አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የበጀት ዕጥረት ለመንገዶች ጥራት ችግር ምክንያት መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ገለጸ።
በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ስትጀመር ጀምሮ የነበሩ መንገዶች አሁንም እንዳሉ ናቸው።
እነዚህን መንገዶች አፍርሶ እንደገና ለመሥራት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።በተለይም በመሃል ከተማዋ ውስጥ የሚገኙት መንገዶች ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ያሉባቸው ስለሆነ እነዚያን አፍርሶ ለመተካት በጀት ይፈልጋል።
ለመንገዶቹ ከፍተኛ ጥገና ማድረግ ባለመቻሉም ጊዜያዊና ቀላል ጥገና ይደረግ ላቸዋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ አንድ መንገድ ሲጠገን በቀጣይ ዓመትም እንደሚጠገን ቢታወቅም የትራፊክ ፍሰቱ ከፍተኛ መሆን አሉታዊ ጫና እንዳሳደረ ይገልጻሉ።
መንገዶቹን በጥራት ለመሥራት እንደ አዲስ መሰራት እንዳለባቸው የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ ያለውን መንገድ እንደ አብነት ይጠቅሳሉ።በዚያ በአንድ መስመር ብቻ ብዙ ቢሊዮን ብር ወስዷል።
የመንገድ ጥገና ሲባል እንደ አዲስ አፍርሶ መሥራትንም እንደሚጨምር የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ለመንገዶች ክብካቤ ማህበረሰቡም ኃላፊነት እንዳለበት ያሳስባሉ።ግንዛቤው ባለመኖሩም የሚጠገኑ መንገዶች ላይ ጉዳት ሲደርስባቸው ይስተዋላል።ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት የተጠገነ መንገድ በአንድ ባለሀብት ጉዳት ይደርስበታል ብለዋል።
የመንገድ ጥገና ባለሙያዎችን ብቃት ለማሳደግ ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በጋራ እየተሰራ ሲሆን፣ የጃፓን ባለሙያዎች ለመንገድ ጥገና የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችንና አጠቃቀማቸውን በተመለከተም የሙያ ድጋፍ አድርገዋል ሲሉም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በዋለልኝ አየለ