አዲስ አበባ፡- በዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት የሕግ የበላይነትን በሚመለከት መንግሥት ሕጋዊ ሕግ አስከባሪ መሆኑን ዜጎችና የፖለቲካ ምሁራን መገንዘብና ማሳወቅ እንደሚኖርባቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።
አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ ‹‹የሕግ የበላይነት በዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት›› በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የውይይት መድረክ ሃሳባቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ መንግሥት ሕግን በሚያስከብርበት የሕግ አውድና ሕግን በሚያስፈጽምበት ተቋማዊ ሥራ አማካኝነት ሕጋዊ ሕግ አስከባሪ መሆኑን ዜጎችም ሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን ማወቅ፣ ማሰብ፣ መናገርን ማስተማር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
መንግሥት ሕግን የሚያስከብርበት የሕግ አውድና የሚያስፈፅምባቸው ጠንካራ ተቋማት መኖራቸው የአመራሩን የሕግ የበላይነትን ማክበር ወይም በሕግ የመገዛት አዝማሚያ ማሳያዎች በመሆናቸው መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ አቅም እንዳለውም አስረድተዋል።
መንግሥት ሕግ የሚያስከብርበት የሕግ አውድ ሲባል በወጣው ሕግ መሠረት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ሲሆን፤ የተመጣጠነ የኃይል እርምጃ ማለትም ከሕግ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ መሆኑን ልሂቃኑም ይህንን መገንዘብ እንደሚኖርባቸው፤ የነበረው ጭቆና በመነሳቱ እንደ ድል አሊያም እንደተጨማሪ መልካም አጋጣሚ አለመጠቀም አዝማሚያዎች ቢኖሩም፤ ምሁራን በነፃነት ያለምንም ችግር ሃሳባቸውን እንዲያመነጩ እንዲጽፉና እንዲናገሩ የሚያስችል አውድ መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በተቋማት ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይመጣ ሕግን ማስከበርና መጠበቅ በራሱ ሰፊ ሥራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንድን የደህንነትና የጸጥታ ተቋም በአንድ ጊዜ መገንባት አታካች መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በፍርድ ቤት ውስጥ በውሸት ክስ ሰዎች ይፈረድባቸው እንደነበርና ይህንን ለማስተካከል መጀመሪያ ተቋሙን በማስተካከል እንደተጀመረ፤ ተቋሙን ለማስተካከል በኃላፊነት የሚቀመጡ ሰዎችን በመፈለግ ሂደት ውስጥም እያንዳንዱን ተቋም መፈተሽ ትልቁ ሥራ እንደነበር ገልጸዋል።በዚህ ሂደትም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ሥራዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ሕጋዊ ሕግ አስከባሪ የሚሆነው፤ ተሰንዶና ታስቦ በተቀመጠ መልኩ ሕጎችን በማሻሻል የትኛው ሕግ የሕግ የበላይነትን ያስከብራል ብሎ መለየትና የማሻሻል ሥራ ነው ብለዋል።
የጸረ ሽብር፣ የሚዲያና የምርጫ ሕጎች ሲነሱ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር በሚያስችለው የሕግ ማዕቀፍ መሆኑንና ሕጎቹ ሲሻሻሉም ምን ዓይነት ሕጋዊ አውድ ያስፈልጋቸዋል የሚል ጉዳይ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ ዜጎችን ያሳተፈ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን በመናገር፤ የተቋማት ሥነ ልቡናዊ አወቃቀር የተቀረጸበት መንገድ አንደኛውን ጽንፍ የተከተለ መሆኑን፤ በኅብረተሰቡና በጸጥታ አስከባሪዎች መካከል በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ ይህንን መቀየር ትልቅ ሥራና ጊዜ እንደሚፈልግ አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፤ የሕግ የበላይነትን ፍልስፍና መሠረቶች፣ በለውጡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ በተለይ መንግሥት ቅቡልነት የሚኖረው ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ሲችል መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁናዊው ሕግ የማስከበር ቁመናው የማባበልና የሕዝብን ሉዓላዊነት ከማስከበር ይልቅ ወደ አጋፋሪነት ሥራ ላይ ያተኮረ መምሰሉን አንስተዋል።ለግጭት መነሻ የሆኑ ሃሳቦችንና ቅስቀሳዎችን መንግሥት ሞጋች በሆነ መንገድ መታገል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በአዲሱ ገረመው