የኩታ ገጠም አቮካዶ ልማት ተሞክሮ – በሉሜ ወረዳ

 የአፈሩ መጥቆር፣ ሽታና ልስላሴ፣ ተፈጥሮ ለአካባቢው ያበረከተችውን ጸጋ ያመለክታሉ:: ከማለዳ ጀምሮ የጣለው ዝናብ ያረሰረሰው ይህ አፈር የተመልካችን ቀልብ ይስባል:: የአፈሩ ለምነት ማሳው ለሰብልም ሆነ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል::

የጤፍ፣ ስንዴ፣ ጥራጥሬና የተለያዩ ሰብሎች ልማት ሲከናወንበት የኖረው የዚህ ማሳ ምርታማነት ከፍተኛ መሆኑን የማሳው ባለቤቶች ሲዲሶ ሞጆና ንጉሤ ለማ ይገልጻሉ:: አርሶ አደሮቹ የተለያየ ሰብል ሲያመርቱበት የኖሩትን ይህን ማሳቸውን በዘንድሮው የምርት ዘመን ለአቮካዶ ተክል ልማት አውለውታል::

በአርሶ አደር ሲዲሴና ንጉሤ የእርሻ ስፍራ ማልደን ነው የተገኘነው:: ሁለቱም ማሳቸውን ለአቮካዶ አትክልት ልማት ለማዋልና በኩታገጠም የግብርና ዘዴ ለማልማት ተስማምተው በፍቃደኝነት ወደ ልማቱ መግባታቸውን ይናገራሉ::ወደ ልማቱ እንዲገቡ በአካባቢው ከእነርሱ ቀድመው የአቮካዶ ልማት የጀመሩ አርሶ አደሮች መነሻ እንደሆኗቸውም ይጠቅሳሉ:: ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን አትክልትና ፍራፍሬ ማልማቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው እነዚህ አርሶ አደሮች ምሳሌ እንደሆኗቸውም ነው የነገሩን::

የአካባቢው አየር ፀባይ፣ መሬቱም ለልማቱ ምቹ እንደሆነና የከርሰ ምድር ውሃም መኖሩን አረጋግጠው ነው አርሶ አደር ሲዲሴና ንጉሤ ወደ ልማቱ ለመግባት ውሳኔ ላይ የደረሱት:: ወሰንተኛ መሆናቸውም ልማቱን ተጋግዘው ስኬታማ ለማድረግ ያስችለናል የሚል እምነት አድሮባቸዋል::

ይህ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ሽራ ዲባዲባ ቀበሌ አካባቢ ለአቮካዶ አትክልት ልማት ተስማሚ መሆኑን ከአርሶ አደሮቹ ተረድተናል፤ አርሶ አደር ንጉሤ ለማ፤ ከተዋሳኛቸው አርሶ አደር ሲዲሴ ጋር በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ አቮካዶ ለማልማት የወሰኑት ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ተገንዝበው መሆኑን ይገልጻሉ::

ልማቱን በኩታ ገጠም ነው የሚያካሂዱት:: ይህም ሁኔታ በልማቱ ወቅት የሚያስፈልጓቸውን ግብአቶች በጋራ ለመጠቀም፣ ተመካክሮ ለመሥራት፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታት እንዲሁም የተከሉት የአቮካዶ ችግኝ ምርት መስጠት ጀምሮ ለገበያ ሲደርስም ምርታቸውን ለሚረከቡ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ በአጠቃላይ በሀሳብና በቁሳቁስ ለመረዳዳት እንደሚያስችላቸው ይገልጻሉ:: ስለኩታገጠም የግብርና ዘዴ ጥቅምና አስፈላጊነት በባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አግኝተዋል፤ ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢያቸው ቀድመው ወደ ልማቱ የገቡት አርሶ አደሮች ተሞክሮ ማየታቸውን ሌላው ወደ ልማቱ እንዲሳቡ ያደረጋቸው ምክንያት መሆኑን አርሶ አደር ንጉሤ ያብራራሉ::

አርሶ አደር ንጉሤ የሰብል ማሳቸውን ለአቮካዶ ተክል ልማት ለማዋል ሲወስኑም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው በማሰብ ነው:: እርሳቸው እንዳሉት፤ ከእርሳቸው የሚጠበቀው ጠንክሮ መሥራት ብቻ ነው:: ልማቱ ውሃ ስለሚፈልግ የጉድጓድ ውሃ ማውጣት እንዲሁም ተከታትሎ እንክብካቤ ማድረግ ከሚጠበቅባቸው ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው::

ልማቱ በገንዘብም በጉልበትም አቅም ይፈልጋል:: በተለይም የጉድጓድ ውሃ ከመሬት ለማውጣት እስከ ሦስት መቶ ሺ ብር ሊፈልግ ይችላል:: ለሰው ጉልበትም ገንዘብ ያስፈልጋል:: ከጉድጓድ ውስጥ ውሃ ስቦ ወደ ማሳው ለማድረስ የሚያስችል የውሃ መሳቢያ ሞተር ዋጋም እንዲሁ በተመሳሳይ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል:: እነ አርሶ አደር ንጉሤ ለዚህም ያሰቡት በኩታገጠም የግብርና ዘዴ የገንዘብና የጉልበት አቅማቸውን ማቀናጀትን ነው::

ልማቱ ከእነርሱንም አልፎ ሀገርንም እንደሚጠቅም ታሳቢ በማድረግ በአቅም የሚያግዛቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም እንዲተባበሯቸውም አርሶ አደሩ ጠይቀዋል:: ድጋፉ ቢገኝ የሚል ሀሳብ እንጂ ልማቱን ከዳር አድርሰው ውጤቱን ለማየት ግን በእርሳቸው በኩል ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት::

አርሶ አደር ሲዲሴ ሞጆም ጠንክራ በመሥራት ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀቷን ትናገራለች:: ለአቮካዶ አትክልት ልማት ያዘጋጀችው ማሳ የቤተሰብ ቢሆንም ኃላፊነቱ የእርሷ እንደሆነ የምትገልጸው አርሶ አደሯ፣ ወደ አቮካዶ አትክልት ልማት ለመግባት ስትወስንም ተጠቃሚነቷ ከፍ እንደሚል ቀድማ ግንዛቤ በመያዝዋ መሆኑን አስታውቃለች::

አርሶ አደሯ እንዳለችው፤ አቮካዶ በምታለማበት ማሳ ላይ ቲማቲም፣ሽንኩርት፣ ድንችና ሌሎች የተለያዩ አትክልቶች፣ እንደ ጥቁር አዝሙድ ያሉ ቅመማ ቅመሞችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል በባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል:: አንዴ የተተከለው የአቮካዶ ተከል ፍሬ መስጠት ከጀመረ ለረጅም ጊዜ በማፍራት ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚያስችልም ያገኘችው ግንዛቤ ለልማቱ የበለጠ አነሳስቷታል::

በዚህ ልማት አካባቢዋ ላይ ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ብትሰማም የአቮካዶ ልማታቸውን ግን እንዳላየች ነው የነገረችን:: ለማየት ዕድሉን ባታገኝም ውጤታማ እንደሚያደርጋት ግን እርግጠኛ ሆናበታለች:: ከልማቱ ቱሩፋት ተጠቃሚ ለመሆን በትእግሥት መሥራት እንደሚያስፈልግና ጊዜዋን ሰጥታ ለመሥራት መዘጋጀቷንም ተናግራለች::

ሲዲሴ ወጣት ናት:: ለግብርናው ሥራ ያላት ፍላጎትም ከፍተኛ ነው:: በኩታገጠም የግብርና ዘዴም አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት የመጀመሪያዋ እንደሆነም በመጥቀስ፣ ኩታገጠም ልማት መረዳዳት የሚታይበትና አቅምንም ለማቀናጀት መልካም እንደሆነ ከጅምሩ እንደተረዳችም ገልጻለች:: በዚህ የግብርና ዘዴ የተሻለ ውጤት እንደምታገኝበትም ተስፋ አድርጋለች:: ይህን የኩታ ገጠም አሠራር ወደፊት በሰብል ልማት ላይም ለመተግበር ጠቃሚ ሆኖ አግኝታዋለች::

ትምህርታዊ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በክትትልና ድጋፍ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የሉሜ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ከጎናቸው እንደሆነም በወረዳው የአትክልትና ቅመማ ቅመም ቡድን መሪ አቶ ጌቱ ካሳ ይገልጻሉ:: እንደ አቶ ጌቱ ማብራሪያ፤ በአካባቢው ላይ በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ እየተከናወነ ያለው የአቮካዶና አትክልት ልማት ‹‹ቢርቢርሳ ጎሮ›› በሚል ስያሜ ነው እየተከናወነ ያለው:: በአካባቢው የአቮካዶ ልማት ከተጀመረ ስድስተኛ አመቱን ይዟል::

የአቮካዶ ተክል ፍሬ ለመስጠት አራት አመት ይፈልጋል:: አንዴ ምርት መስጠት ከጀመረ ግን ከፍተኛ ምርት ይሰጣል:: አንዱ የሌላውን በማየት ወደ ልማቱ  የሚገባው አርሶ አደር ቁጥር ከአመት አመት እየጨመረ ይገኛል፤ በአንድ አርሶ አደር የተጀመረው ልማት በአሁኑ ጊዜም ወደ 160 የሚሆኑ አርሶ አደሮችን መሳብ ችሏል::

በዚሁ መሠረትም በመጀመሪያ ከደረሰው የአቮካዶ ምርት ወደ 92 ነጥብ ሁለት ኩንታል አቮካዶ ማግኘት ተችሏል፤ ምርቱንም ለውጭ ገበያ በማቅረብ አልሚዎች ተጠቃሚ ሆነዋል:: ዘንድሮ ምርቱ በብዙ እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል፤ ይህንንም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅራቢዎች (ኤክስፖርተሮች) እየጠበቁ ናቸው:: ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ብቻ በ18 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ የአቮካዶ አትክልት ይገኛል::

ከአንድ ዛፍ የሚገኘው የምርት መጠን ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ከአንድ የአቮካዶ ዛፍ አንድ ነጥብ አምስት ኩንታል እንደሚገኝ አስረድተዋል::የአቮካዶ ተክል ውሃ ካገኘና ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገለት ምርታማነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የገለጹት::

በኩታገጠም ብቻ በዚህ አመት በ12 ሄክታር መሬት ላይ የአቮካዶ ችግኝ ተከላ መከናወኑን አቶ ጌቱ ጠቅሰው፣ በኩታገጠም በወረዳው አስር ቀበሌ ውስጥ ልማቱ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል:: አካባቢው ለልማቱ ምቹ መሆኑና ሌሎች የግል አልሚዎችም ቢገቡ ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል::

ለአርሶ አደር ሲዲሴና ንጉሤ ጽሕፈት ቤቱ እያደረገ ስላለው ድጋፍ አስመልክተው እንደገለጹት፤ ለአርሶ አደሮቹ በጽሕፈት ቤቱ በኩል የሙያ እገዛ እየተደረገላቸው ነው፣ የችግኞች አቅርቦት፣ የገበያው ሁኔታና ምርቱ ግን አልተጣጣመም:: ተወዳዳሪ የሆነ ላኪ (ኤክስፖርተር) ለማግኘት በተለይ በዚህ አመት ተግዳሮት ገጥሟቸዋል:: ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት እና ለሀገር ውስጥ የሚቀርብበት ዋጋም አለመመጣጠን እንዲሁ ፈተና ሆኖባቸዋል:: ለውጭ የሚቀርበው በዝቅተኛ ዋጋ ነው:: ይህ ደግሞ በአርሶ አደሩ በኩል ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል:: ኃላፊው በዚህ በኩል ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል::

በአካባቢው ላይ እየተከናወነ ያለው የአቮካዶ አትክልት ልማት እንደ ሀገር ለተያዘው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር አጋዥ ይሆናል:: የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሠራተኞችም ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር መሠረት በማድረግ በኩታገጠም የግብርና ዘዴ ልማት በጀመሩት የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የአቮካዶ ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን አሳርፈዋል:: የኢንስቲትዩቱ እንቅስቃሴ ዐሻራ ከማሳረፍም በላይ በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ የሚያለሙ አርሶአደሮችንም እየደገፈ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈስ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እንዲጠናከር በተለይም በአቮካዶ በሙዝና በፓፓያ ፍራፍሬዎች ልማት በችግኝ አቅርቦት በሥልጠና እና የተለያየ ድጋፍ በማድረግ ያግዛል።

አርሶ አደሩ ከሰብል ልማት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ በሚያስችለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የአረንጓዴ ዐሻራውንም እንዲያሳርፍ የሚያስችል ጭምር እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ይፍሩ፤ ኢንስቲትዩቱ የኩታገጠም የግብርና ዘዴ ላይ ድጋፍ በማድረግ የማበረታታቱን ሥራ ከጀመረ አራተኛ አመቱን መያዙንም አመልክተዋል::

በአትክልትና ፍራፍሬዎች በኩታገጠም የግብርና ዘዴ እየተከናወነ ካለው የልማት ሥራ በተጨማሪ በጤፍ፣ ስንዴ፣ የገብስ ብቅል፣ አኩሪአተርና ሰሊጥ የሰብል ዓይነቶች በኩታገጠም እንዲለማ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በድምሩ በኢንስቲትዩቱ ድጋፍና ክትትል በኩታገጠም ማሣ ላይ አስር ዓይነት ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬዎች እየለሙ መሆናቸውን አስረድተዋል::

እስካሁን የተደረገው ድጋፍም አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢንስቲትዩቱ ከአራት አመት በፊት ድጋፍ አድርጎላቸው ማምረት የጀመሩ የአቮካዶ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ገልፀዋል። ቀድመው የጀመሩትን በማየት የተበረታቱ አርሶ አደሮች ወደ ልማቱ እየገቡ እንደሆነም ጠቁመዋል::

እንደ ዶክተር ይፍሩ ማብራሪያ፤ ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ እያደረገላቸው በኩታ ገጠም የሚያለሙትን የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው በማድረግ ጭምር እገዛውን በማጠናከር እስከ ኩባንያ ደረጃ የማድረስ ዓላማ ነው ያለው:: ኩባንያ ደረጃ ከደረሱ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ፈጥረው ሥራውን ያስቀጥላሉ የሚል እሳቤ ይዟል:: ኢንስቲትዩቱ በስምንት አመት ጊዜ ውስጥ ወደ ኩባንያ ደረጃ ለማድረስም ነው አቅዶ እየሠራ የሚገኘው:: እዚህ ደረጃ ለማድረስም በአምስት የክትትልና ድጋፍ ሥራው፣ በአምስት ምዕራፎች ውስጥ እንዲያልፍ መደረጉን ነው የገለጹት::በዚህ ደረጃ የሚታሰቡት አርሶ አደሮች የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየሠራ ነው::

ኢንስቲትዩቱ የኩታገጠም የልማት ሥራውን እየሠራ የሚገኘው በአማራ፣ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ውስጥ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ይፍሩ፤የልማት ሥራውንም ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር በማስተሳሰር አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን የኢንስቲትዩቱን ሠራተኞችንም በማሳተፍ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በየአመቱ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር እንደሚያከናውን ገልጸዋል::

ኢንስቲትዩቱ በኩታገጠም የግብርና ዘዴ ልማቱን ለማጠናከር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዕድሉን ተጠቅመው ለስኬት የሚበቁ አርሶ አደሮች ሌሎችን ለማበረታታት እንደሚያግዙም አመልክተዋል:: እስካሁን በተሠራው ሥራም የኩታ ገጠም የግብርና ዘዴን አስፈላጊነት በአርሶ አደሩ ውስጥ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል::

በሥራ ውስጥ ስላጋጠሙ ተግዳሮቶች ዶክተር ይፍሩ እንደገለጹት፤ የፋይናንስ አቅርቦት ከፍተኛው ተግዳሮት ነው ብለዋል:: ለግብርና ሥራ ብድር የሚሰጥ ባንክ አለመኖር ችግሩን እንዳባበሰው፣ አርሶ አደሮችም ተቋም አለመሆናቸው ለባንክ አሠራር ምቹ ሆኖ አልተገኘም ነው የሚሉት::

እሳቸው እንዳሉት፤ ችግሩ ወደፊት በዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መሆን ይፈታ ተብሎ ይጠበቃል:: ሌላው የግብርና ሜካናይዜሽንን ጨምሮ የዘርና አስፈላጊ የሆኑ የግብአት አቅርቦት አለመኖር ነው:: ከዝናብ ጥገኝነት አለመላቀቅም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያስቻለ አይደለም::

ኢንስቲትዩቱ በኩታገጠም የግብርና ዘዴ ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሮችን ወደ ኩባንያ ደረጃ ለማሳደግ ሲንቀሳቀስ መነሻው ምን እንደሆነም ዶክተር ይፍሩ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የመሬቱ ምቹነት፣ የአርሶአደሩ ፈቃደኝነትና ሌሎችም ነገሮች በጥናት ተለይተውና የሌሎች ሀገሮችም ተሞክሮ ተቀምሮ ነው ወደ ሥራ የተገባው ይላሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ በኩታገጠም ለመንቀሳቀስም ቢያንስ 15 ሄክታር መሬት መዘጋጀት አለበት:: ይህን ለማሟላትም ቢያንስ 30 የሚሆኑ አርሶ አደሮች መቀናጀት ይኖርባቸዋል:: የኩታ ገጠም ግብርና ዘዴ ዋና ጥቅም መሬት በማሰባሰብ ወጪን በመቀነስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን መቻል ነው:: በዚህ ዘዴ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን አመጋገቡ ላይም ለውጥ እንዲያመጣ ማስቻል ነው::

 ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *