በሁለት የኃይል አማራጮች የሚሰራ ‹‹ባጃጅ›› የፈጠረው ወጣት

ኢብሳ ጉታ ይባላል። ነዋሪነቱ ወሊሶ ዞን ቀርሳ ማሊማ ወረዳ ነው። ለየት ያለ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የፈጠራ ባለቤት ነው። የኢብሳ የፈጠራ ውጤት የሆነው ይህ ተሽከርካሪ ከሌሎች ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የሚለየው የተሻሻለና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያካተተ ወይም ‹‹ሃይብሪድ›› እየተባለ የሚጠራ የፈጠራ ሥራ በመሆኑ ነው።

ኢብሳ መነሻው ትምህርት ቤት ነው፤ በቆይታው ከሚያያቸው ነገሮች በመነሳት በአካባቢው ያሉ ቁሳቁስን ተጠቅሞ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቹን መጀመሩን ይናገራል። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ሲሞካክር የነበረውን ሃሳቡን በስኬት ሠርቶ መጨረሱ በሌላ የፈጠራ ሃሳብ ላይ ለማተኮር ተነሳሽነት እንደጨመረለት ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪም የመጀመሪያ ሥራዎቹን የተመለከቱ ጓደኞቹ፣ ተማሪዎች እና መምህራኑ የሰጡት የሞራል ድጋፍና ማበረታቻ በይበልጥ ውስጣዊ ፍላጎት እንዲጨምር እንዳደረገው ይገልፃል። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው በፈጠራ ሙያ ላይ ለመስራት ያለው ፍላጎት የበለጠ እየጨመረ መጥቶ አሁን ለደረሰበት ውጤት ትጋቱ ምክንያት እንደሆነው ይናገራል።

በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ትኩረት አድርጎ የፈጠራ ሥራዎች ሲሰራ እንደነበር የሚናገረው ኢብሳ፤ አካባቢው ላይ የሚገኙ ቁሳቁስን በመጠቀም አቅሙንና ችሎታውን ቀስ በቀስ እያዳበረ መምጣቱ የዛሬ ማንነቱን በተሻለ መልኩ እንዲገነባና እምቅ ችሎታውን ማውጣት እንዲችል እንዳገዘው ያስረዳል።

ፈጠራ ውስጣዊ ፍላጎቱ በመሆኑ ቁጭ ብሎ እንኳን እጆቹ ከመስራትና ከመነካካት እንደማይቦዝኑ የሚናገረው ኢብሳ፤ አሁን የሥራው ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ የሆነውን ባጃጅ ለመስራት ያነሳሳው በሀገራችን ያለው የትራንስፖርት ችግር እንደሆነ ይናገራል። “‹በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ያለው የትራንስፖርት ችግር በጣም የከፋ መሆኑን ስመለከት የፈጠራ ችሎታዬን ተጠቅሜ ለዚህ ችግር መፍትሔ በመስጠት ችግሩን መቅረፍ እችላለሁ የሚል ውሳኔ ላይ ደረስኩ›› የሚል ወጣት ኢብሳ አሁን ለሰራው ስራ ምክንያት የሆነው በአካባቢው ያየው ችግር መሆኑን ይናገራል። ለፈጠራ ስኬት ዋናው ቁልፍ ችግር መፍታት እንደሆነም ይገልፃል።

የኢብሳ የፈጠራ ስራ የሆነው የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ‹‹ሃይብሪድ›› የተሰኘበት ዋንኛ ምክንያት ሁለት የኃይል አጠቃቀም አማራጮች ስላሉት ነው። ይህ ማለት ተሽከርካሪው ቤንዚን ወይም ኤሌክትሪክ ከሁለቱ አንዱን አማራጭ በመጠቀም ወይም አንዱ ሲያልቅ አንዱን በመተካት ማሽከርከር የሚያስችል እድል ስለሚፈጥር ነው።

የኢብሳ የፈጠራ ስራው በኢንዱስትሪያል ዲዛይን የተሰራ በመሆኑ ከኢትዮጵያ የእእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት “የፈጠራ ባለቤትነት መብት” ማግኘት ችሏል። እርሱ እንደሚለው ይህ ተሽከርካሪ በሁለቱም ዘዴዎች (ሲስተሞች) በመጠቀም መንቀሳቀስ ይችላል። አሁን አሁን በአገራችን ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱና በከተማዋም በስፋት እየተሰራጩ ከመሆኑ አንፃር የእርሱ ስራ በቶሎ ተቀባይነት የሚያገኝበት እድል ሰፊ ነው።

“እስካሁን በሀገራችን ተሽከርካሪዎች አይመረትም፤ ይገጣጠማሉ እንጂ” የሚለው ኢብሳ፤ ወደፊት ኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎችን ማምረት እንድትችል የእርሱ የፈጠራ ውጤት እንደ መነሻ ሊሆን እንደሚችል እምነት አለው። በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ በሀገር ውስጥ መስራት ከተጀመረ ይህን በማሳደግ ባለአራት እግር ተሽከርካሪዎችን ማምረት የሚቻልበት አጋጣሚ መፍጠር እንደሚቻል ይናገራል። ለዚህ ስኬትም የእርሱ ስራ ትልቅ ምሳሌና መነሻ መሆን እንደሚችል ይናገራል።

የፈጠራ ሥራውን ለመስራት ሁለት ዓመታት ያህል እንደፈጀበት የሚናገረው ኢብሳ፤ የተለያዩ ቁሳቁስን ተጠቅሞ በመገጣጠም እንደሰራውም ተናግሯል። የተሽከርካሪው 60 በመቶ የሚሆኑት የመኪና እቃዎች ከተለያዩ ነገሮች ተወስደው የተሰሩ የራሱ ፈጠራ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ 40 በመቶ ያህሉን ደግሞ ‹‹ዳማስ›› በመባል መጠሪያ የምትታወቀውን መኪናና የተለያዩ ብረታ ብረቶች እቃዎችን ተጠቅሞ እንደሰራው ይገልጻል።

የባጃጁ የውጪ ክፍል (body) የተገጣጠመው ከተለያዩ ብረታ ብረቶች እንደሆነ ይገልጻል፤ እነዚህን የመኪና እቃዎች ‹‹ሽት ሜታል›› ከሚባሉና “ዩ ቻናል” በመባል ከሚታወቁ ብረታ ብረቶች እንደሚሰራቸው ጠቅሶ፣ የባጃጁን ‹ሻንሲ›ም እንዲሁ የራሱ የፈጠራ ውጤት እንደሆነ ነው ኢብሳ የሚገልጸው። ይህንን ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ለመስራት የሚያስፈልጉት ጥሬ እቃዎች ትላልቅና ጠንካራ የብረት አይነቶችን በመጠቀም ወይም ባጃጆች ለመገጣጠም የሚያገለግሉትን የተለያዩ ቁሳቁሶች በመጠቀም በራሱ የፈጠራ ዲዛይን በመጠቀም ባለሦስት እግር ተሽከርካሪውን (ባጃጁን) መስራት ችሏል።

ባለሦስት እግር ተሽከርካሪውን (ባጃጅ) ሰርቶ በቤንዚንም ሆነ በኤሌክትሪክ ተጠቅሞ ፍተሻ አድርጓል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ለራሱ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተጠቀመበት እንደሚገኝም ነው ኢብሳ የሚናገረው። ኢብሳ ባጃጁን ለመስራት 300 /ሶስት መቶ/ ሺ ብር እንደፈጀበትም ይገልጻል። አሁን ላይ ይህንን ተሽከርካሪ ሰርቶ ለገበያ ለማቅረብ ባለው የዋጋ ግምት 430 ሺ የሚሆን ብር እንደሚያስፈልግም ይገልጻል። ይህ ተሽከርካሪ ‹‹ሃይብሪድ›› (በቤንዚልና በኤሌክትሪክ) በመስራቱ በገበያ ላይ ካሉት ተሽከርካሪዎች ለየት እንደሚል ጠቅሶ፣ አሁን በገበያ ላይ ያሉ ሌሎች ባጃጆች ከ380 ሺ እስከ 400ሺ ብር እንደሚሸጡ ይጠቁማል።

የባጃጁ የውጪ ክፍል /ቦዲ/ እንደ ሌሎች ባጃጆች ሳይሆን፣ የተለየ ነው የሚለው ኢብሳ፤ ተሽከርካሪው ራሱን የቻለ የውስጥ ክፍል (body) እንዳለውም ይናገራል፤ የውስጥ ክፍሉ (body) መስታወት እንደተገጠመለትም ይገልጻል። ይህ ደግሞ የተሳፋሪዎችን ፍላጎት የሚያሟላና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ ምቹ ተሽከርካሪ እንደሆነ ማሳያ ነው ይላል። ባጃጁ በጠጠር /ፒስታ/ መንገድ ላይ አቧራ እንዳይኖረውና የተሳፋሪው ምቾትና ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን እንደሚያደርግ ይገልፃል።

ኢብሳ እንደሚለው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ ‹‹ሃይብሪድ›› ስለሆነ ብዙ ነዳጅ አይፈጅም። በኤሌክትሪክ ብቻ ለመንዳት ከተፈለገ ደግሞ ኤሌክትሪኩ አንዴ ብቻ ቻርጅ ከተደረገ በኋላ 120 ኪሎ ሜትር ማሽከርከር ያስችላል። ነዳጅ በመጠቀም የሚሽከረከር ከሆነ ደግሞ በአንድ ሊትር ቢንዚን 20 ኪሎ ሜትር መሄድ ይቻላል።

ረጅም መንገድ ለመጓዝ የሚፈልግ ሰው ጉዞውን ሲጀምር በኤሌክትሪክ ተጠቅሞ እየነዳ ከሆነና በጉዞ ላይ እያለ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ቢያልቅበት በኤሌክትሪክ የሚያደርገውን ጉዞ ወደ ነዳጅ በመቀየር በቤንዚን ተጠቅሞ መጓዝ የሚችልበት ቀላል አማራጭ ይኖረዋል፤ ሲል ኢብሳ የባጃጁን ለየት ያለ መሆን ያብራራል። በኤሌክትሪክ ወደ ነዳጅ፤ ነዳጅን ወደ ኤሌክትሪክ ለመቀየር የሚደረገው ሂደት በባጃጁም ሆነ በአሽከርካሪው እንዲሁም በተሳፋሪው ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያስከትልም ይናገራል። ከሌላው ተሽከርካሪ በተለየ መልኩ አንዱ ሲያልቅ ሌላውን መጠቀም የሚችልበትን ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ይገልጻል። የባጃጁ ሞተር (engine) ችግር ካላጋጠመው በስተቀር እንደፈለገው መጓዝ እንደሚችልም ያብራራል።

ባጃጁን የመስራት ሀሳቡ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ የፈጠራ ሥራውን ለመስራት አስቀድሞም ጥናት ለማካሄድ እንዲሁም የፈጠራ ሥራውን በፕሮቶታይፕ ደረጃ ለማውጣት ረጅም ጊዜ እንደወሰደበትም ነው የሚናገረው።

ባጃጁን ለመሥራት በሚያደርገው ጥረት ከጎኑ ሆነው በሞራልም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ ያደረጉለትን አካላት እንዳሉም ጠቅሷል። እሱ እንዳለው፤ በቅርበት በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ቀበሌ፣ ወረዳና የኦሮሚያ ክልል የሚመለከተው ቢሮ እገዛና ድጋፍ አድርገውለታል። በተለይ የትምህርት ቤቱ መምህራን በቴክኒካል ሥራዎቹ ላይ በቅርበት እገዛ እንዳደረጉለት ጠቅሶ፣ ሰዎች የሚሰጡት ማበረታቻና ድጋፍ ጥረቱን እንዲቀጥልበት ማበረታቻ እንደሆኑት ይናገራል።

በ‹‹ሃይብሪድ›› ባጃጅ የፈጠራ ሥራው በብሩህ ኢትዮጵያ ውድድር ላይ ሊቀርብ የሚችልበት እድል ማግኘቱ የፈጠራ ስራውን ተግባር ላይ እንዲያውል እንደሚያግዘው ነው ኢብሳ የሚናገረው። ይህ የውድድር መድረክ በእቅድ የያዘውን ሥራ ለማሳካት የሚችልበትን እድል እንደሚያሰፋለት ጠቁሟል።

ወደ ብሩህ ኢትዮጵያ ውድድር ከመጣ በኋላ ባገኘው ስልጠና በፈጠራ ሥራዎቹ ላይ ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲመለከትና ማሻሻል ያለበትን እንዲያሻሽል ትልቅ እድል እንደፈጠረለት ጠቅሶ፣ ‹‹ስልጠናው አሁንም በጣም ረድቶኛል፤ ወደፊትም ለሥራዬ ትልቅ ብርታት ሆኖኛል›› ይላል።

በቀጣይም ሊሰራቸው ያሰባቸው በርካታ እቅዶች እንዳሉት ጠቅሶ፣ የፈጠራ ውጤቱ የሆነውን ባጃጅ ወደ ማምረት ሂደት ውስጥ ለመግባት አልሞ እየሰራ መሆኑን ይናገራል። ይህ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ እንዲመረትና ከውጭ የሚመጡት የባጃጅ መገጣጠሚያ እቃዎች (በተለይ ባጃጅ RE የሚባሉ ከህንድ ሀገር የሚገቡ) ማስቀረት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አስታውቋል።

የፈጠራ ውጤቱን በሀገር ውስጥ በማምረትና በመገጣጠም የትራንስፖርት ችግርን ከመቅረፍም በላይ፤ ለባጃጅ መገጣጠሚያ የሚውሉ ከውጭ የሚመጡ እቃዎች በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማዳን እንደሚያስችል ጠቁሟል። አዲሱ የፈጠራ ሥራ የሚገጣጠምባቸው እቃዎች ከሞተሩ /ኢንጂኑ/ በስተቀር በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻልም ይጠቁማል። ሞተሩም ቢሆን ከውጭ እንደመጣ እንደማይገጠም ጠቅሶ፣ የፈጠራ ችሎታውን ተጠቅሞ ማሻሻያ እንደሚያደርግበት ነው የሚናገረው።

ይህንን የፈጠራ ውጤት በሀገር ውስጥ የመስራት ራዕይ አንግቦ እየሰራ ያለው ኢብሳ እንደሚለው በተለይ ለባጃጁ የሚሆነውን መለዋወጫ (ስፔር ፓርት) በበቂ ሁኔታ ማምረት ከእሱ እንደሚጠበቅ ይገልጻል።

‹‹ይህንን የፈጠራ ሥራ ስሰራ ተስፋ መቁረጥን ጨምሮ ብዙ አይነት ተግዳሮቶች አጋጥመውኝ ነበር›› የሚለው ኢብሳ፤ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ችሎታቸውን አውጥተው ተቀባይነት እስኪያገኙ ድረስ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በትግስት ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዝባል። እርሱም ይህንን ስኬታማ የፈጠራ ሥራ ለመስራትና ውጤት ላይ ለመድረስ ብዙ ጥረትና ትእግስት እንደሚጠይቅ ትምህርት መውሰዱን ይናገራል። በተለይ ወጣቶች የፈጠራ ባለሙያዎችም ሆኑ በውስጣቸው የፈጠራ ሀሳብ እያላቸው ይዘውት የተቀመጡ ወጣቶች ብርታትና ጥንካሬ ሊኖራቸው ይገባል ሲል አስገንዝቧል። ‹‹እነሱ በፈለጉት ሰዓት ባይሳካላቸው፤ በጊዜ ሂደት የሚፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ በማወቅ በትግስት ሊጠብቁ የግድ ይላቸዋል›› ሲል ምክረ ሀሳቡን ለግሷል።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *