አዲስ አበባ፡- ባለፉት አራት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ሲከናወን የቆየው የቢዝነስ ክንውን ማሻሻያ መጠናቀቁንና ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።የአሠራር ማሻሻያዎቹ በተጨባጭ መሬት ላይ እንዲተገበሩ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ትናንት የማሻሻያዎቹን ትግበራ አስመልክቶ በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፤ የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙትን አላስፈላጊ አሠራሮችን ለመፍታትና ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ስምንት አዳዲስ ሕጎችና ከ40 በላይ የአሠራርና አስተዳደራዊ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
የማሻሻያዎቹ ተግባራዊ መሆኑንም በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ከመቅረፍ ባለፈ የግሉ ዘርፍን ጊዜና ገንዘብን በመቆጠብ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ወሳኝ ሚና አለው።
«ማሻሻያዎቹ የንግድ ሥራ ፈቃድ ከማግኘት እና በሥራ ላይ እስካሉ የሚገጥሙ ችግሮችን እንዲሁም የንግድ ተቋምን ለመዘርጋት ባስፈለገ ጊዜ ከዚሁ ጋር ያሉ ሌሎች አሠራሮችን ማቅለል ላይ ያተኮሩ ናቸው» ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ይህም የሀገር ውስጥ አነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ የንግድ ተቋማት ዋነኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ላይ ያሉ ውስብስብ አሠራሮች ማሻሻያ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ሲሆኑ፣ በተለይም የንግድ ስምን በጋዜጣ የማሳወጅ እና የኪራይ ውል የማቅረብን የመሳሳሉት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲነሱ ተደርጓል።
የብድር መረጃ ቋትን በማስፋት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ማካተት ተችሏል።ዘመናዊና ዓለምአቀፍ ይዘቱን የጠበቀ የታክስና የጉምሩክ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን አስተዳደር ሥርዓቶች መገንባታቸውና ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል።
በተጨማሪም የግንባታ ፈቃድ፣ የንብረት ምዝገባና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በዘመናዊ የመረጃ መረብ በታገዘ መልኩና በሕግ በተገደበ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አቶ አበበ አመልክተዋል።
እንዲሁም በፍርድ ቤቶች የንግድ ነክ ክርክሮችን በጥራት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የንግድ ክርክር ችሎቶች ማስፋት እና የጊዜ ገደብና አሠራር መመሪያዎችን የማሰባሰብና የማጠናቀቅ ሥራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፤ በቅርቡ በተደረገ ዓለምአቀፍ ጥናት ከንግድ ምቹነት አኳያ ከ199 አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ 159ኛ ደረጃ መሆኗን አመልክተዋል።ይህም ለኢንቨስትመንት ምቹ አሠራሮች የሌሏት መሆኗን እንደሚያሳይ አስገንዝበው፣ በተለይም በብድር አቅርቦት መረጃ ደካማ ከሚባሉት አገራት መካከል በዋነኝነት እንድትጠቀስ ያደረጋት መሆኑን አብራርተዋል።
ባንኩ የብድር መረጃ ሥርዓት ለማዘመን ባለፉት ሁለት ወራት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።በዚህም ከዚህ ቀደም 22ሺ ብቻ የነበረውን የተበዳሪዎች መረጃ ወደ 6 ሚሊዮን ከፍ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
ይህም ቢሆን ግን የዓለም ባንክ ከሚያስቀምጠው መስፈርት አኳያ ዝቅተኛ የሚባል በመሆኑ በንግድ አሠራሮች ላይ ማሻሻያ በመደረጉ በርካታ ባለሀብቶች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ በማድረግ የአገሪቱን ደረጃ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ተናግረዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የንግድ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው፤ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመን ከዚህ ቀደምም በርካታ አሠራሮች ተግባራዊ ቢደረጉም ወቅቱ ከሚፈልገው አንፃር ውጤታማ መሆን አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል።በተለይም የብድር አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎቶች አሁንም ደካማ የሚባሉ በመሆናቸው የግሉን ተዋናይ ተስፋ እያስቆረጡና ከገበያ እያስወጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በመሆኑም መንግሥት አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎችንና አሠራሮችን ከመዘርጋት ባለፈ በተጨባጭ መሬት ላይ ወርደው ስለመተግበራቸው ማረጋገጥ እንደሚገባው፤ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት ካልተቻለ ዘርፉ አሁን ካለበት ደረጃ በበለጠ እንዲቀዛቀዝና የአገሪቱንም ኢኮኖሚ እንዲዳከም የሚያደርግ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እንዲሰራበት ጠይቀዋል።
የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ይህ አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ከ80 በላይ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን፣ ከአስር በላይ በሆኑ የመንግሥት ተቋማት ስር በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ እቅድ ውስጥ ተካተው የሚተገበሩ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በማህሌት አብዱል