አዲስ አበባ፡- ከዛሬ 42 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የሜይዴይን በዓል ለማክበር በወጡ ወገኖች ላይ የደረሰውን የግፍ ጭፍጨፋ ለማስታወስ ዕለቱ በፓናል ውይይት ታስቦ እንደሚውል ተገለጸ።
የቀይሽብር ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር ትናንት በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ ደራሲ ሀይለመለኮት መዋዕል እንዳስታወቁት፤ ሚያዝያ 21 ቀን 1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሜይዴይን በዓል ለማክበር በወጡና የደርግ መንግሥትን አገዛዝ በተቃወሙ በርካታ ሰዎች ላይ በጥይት የታገዘ ግፋዊ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል።
እንደ አቶ ሀይለመለኮት ገለፃ፤ በዕለቱ በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች በተደረገው ግድያ ቁጥራቸው ከአምስት መቶ በላይ የሚገመት ወገኖች ሕይወት ያለፈ ሲሆን በበርካታ ሰዎች ላይም አካላዊ ጉዳት ደርሷል።
በወቅቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰማዕታት ቤተሰቦች አስከሬንን ለመውሰድ የጥይት ዋጋ የተጠየቁ ሲሆን በሕይወት የተረፉትም እስርና እንግልት ደርሶባቸዋል። ይህን መሠረት በማድረግም «መቼም፣ የትም፣ እንዳይደገም» በሚል መርህ ማህበሩ ተቋቁሟል፡፡
የቀይሽብር ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጳውሎስ ሶርሳ በበኩላቸው፤ ዕለቱን ለማስታወስ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ቀኑ አይሬሴ ክስተት የተፈፀመበት በመሆኑና ለአዲሱ ትውልድ ያን ታሪክ ለማሳወቅና እንዳይደገም ለማድረግ ነው። ይህ ቀን ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም «ቀይሽብርና ሰላም» በሚል የፓናል ውይይት የሚከበር ሲሆን በዕለቱም «ያ ትውልድ» በሚለው መጽሐፋቸው የሚታወቁት አቶ ክፍሉ ታደሰ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ