– የትምህርት ማስረጃ ለመውሰድ የሚከፈለውን 470ሺ ብር አስቀረ
አዲስአበባ፡- ከዚህ ቀደም በፌዴራል ሆስፒታሎች ሲቆረጥ የነበረው የትርፍ ሰዓት እና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ታክስ እና የሐኪሞች የትምህርት ማስረጃ ለመውሰድ የተቀመጠውን የ470 ሺ ብር ክፍያ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ መቅረቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።
በጤና ባለሙያዎች ወቅታዊ ጉዳይ እና በሚነሱ ጥያቄዎች አስመልክተው የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ከፌዴራል የጤና ተቋማት ሠራተኞች ጋር ተያይዞ የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማ ጥቅም ክፍያ ላይ የሚቆረጠው ታክስ እንደሚቆም ተደርጓል።
በመሆኑም በፌዴራል ሆስፒታሎች የሚገኙ ሠራተኞች የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማ ጥቅም ታክስ ክፍያ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌዴራል መንግሥት በራሱ ለመሸፈን ወስኗል። በዚህ መሠረት አጠቃላይ በወር 70 ሚሊዮን ብር ይሸፍናል።
እንደ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር ገለጻ፤ የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማ ጥቅም ታክስ ክፍያውን የማስቀረት ሥራ በክልሎችም ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። የታክስ ማስቀረቱን ተግባራዊ ያላደረጉ ክልሎች በአጭር ጊዜ ጉዳዩን ወደ ክልል ካቢኔ አቅርበው እንዲያስወስኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሌላ በኩል የሐኪሞችን የትምህርት ወጪ መጋራት ክፍያ በተመለከተ ማስተካከያ መደረጉን ዶክተር አሚር ተናግረዋል። በተለይም ከዚህ ቀደም ሐኪሞች የትምህርት ማስረጃ ለማግኘት መክፈል አለባቸው ተብሎ የተቀመጠው 470 ሺ ብር ክፍያ እንዲቀር መደረጉን አስረድተዋል። በመሆኑም እንደማንኛውም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በወጪ መጋራት ሕግ መሠረት እንዲስተናገዱ መወሰኑን ገልጸዋል።
ዶክተር አሚር እንደገለጹት፤ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የተነሱ የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም እንዲሁም የሥራ ላይ ደህንነት የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የተውጣጣው ግብረኃይል የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ይሆናል።
በሌላ በኩል በፌዴራል ሆስፒታሎች ከዚህ በፊት የነበረው ወደጎን የሚሄድ የእድገት ደረጃ ከግንቦት 2011ዓ.ም ጀምሮ ወደላይኛው እርከን እንዲሆን መወሰኑን ዶክተር አሚር ገልጸዋል። በተመሳሳይ ክልሎች ጉዳዩን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ፣ በኢትዮጵያ 9ሺ 182 ሐኪሞች እና 59ሺ 469 ነርሶች በሥራ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በጌትነት ተስፋማርያም