አካባቢው በጦርነት ስጋት ተወጥሯል። የትናንቱ ሰላማዊ መንደር ዛሬ መድፍና መትረየስ እያውካካበት ነው። ምሽግ ውስጥ የተደበቁ ነዋሪዎች ሰማይና ምድሩን እያመኑት አይደለም። አሁን የእግር ኮሽታ እንኳን ያስደነብራል። ሕፃናት ይቦርቁበት የነበረው ደማቅ ሰፈርም በጭርታ ተውጦ ሕይወት አልባነቱን ይመሰከር ይዟል። 1969 ዓ.ም ሐረር።
ምሽጉ ከደበቃቸው ነዋሪዎች አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው። በርካቶቹ እናቶች ልጆቻቸውን ከተባራሪ ጥይት ለመከላከል በምሽጉ እንዳደፈጡ ውለው ያድራሉ። ከነዚህ መሀል አብዛኞቹ ባሎቻቸው ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱ የወታደር ሚስቶች ናቸው። ወቅቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ለመመከት የሞት ሽረት ትግል የገጠመችበት ፈታኝ ጊዜ ነበር።
ሀገር ለመውረር ድንበር ጥሰው የዘለቁት የዚያድባሬ ወታደሮች ለሐረርና አካባቢው ድንገቴ ሆነዋል። ይህ አጋጣሚም መላውን ነዋሪ አሸብሮ ክፉኛ አደናግጧል። በምሽጉ ቀናትን የገፉ ሕፃናት በለቅሶና ዋይታ መራኮት ከጀመሩ ቆይተዋል። እንዲህ ለመሆናቸው ዋንኛ ምክንያት ደግሞ ቀናትን ያለበቂ ምግብና ውሃ የማሳለፋቸው እውነት ነበር። ካጠገባቸው ያሉ እናቶች በልጆቻቸው ስቃይ አብረዋቸው እያነቡ ነው። «እማማ ራበኝ» ለሚል ጨቅላ ከሞሰባቸው ቆርሰው ማጉረስ ያለመቻላቸው ሆድ አስብሷቸዋል።
ከእነዚህ እናቶች መሀል ግን የአንደኛዋ ሁኔታ ከሌሎች የተለየ ሆነ። ተርበው የሚያለቅሱ ልጆቿን ዕንባ ማየት አልተቻላትም። የሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ማባባሉ በእጅጉ ከበዳት። በድንገት ከነበረችበት ተነሳችና «መጣሁ» ብላቸው ወጣች። ከምሽጉ ብቅ እንዳለችም በአቅራቢያው ለተኩስ ከተዘጋጀው መድፍ ጋር ተፋጠጠች። ይህ ሁሉ ግን ለእሷ ምኗም አልነበረም። መድፉን አልፋ ሽቅብ ወደ መኖሪያዋ ሮጠች።
ከቤቷ ደርሳ ከተቦካ ቀናት ያስቆጠረውን የቡሆ ዕቃ ከፈተች። ጊዜ አላጠፋችም። ሊጡን እንደነገሩ አብላልታ እንጀራ ለመጋገር እሳቱን አይዛ በጉጉት ጠበቀች። የምጣዱ መስማት በእጥፍ ረዘመባት። አሁንም የተራቡ ልጆቿን እያሰበች ነው። ለቅሶና መከፋታቸው ውል እያላት ትጨነቃለች።
ጥቂት ቆይታ ያዘጋጀችውን ሊጥ በምጣዱ አፈሰሰች። አንድ እንጀራ አውጥታም ሁለተኛውን ልትጋግር ምጣዱን ማሰስ ጀመረች። ምኞቷ እንዳሰበችው አልተሳካም። የጣራውን ጭስ በርቀት የተመለከቱ ወታደሮች ተሯሩጠው አስቆሟት። ድርጊቷ ለጠላት ምልክት መስጠት መሆኑን ያልገመተችው እናት ከልቧ ተሳቀቀች።
እናቲቱ እንደምንም ያወጣቻትን እንጀራ በጉያዋ ሸሽጋ ወደ ምሽጉ ሮጠች። ልጆቿ በእጇ ላይ ያለችውን አንዲት እንጀራ ባዩ ጊዜ በደስታ ዘለሉ። ልክ እንደ እናት ወፍ እንጀራዋን ቆራርሳ በአፍ ባፋቸው ለማጉረስ አዘጋጀች። አጋጣሚ ሆኖ ከእሷ ድርጊት ጋር የመድፎቹ ተኩስ ሲደበላለቅ አንድ ሆነ። ልጆቹ በድንጋጤ ራዱ።
በጭንቅ የደረሰችው አንዲት እንጀራም በአካባቢው ንቅናቄ ከአፈር ተለውሳ ወደቀች። ጠንካራዋ እናት ግን ተስፋ አልቆረጠችም። ከመሬት የወደቀችውን እንጀራ ካፈሩ አራግፋ ለልጆቿ አቃመሰች። «አይዟችሁ! አለሁላችሁ» ስትልም ዕንባቸውን አበሰች።
መምህር ልዑል ሰገድ ሰይፉ ዛሬ ላይ ሆኖ የዚያን ጊዜውን ክፉ አጋጣሚ ሲያስታውስ የእናቱን ውለታ ያስቀድማል። ልዑል በወቅቱ በምሽጉ ከተደበቁ ወንድማማች ሕፃናት መሀል አንደኛው ነበር። ለዛሬው ማንነቱና በሕይወት መቆሙ ዋስትና ለሆኑት ወላጅ እናቱ የተለየ አክብሮት አለው። በእሳቸው ማንነት ውስጥ የበርካታ እናቶችን ጥንካሬ ያይበታል። በእንዲህ ዓይነቶቹ እናቶች ትከሻ ላይም የብዙዎች ሕይወት መሠረት እንደተገነባ ዕምነቱ ነው።
ልዑል ደጋግሞ እንደሚለው እናቶች ምንጊዜም ለልጆቻቸው መስዋዕት ለመሆን እንደተዘጋጁ ነው። ለዚህ እውነታ ደግሞ በጦርነት መሀል ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡትን እናቱን ዋቢ ያደርጋል። በእሱ ዕምነት የእሱን መሰል እናቶች ታሪክ ታላቅ ገድል ነው። ተነግሮ አያልቅም።
እንዲህ ዓይነቶቹን ታላላቅ እናቶች ለመዘከር ደግሞ የአንድ ቀን መታሰቢያ ብቻ በቂ አይሆንም። «እናት በየሰከንዱና በየደቂቃው፣ ሰዓታትና ቀናት ሳይወሰንላት ልትከበርና ልትወደስ ይገባታል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ቢያንስ እንጂ አይበዛባትም» ይላል ልዑል። ዛሬ የልዑል ሰገድ እናት የሰባ ስድስት ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። አሁንም ከነጥንካሬያቸው ተጉዘው ለእሱ ልጆች መመኪያ የመሆናቸው እውነት ደግሞ ከልብ ያኮራዋል።
እናት የመሆንን ጸጋ በቅርብ ቀን ያገኘችው ወይዘሮ ሕይወት መኮንን ደግሞ እናትነትን በተለየ ትገልጸዋለች። እንደወይዘሮዋ ዕምነት የእናትነት ስሜት እናት ከሆኑ በኋላ ትርጉሙ ይለያል። የእርግዝናና የምጡን ስቃይ ሲያልፉበትም መለስ ብሎ የእናትን ድካም ማሰቡ ግድ ይሆናል።
ሕይወት እንደምትለው ልጅ ማለት ሁሌም ቢሆን ለእናቱ ልጅ ነው። እናት ደግሞ መቼውንም ይህን ስሜት ልትተወው የሚቻላት አይሆንም። ይህ እውነት ታዲያ የእናትን ውለታ በየአፍታው እያሰቡ እንዲያከብሯትና እንዲያወድሷት ያስገድዳል። ለእናትነት አንዲት ቀንን ብቻ ወስኖ «እንዲህ ናት…» ማለቱም በቂ የሚባል አይሆንም።
አቶ አድነው አበራ በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው። እስከዛሬ በሀገራችን የእናቶች ቀን የሚከበረው የማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስታኮ እንደነበር ይናገራሉ። ይህ የተለመደ አካሄድ ግን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አይደለም።
አቶ አድነው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ለእናቶች ቀን መከበር የተለየ ትኩረት በመሰጠቱ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ቀኑ የሚከበረው በተለየ ትኩረት ይሆናል። ለዚህ ቀን መሪ ቃል ተመርጦለትና ጊዜ ተወስኖለት የማክበር ዕቅድ መያዙን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የትኩረት አቅጣጫውም የሴቶችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ተደጋግሞ እንደሚነገረው ሴቶች ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሃምሳ በመቶውን ድርሻ ይሸፍናሉ። ካለባቸው ተደራራቢ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አንጻር ግን የተሰጣቸው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለይም እናቶች ያሉትን ጫናዎች ተቋቁመው ልጆቻቸውን ለማሳደግና ቤታቸውን ለማቆም የሚያደርጉት ትግል ከሚባለው በላይ ታላቅ ዋጋ ያስከፍላቸዋል።
የእናቶችን ቀን በተለየ ትኩረት አስቦ የሚገባውን ሁሉ ክብር ለመስጠት መንግሥትና ኅብረተሰቡ ድርሻውን ሊጋሩት ይገባል። እናት፣ የማንነት ውልና የትውልድ ሐረግ መነሻ፣ የቤተሰብ ብሎም የሀገር መሠረት ናትና። «ክብር ለእናቶቻችን» ይሁን።
ዓለም አቀፍ የእናቶች ቀን እ.አ.አ የግንቦት ወር በገባ ባለው ሁለተኛ እሁድ ይከበራል።እአአ የ2019 ዓለም አቀፍ የእናቶች ቀን ነገ ይከበራል።
የእናቶች ቀን መከበር የጀመረው እአአ 1908 ሲሆን፣ አና ጃራቪስ የተባለች አሜሪካዊት ምዕራብ ቬርጅንያ፣ በግራፍቶን በሚገኘው የቅዱስ አንድሪው ቤተክርስቲያን የሰላም አክቲቪስት፣ የማህበረሰብ አደራጅ እንዲሁም በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከሁለቱም ወገኖች የቆሰሉ ወታደሮችን በማከም የምትታወቀውን እናቷ አና ሪቪስ ጃራቪስ መታሰቢያ በአዘጋጀችው ፕሮግራም ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ