የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ 75/2014 የተቋቋመ እና ሙስናን በመዋጋት ላይ የሚሰራ ተቋም ነው።የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት የሞራል እሴቶችን በመገንባት የነቃ እና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ህብረተሰብ መፍጠር፣ የሙስና ወንጀል እና ብልሹ አሰራርን መከላከል፣ ነዋሪው የፀረ-ሙስና ትግል ባለቤት እንዲሆን ማድረግ፤ በጸረ ሙስና ትግል ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ሥርዓት ማስፈን እና በህግ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባር ለመፈጸም የሚያስችል ተቋማዊ አቅም መገንባት ከዓላማዎቹ ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው። በከተማዋ ሙስና ስር እንዳይሰድ መከላከልና ሠላማዊ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማስቻል የተቋሙ ትኩረት ነው።
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ሙስናን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል ሲል የዝግጅት ክፍላችን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አሰፋ ቶላ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ሞልቶታል፤ በዚህ ቆይታው ምን ተግባራትን አከናወነ?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ 75/2014 ከተቋቋመ ወዲህ አንድ ዓመት ሞልቶታል።በአንድ ዓመት ቆይታውም በርካታ ተግባራትን አከናውነናል።ከአዋጁ በመነሳት ደንቦችንና መመሪዎችን አዘጋጅተናል።ከደንቦቹ ላይ ለሥራ የሚያስፈልጉ ስምንት መመሪያዎች ወጥተው ለፍትህ ሚኒስቴር ተልከዋል።የተቋሙን የሰው ኃይል አስፈላጊነት በምን ደረጃ ነው የሚለውን በማጥናትና በመለየት 30 ከመቶ በቅጥር አሟልተናል።በጀት አፅድቀንም ሥራ ጀምረናል።ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡
እንደሚታወቀው የሙስና ትልቁ መንስዔ መንፈሳዊ በሽታ ነው።ሰው ውስጡ ከታመመና ከቆሸሸ ወደ ሌብነት ይገባል።እኛም ይህን ለማስተካከል በበጀት ዓመቱ ሰፊ ርብርብር አድርገናል።ሌብነት በከተማዋ ብሎም በአገሪቱ እንዳይንሰራፋ ዜጎች አስተሳሰብ ላይ መሥራት ትኩረት ተሰጥቶታል።በመሆኑም በዚህ በጀት ዓመት ሰፋፊ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ከሁሉም ቅድሚያ የተሰጠው ሥነ ምግባር ሲሆን ይህ ከስር መሰረቱ ተጀምሮ የሚሰራበት ነው።እኛም ይህን ለማስተካከል ግብረ ገብነት ላይ መስራት ይገባል በሚል መነሻ በከተማዋ ከሚገኙ የትምህርት አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት አድርገናል።በሚኒ-ሚዲያም ሥነ ምግባር ማነፅ ላይ በስፋት እንዲሰሩም መግባባት ላይ ተደርሶ በትምህርት ተቋማት ጋር በሚገባ እየተሠራ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ሙስናን ለመዋጋት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ምክክር አድርጓል። እንደሚታወቀው መገናኛ ብዙሃን የተቃና የማህበረሰብ እሳቤን በመቅረጽ ጭምር ሚናቸው ትልቅ ነው።በተለይም ደግሞ የምርመራ ጋዜጠኝነት የበለጠ እንዲጠናከር በማሰብ ሥምምነት ፈጽመን እየሰራን ነው። ሌላኛው በሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸውና የሃይማኖት ተቋማትን ከሚመሩ የዕምነት መሪዎች ጋር ለመሥራት አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በዚህ አውድ የመጀመሪያው የሃይማኖት አባቶች በራሳቸው አርዓያ እንዲሆኑ የተግባባን ሲሆን፤ ተከታዮቻቸውን ማስተማር እንዳለባቸው ተስማምተናል። በከተማ፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤዎች ጋር ሙስና በመከላከል ላይ በጋራ ለመስራት ሥምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ ሙስናን በመከላከል ረገድ የተቋማት ሰራተኞች ሚና ትልቅ ነው።በተለይም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠትና ተገልጋዮችን ማርካት ተገቢ ነው። በዚህ ላይ ሰራተኞችን ለማብቃት ስልጠናዎችን እየሰጠን ነው። ከወረዳ ጀምሮ እስከ ማዕከል ለሚገኙ አመራሮችም ስልጠና ለመስጠት ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል። በአጠቃላይ ሙስናን ለመዋጋት በሚያስችል መንገድ ከከተማ ነዋሪዎች፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ ወጣቶችና ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሙስና የመከላከል ስልጠና ምን ያክል ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- በዚህ ዓመት 303ሺ በላይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ማግኘት ችለናል። ስልጠናን በሚመለከትም 455 የስልጠና መድረኮችን አዘጋጅተናል። እነዚህ ግን በማዕከል ብቻ የተደረጉ ሳይሆኑ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ እና በማዕከል ጭምር ነው።በተሰራው ሥራም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችን ማየት ችለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሙስና የመከላከል ስልጠና ከተሰጠ በኋላ ምን ውጤት ተገኘ?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- በከተማ አስተዳደሩ ሙስናን ለመከላከል ቅንጅታዊ ትግበራ እንደሚያስፈልግ ይታመናል።የሥነ ምግባር ግንባታው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሮች ሲፈጠሩ ደግሞ የመከላከል ሥራ መሠራት አለበት።ለዚህም የሚያስፈልግ የጥቆማ መስጫ አውዶችን ፈጥረናል።ካዘጋጀነው የጥቆማ መስጫ መካከል ‹‹8887›› ነፃ የስልክ መስመር አለን።
በተለያዩ መንገዶች በዚህ በጀት ዓመት አመርቂ ስራ ሰርተናል ማለት ይቻላል።በበጀት ዓመቱ ሙስናን ለመዋጋት በተጀመረው ጥረት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ማዕከል በነበረው ስራ 3ሺ811 የሚሆኑ ጥቆማዎች ወደ ኮሚሽኑ መጥተዋል።ከዚህ መካከል እንደየሁኔታው ጥፋተኛ የሆኑ 2ሺ751 አካላት ተጠያቂ ተደርገዋል።ይህም ከትንሹ የሥነ ምግባር ግድፈት ቅጣት እስከ ሥራ ስንብት የደረሱ አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ምን ያህል ሃብት ማዳን ተችሏል?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- ሃብትን ከሙስና በማዳን ረገድም በተመሳሳይ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። ተቋሙ ውስጥ አስቸኳይ ሙስና መከላከል ዘርፍ የሚባል አለ። በዚህ አስቸኳይ ሙስና መከላከል ዘርፍ በተሰራው ጥንቃቄ የተሞላው ስራም አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ከሙሰኞች እጅ ማዳን ተችሏል። በእርግጥ ሙስና መከላከል ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚተው አይደለም።በዚህ ላይ ህብረተሰቡ፣ ማህበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በስፋት መሥራት አለባቸው፡፡
በአጠቃላይ 2015 በጀት ዓመትም በሌሎች ሙስና የመከላከል ሚና ባላቸው አካላት ጋር በተሠራው ቅንጅታዊ አሠራር ሰፊ ርብርብ የተደረገ ሲሆን፤ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሃብት ማዳን ተችሏል።ይህ ሃብት በጣም ትልቅ ነው።ከሙሰኞች የዳነ ሃብት ነው።ለከተማዋ ዕድገትና መሰረተ ልማት ግንባታ ቢውል እጅግ ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ የሚሰራበት ሃብት ነው። በእነዚህ ጥረቶች በጥቅሉ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ከሙስና ድኗል። በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ ከገንዘብ ባሻገር 240ሺ681 ካሬ ሜትር መሬት ለመሬት ባንክ ገቢ ማድረግ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከወረዳ እስከ ማዕከል በነበረው ሥራ 3ሺ811 ከሚሆኑ ጥቆማዎች ተጠያቂ የሆኑት 2ሺ751 ናቸው።ቀሪዎቹስ ጥቆማዎች ምን ተደረጉ?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- በሂደት ላይ ያሉ ጥቆማዎች አሉ። ከዚህም ውጭ በከተማ ደረጃ የተቋቋመ ፀረ-ሙስና ኮሚቴ አለ። ይህ ለእኛ ኮሚሽን ከደረሱ 3ሺ811 ጥቆማዎች ውጭ 1ሺ700 የሚሆኑ ጥቆማዎች ለኮሚቴው ደርሰውታል። እነርሱ በራሳቸው መንገድ ሁኔታዎችን እያጠኑና እያጠናከሩ በፖሊስና በአቃቢ ህግ የራሳቸውን ሥራ እየሰሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚቴ የኮሚሽኑ ሚና ምንድን ነው?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- ፀረ-ሙስና ኮሚቴ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ በከተማ ደረጃ ሲቋቋም አንዱና ዋነኛ ዓላማው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ለማጠናከር ነው። ለእኛ ተጨማሪ አቅም ለመሆን ነው።ብዙውን ጊዜ ከተማዋ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በራሱ ጊዜ የመመርመር የመክሰስ ስልጣን የለውም። ኮሚሽኑ ‹‹እኔ የላየኋቸው ‹ኬዞች› በፍጥነት ምርመራ ተደርጎ ክስ አይጀመርም›› የሚል ቅሬታ ሲያነሳ ስለነበር ይህን ችግር ለማቃለል በአገር ደረጃ ምክክር ተደርጎ ኮሚቴ ተቋቁሟል። በመሆኑም የፀረ-ሙስና ኮሚቴ መቋቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥራ ለመቀማት ሳይሆን ለመደገፍና ተጨማሪ አቅም ለመሆን ነው።
እንግዲህ ይህ ኮሚቴ ከተቋቋመ በኋላ 1ሺ700 በላይ ጥቆማዎችን በመቀበል ተጠያቂነትን እያሰፈነ ነው።በዚህ ውስጥ የተቋማችንን ሚና በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር የኮሚቴው ፀሃፊ ነው።በመሆኑም ተቋማችን በዚህ ውስጥ ይሳተፋል፤ በጋራ ሥራ ይገመግማሉ።ያሉትን ጥንካሬዎችንና ጉድለቶችን በጋራ በመገምገም አቅጣጫ ያስቀምጣሉ።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ያለው የሙስና ተጋላጭነት የሚያሳይ ጥናት ተደርጓል?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- በበጀት ዓመቱ መጠነ ሰፊ የፀረ ሙስና ትግል ተደርጓል።ሙስና ያለበትን ደረጃ ለማወቅም
በዚያው መጠን ጥረት ተደርጓል። ሙስና ያለበትን ሁኔታ ማወቅና መፍትሄ ማስቀመጥም አንዱ ሥራችን ነው። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ 30 የአሰራር ጥናቶች አድርገናል። እነዚህ የጥናት ውጤቶች የሚያመለክቷቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአሰራር ጥናቶቹ ያመላከቱት ነገር ምንድን ነው?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- ባካሄድናቸው የአሰራር ጥናቶች ብዙ ነገሮችን ለመረዳት አስችሎናል። የመንግስት ተቋማት የሙስና ተጋላጭነት የሚያሳይ ነው። የመንግስት ሃብት ወደ ማህበረሰቡ የሚወጣባቸው ተቋማት ሙስና እንደሚበዛበት ጥናቱ ያሳያል። ህጋዊነትን የሚያሰፍኑ አንዳንድ ተቋማትም ለሙስና ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል። መሬት አስተዳደር፣ ወሳኝ ኩነት፣ በመሳሰሉት ተቋማት ለሙስና ተጋላጭ መሆናቸውን ተረድተናል። በተጨማሪም የመንግስት ግዥ፣ ሐሰተኛ መታወቂያ፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ በቀበሌ ቤቶች እና በመሳሰሉት ላይ ሰፋ ያለ የሙስና ዝንባሌና ድርጊቶች አሉ። አገልግሎትን የመሸጥ ዝንባሌዎችም እንደሚስተዋሉ ደርሰንበታል። በመሆኑም በዚህ አካባቢ ያሉ የአሰራር ክፍተቶች ተለይተው ለመንግስት ቀርበዋል። ከብቃት ማረጋገጫ (ሲ.ኦ.ሲ) ፈተና ጋር በተያያዘ ሰፋ ያሉ ክፍተቶች አሉ። በዚህ የተረዳነው የማይመጥነውን ወይንም ብቁ ያልሆነን ሰው የማሳለፍ ዝንባሌዎች አሉ። በዚህም ተጠያቂ እየሆኑ የሚገኙ አካላት አሉ። ከቀበሌ ቤቶች ጋር የተያዘው የቆዩ ቢሆንም ያለአግባብ ቤቶችን ለማይመለከተው አካል ማስተላለፍ ነው። የመንግስት ቤቶችንም ወደ ግለሰብ ያዞሩ አሉ። በዚህ ላይ ሰፋ ያሉ ክፍተቶች በመኖራቸው ማስተካከል ይጠይቃል።እኛም መፍትሄ እንዲሰጠው እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ ካለው ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መስተጋብር በተጨማሪ ከሚስተዋለው ከፍተኛ የሙስና ዝንባሌና የቴክኖሎጂ ዕድገት አኳያ ኮሚሽኑ ሙስናን መከላከል የሚያስችል አቅም ገንብቷል?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- የተቋም ግንባታ በሂደት የሚከናወን ነው።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ደግሞ ዕድሜው በጣም አጭር ነው፤ ገና አንድ ዓመቱ ነው።ራሳችንን ገንብተን አጠናቀናል የሚል ግምገማ የለንም።ገና ብዙ መሄድ ይጠበቅብናል፤ የተቋም ቅርፅ ነው ያስያዝነው።በሙሉ አቅም ወደ ስራ አልገባንም። ለምሳሌ የሃብት ምዝገባ አልጀመርንም።አንዱ ሙስናን ለመከላከል ከሚጠቅሙ አሰራሮች መካከል የሰራተኛውንና የአመራሩን ሃብት መዝግቦ መያዝ ነው።በተጨማሪም የነዋሪዎችን ሃብት መዝግቦ መያዝንም ያካትታል፡፡
እኛ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለሃብት ምዝገባ የሚያስፈልጉ ምቹ ሁኔታዎችን ነው እየፈጠርን ያለነው። ቀደም ሲል እንደነበረው የሃብት ምዝገባው በማንዋል መመዝገብ አዋጭ ባለመሆኑ በቴክኖሎጂ መመዝገብ ይገባል። በመሆኑም ዲጂታል በሆነ መንገድ ሃብት ለመመዝገብ ምቹ ሁኔታ እየፈጠርን ነው፡፡
ሁለተኛው ከሠው ኃይል አንፃር ወደ ኮሚሽኑ የሚመጣ ወይንም የሚቀላቀል ሰው በሥነ ምግባር የተሻለ ሰውና ከሌብነት የፀዳና በድፍረት የሚታገል መሆን አለበት። ከወረዳ እስከ ማዕከል የሚደረገው የሥነ ምግባር መኮንኖች ምደባም አልተጠናቀቀም። ስለዚህ የተቋም ቅርፅ አስይዘን ጎን ለጎን ሥራዎችንም እየሰራን ነው።እኛ ጥሩ መሰረት እንዲይዝ እየተጋን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተቋም ደረጃ የተሟላ የሰው ኃይል ምደባ ወይንም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ሙስና ያስቀራል?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- ሌብነትን ለመቀነስ የመጀመሪያው ህሊና ቢስነትን መቀነስና ሞራል ግንባታው ላይ መሥራት ነው።ሰው ከራሱ ጋር ሰላም መሆን አለበት፤ ሰላም ለመሆን ደግሞ ጤናማ መሆን አለበት።እውነትን ደፍሮ የሚናገር መሆን አለበት።ወርቃማ የሥነ ምግባር መርሆችንም መከተል ተገቢ ነው።በማህበረሰቡ ዘንድ አመለካከት ላይ መሰራት አለበት።የማህበረሰቡ አስተሳሰብ ከተቀየረ መዋቅራዊ ሌብነት ይቀራል።በመሆኑም ይህን ለማምጣት ደግሞ በሰው ልጅ ጭንቅላት ወይንም የሁለመናው ገዥ በሆነው አስተሳሰብ ላይ በአንክሮ መሥራት ግድ ይላል።እኛም ይህን ለውጥ መኖር አለበት ብለን እየሰራን ነው፡፡
ሙስናን ለመዋጋት የትምህርት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች፣ የሲቪል አደረጃጀቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህዝብ ተመራጮች ጭምር በዚህ ላይ ሚናቸው ጉልህ ነው።የህዝብ ተመራጮች ስለሙስና አፀያፊነት ብዙውን ጊዜ ያነሳሉ፤ ይህ ጥሩ ነገር ነው።ነገር ግን በተመረጡበት አካባቢ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው።ማን እየሰረቀ እንደሆነ፤ ምን እንደተሰረቀ በመረጃ እና ማስረጃ እየደገፉ ለፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ ተጨማሪ አቅም መሆን አለባቸው።ይህም ብቻ ሳይሆን በተመረጡበት አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ሙስናን የማይሸከም ማህበረሰብ እንዲሆን መስራትና አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል።ይህ ከሆነ በከተማችን ሌብነት ስጋት የመሆን ዕድል አይኖረውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ሙስናን ለመዋጋት ስጋቶች ብሎ የለያቸው ምንድን ናቸው?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- እንደ ስጋት የምንመለከተውና ለፀረ ሙስና ትግሉ እንቅፋት ሊሆን የሚችለው የሥነ-ምግባር መሸርሸሩ አንዱ ነው።አሁን ባለው ሁኔታ በርካቶች ህሊናቸውን ከመፍራት ይልቅ የንዋይ አምላኪ እየሆኑ ነው።በቤተሰብ መካከል በራሱ አለመተማን እየታየ ነው።በብዛት የሞራል ዝቅጠት እያስተዋልን ነው።አንዱ ሥራችን ከሥነ ምግባር ዝቅጠት ውስጥ መውጣት አለበት ነው።እኛም ይህን ለማስተካከል ነው እየሰራን ያለነው፡፡
ሌላኛው የመረጃ መዛባት ነው።በዲጂታል ዘመን ላይ በመሆናችን ጥሩ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ፈተና አለው።አሁን ድኅረ እውነት ዓለም ላይ ስለሆንን፤ ውሸት የሆኑ ግን እውነት የሚመስሉ ነገሮች ይፈበረካሉ።የተቀባባ ውሸት እውነት ሆኖ የመቅረብ ዕድል አለው።ይህ ደግሞ ሌቦች መረጃዎችን ለማዛባት በጣም ይጠቀሙበታል።የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ዓርዓያ የሆነውን ሰው የማጥቃት ሁኔታ አለ።በዚህ ውስጥ እነርሱ የሚሰሩት ወንጀል እንዲደበቅ ይሆናል።መረጃን በአሉባልታ የመሸፈን ሁኔታዎች ስለሚኖሩም በደንብ የሚታገሉ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ያሸማቅቃል።ሌቦች በኔት ወርክ በመደራጀት ሀቀኛ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።ይህ ደግሞ የፀረ ሙስና ትግሉን ያዳክመዋል።ይህ አንዱ ስጋታችን ነው።
የደላላ መብዛትም ስጋት ነው።የሚሰርቅ አመራርና ባለሙያ አለ።በዚያው ልክ ጠንካራና ቁርጠኛ ባለሙያና አመራር መኖሩንም መካድ የለብንም።ደላሎች የገንዘብ አቅምና ኔትወርክ አላቸው።እነዚህ ደግሞ የመንግስት ሰራተኞችን እያሳሳቱ ወደ ሙስና የማስገባትና የመጥለፍ አካሄድን በመጠቀም ወደ ወጥመድ ያስገባሉ፡፡
ተቋሙ ከሙስና ጋር በተያያዘ ሁሉንም ሙሉ ለሙሉ አይሰራም።በዓለም ነባራዊ ሁኔታ መሰል ተቋማት ሦስት አቅም አላቸው። አንዳንዶች ሙስናን ይከላከላሉ፤ ይመረምራሉ፣ ይከሳሉ። አንዳንዶች ደግሞ ይከላከላሉ፤ ይመረምራሉ።በእኛ አገር ነባራዊ ሀኔታ ደግሞ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይከላከላል።የሚመረምረው ፖሊስ ነው።ከሳሽ ደግሞ ዓቃቢ ህግ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተሰጠው ስልጣን ውስን መሆኑና መክሰስና መመርመር አለመቻሉ አቅሙን የበረታ እንዳይሆን አድርጎታል።በተጨማሪም ሙስና የሚሰሩ አካላት በየጊዜው ባህሪው ተቀያያሪ በመሆኑ ለመከላከል አስቸጋሪና አሳሳቢ እያደረገው ነው።የቴክኖሎጂው እያደገ መምጣት ለሙሰኞች ፈተና እንደመሆኑ መጠን በዚያው ልክ ደግሞ አመቺ ሁኔታ የመፍጠር ዕድልም አለው።
በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታና ደግሞ በፍትህ ተቋማት ውስጥ ሌብነቱ ከፍተኛ ነው። እንደ አገር ያለው ግምገማ የሚያሳው ይህንን ነው።ስለዚህ ሌብነቱ በብዛት አለበት ተብሎ ለሚታሰበው አካል ምርመራ እና ክስ ይሰጣል፤ ይህ ስጋት ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም የፍትህ ተቋማት ሌቦች ናቸው ማለት አይደለም።በፍትህ ተቋማት ውስጥ ሕይወታቸውን መሥዋዕት እስከ መክፈል የሚደርሱ ፖሊሶች፣ አቃቢ ህጎችና ዳኞች መኖራቸውን ማወቅም ተገቢ ነው፡፡
ዋናው ነገር ግን የፍትህ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ አለመገንባታቸው ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።ፍትህን ያስከብራል ብለን የምናስበው አካል በራሱ ስርቆት ውስጥ አለበት።እነዚህ አካላት ስርቆት ውስጥ መሆናቸው የአገራችን ሙስና አሳሳቢ ያደርገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሙስናን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም የሚፈልጉ አካላት አሉ። በተጠና መልኩ ሙስና ላይ ዘመቻ ሲጀመር የብሄር፣ ሃይማኖትና ሌሎች ዘውጎችን በመጥቀስ ለተጠርጣሪው ሽፋን ለመስጠት ይሞከራል። ይህ ደግሞ ማህበረሰቡ የተሳሳተ ዕይታ እንዲኖረው ያደርጋል። በሌላ መልኩ ደግሞ ለበቀል ብቻ የተሳሳተ ጥቆማ የሚሰጡ አሉ። እነዚህ ደግሞ የፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ ክፍተት ይፈጥራሉ ብለን የምናስባቸው ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰዱትስ ምንድን ናቸው?
ኮሚሽነር አሰፋ፡- እንደመልካም አጋጣሚ የምንወስደው፤ እንደ ከተማ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መደራጀቱ አቅም ፈጥራል። ሌላው የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው። እንደ አገር የተፀነሱ እሳቤዎች ለአብነትም ብሄራዊ የእርቀ ሠላም ኮሚሽን፤ ሰው ውስጡን እንዲያዳምጥ፣ የትርክት ለውጥ የሚያመጣ እና የጋራ መግባባት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር ያግዛል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የሞራል እሴት ግንባታ ይሰራል ብለን እናስባለን። ሠላም እጦት ባለበት ሥፍራ ሙስና ይንሰራፋል። ሠላም እየሰፈነ የሚሄድ ከሆነ ሌብነት ይከስማል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
ኮሚሽነር አሰፋ፡- እኔም አመሰግናለሁ። ከማጠናቀቄ በፊት ግን አንድ ሃሳብ መጨመር እፈልጋለሁ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመዋጋት በትኩረት እየሰራ ነው። የከተማችን ነዋሪዎች የፀረ ሙስና ትግሉ አካልና ባለቤት መሆን አለባቸው። ሥራዎች በይመለከተኛል መንፈስ መሥራት ይገባል። የከተማችን አመራርና ሰራተኛም በታማኝነት ህዝቡን ማገልገል አለበት። ውግናችን ለህዝብ መሆን አለበት፡፡
ሲንጋፖር በዓለማችን ካሉ አገራት ሙስናን በመከላከል ቀዳሚ አገር ናት። ለዚህም አምስቱ ‹‹ሲ›› የሚባሉ ዘዴዎችን ትጠቀማለች። አንደኛ አመራር፣ ሰራተኛ እና ህዝቡ ጋር መተሳሰርና አለበት። ሁለተኛው ለእውነት የሚታገልና ድፍረት የተሞላው አመራርና ሰራተኛ ይፈልጋል። ሦስተኛው ቆራጥነት ነው፤ ይህ ጥቆማ የሚሰጡትን ይመለከታል። አራተኛው ‹‹ኮስሞሎጂ›› ነው። ይህ ማለት ምን አገባኝ ከሚል እሳቤ መራቅና እኖራለሁ ብሎ ማሰብ ነው። ስለዚህ ሌብነት ሀጥያት መሆኑን ማወቅ ነው። የመጨረሻው አካባቢን መንከባከብ ነው። አካባቢንና ቤቱን የሚንከባከብ ሰው ከአካባቢው ልማት አይሰርቅም። ስለዚህ የሲንጋፖርን ተሞክሮ ወደ እኛ አገር ማምጣት አለብን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም