናሉ።
እንደ አቶ ገብረስላሴ ገለፃ፤ በአገሪቱ ከ35ሺ በላይ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን፤ አንዱ ቤተ እምነት ከአንድ እስከ 4000 ሄክታር የሚሸፍን ደን ያለው ሲሆን ቢያንስ በአሁኑ ወቅት 3ነጥብ5 ሚሊዮን ሄክታር የቤተ እምነት ሥፍራዎች በደን የተሸፈኑ ናቸው።
ምንም እንኳን የቤተክርስቲያንና ገዳማት ደኖች የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በሚያስገኝ መልኩ በሚገባ ባይሰራበትም፤ የሥነ ምህዳር ሚዛንን በመጠበቅና የካርቦን ልቀትን በመቆጣጠር እጅግ የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑንም በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኝ ደን ክምችትም ለመድሃኒት ቅመማ፣ ለኢኮ ቱሪዝም ትልቅ አበርክቶ እየሰጠ ነው። የደን ልማቱን ለማጠናከርም ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ህብረት አካል የሆነው አክት፤ መካነ እየሱስ፣ ፓድ፣ ሉተራልና ሌሎች ቤተ ተቋማት ጋር የገዳማት ደን ተጠብቀው እንዲቆዩ በትብብር እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይሁንና የሕዝብ ብዛት መጨመርና የእርሻ መሬት ጥበት፣ ልቅ የግጦሽ ስምሪት፣ እንጨት ለቀማና ከሰል ማክሰል የተሰማሩ አካላት፣ ለግንባታ፣ ለማዕድን ሥራ፣ ለአደንና ለመሳሰሉት ተብሎ ደኑ እየተመነጠረ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ደኖቹ ጥቅጥቅ ያሉ በመሆናቸው ዘራቸውን ለመተካት አለመቻልና ዘመናዊ የደን እንክብካቤና አስተዳደር አለመኖሩ በገዳማትና ቤተክርስቲያናት የሚገኙ ደኖች እንዲመናመኑ በማድረጉ አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል። ዘርፉ ከሚመለከታው የመንግሥት አካላት ጋር የሚሰራ ሲሆን፤ ምንም እንኳን አገሪቱ የደን ሽፋን እየጨመረ ነው ቢባልም በቤተክርስቲያንና ገዳማት አካባቢ የደን ሽፋን እየቀነሰ መሆኑንም በጥናት መደረሱን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክር ስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በአዋጅ 1964 ዓ.ም የተመሰረተ መንግሥታዊ ያልሆነ የልማት ድርጅት ሲሆን፤ የቤተክርስቲያን የልማት ክንፍ ሆኖ በማገልገል ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን ሰብዓዊና ልማት ድጋፍ ለማጠናከርና በ1960ዎቹ በአፍሪካ የፀረ ቅኝ ግዛት አቀንቃኞችና ነፃነት ተዋጊዎች ልምድ ለመቅሰም ሲመጡ በሚደርስባቸው ጫና ከለላ ለመስጠት የተቋቋመ ነው። በተጨማሪም በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ስደተኞችና ስደት ተመላሽ ማገዝ፣ ሕፃናትና እናቶች ላይ ሥነ ምግብ ላይ እየሰራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በ19 ገዳማትና ቤተክርስቲያናት ደንና በመንግሥት ጥብቅ ደን ልማት ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በ ክፍለዮሐንስ አንበርብር