አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ የፋይናንስ ደህንነት ተቋማት ህብረት የሆነው የዓለም አቀፉ ኢግሞንት ግሩፕ አባል ስትሆን በውጭ አገራት በሕገወጥ መንገድ የተቀመጡ ገንዘቦቿን ማስመለስ እንደምትጀምር የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ገለጸ።
የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አስፈላጊ ዝግጅቶች በመጠናቀቃቸው ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ 159 አገራት የፋይናንስ ደህንነት ተቋማትን በአባልነት የያዘው ኢግሞንት ግሩፕ አባል ትሆናለች። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ሙስናን ጨምሮ በሕገወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ገንዘቦችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት አባል አገራቱ ሙሉ መረጃ በመስጠት እና በማስመለስ ረገድ ትብብር ማድረጋቸው አይቀርም።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ደህንነት ተቋም (ኢግሞንት ግሩፕ) አባል አገራት መካከል ሙስናን ጨምሮ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን የመከላከል ግዴታ ተጥሏል።
በመሆኑም በውጭ አገራት ባንኮች እና በተለያዩ ቦታዎች የተከማቹ ገንዘቦች ለማስመለስ የሚያስችል አቅም ስለሚፈጠር ገንዘቡ ወደአገር እንዲመለስ ይደረጋል። በቀጣይ ዓመት ስዊዝ ባንክም ሆነ የትኛውም አገር ላይ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ከኢትዮጵያ የወጣ ገንዘብ ካለ መረጃ ተሰብስቦበት በመጀመሪያ መጠኑ እንዲታወቅ ይደረጋል። ከዚያም የማስመለስ ሥራው ከየመንግሥታቱ እና ተቋማቱ ጋር ይካሄዳል።
በሌላ በኩል የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ አጠራጣሪ የሆኑ ግብይቶች እና የገንዘብ ዝውውሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደደረሱት አቶ እንዳለ ገልጸዋል። በሙስና፣ በግብር ማጭበርበር፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎችም ወንጀሎችን የያዘው ጥቆማ ዝርዝር መረጃ ተሰብስቦበታል። 52 ጉዳዮችም አስፈላጊው መረጃ ተጠናቅሮባቸው ጉዳያቸው ወደ ፖሊስ መላካቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ እንዳለ ከሆነ፤ ማዕከሉ በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ገንዘቦችን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመከላከል በኢትዮጵያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማትን የገንዘብ ዝውውሮች መረጃ ይተነትናል።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጥርጣሬ የታየባቸው የስድስት ቢሊዮን ብር መጠን ያላቸውን ጉዳዮች አጣርቷል። እያንዳንዱ ባንክ፣ ኢንሹራንስ እና ቁጠባ ተቋማት በየቀኑ የሚደረገውን ከ300 ሺ ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ዝውውር እና ጥርጣሬ የታየባቸውን መረጃዎች እያቀረቡ በመሆኑ የገንዘብ ዝውውሮች ከሕገወጥነት ጋር እንዳይያያዙ ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል።
እንደ ማዕከሉ መረጃ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ እና ቁጠባ ተቋማት፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የተፈቀደላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች፤ በቤት ግንባታ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ የገቢዎች እና የጉምሩክ ተቋማት ለፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የገንዘብ ልውውጣቸውን የሚመለከት ሪፖርት የመላክ ግዴታ በሕግ ተጥሎባቸዋል። እስከአሁን ግን እያንዳንዱን የሒሳብ ባለሙያ እና ኦዲተሮች መረጃ ለማዕከሉ የሚያቀርቡበት ልምድ አልተፈጠረም።
መቀመጫውን ቤልጂየም ብራሰልስ ያደረገው ዓለም አቀፉ ኢግሞንት ግሩፕ አሜሪካን ጨምሮ 159 አገራት የፋይናንስ ደህንነት ተቋማትን በአባልነት የያዘ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በጌትነት ተስፋማርያም