አዲስ አበባ፡- የህትመት ጥራት ችግር እና የህትመት ውጤቶቹ መዘግየት በተነባቢነትና በገቢ አሰባሰብ ላይ ችግር እንደፈጠረበትና በስርጭት ማስፋፋቱም ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትናንት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ከማተሚያ ቤት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው የህትመት ውጤቶቹ መዘግየት ስርጭት የማስፋት ፍላጎት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል፣ የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም መቸገሩንና በገቢ አሰባሰብ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩንም በውስንነት አንስተዋል።
ተቋሙ የተጣለበትን የዲፕሎማሲ፣ የአገር ግንባታ፣ የለውጥ እንቅስቃሴ፣ የገጽታ ግንባታ፣ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ለመስራት የህትመት ጥራት ችግር እና በህትመት ውጤቶቹ መዘግየት እንደተቸገረ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የጠቆሙት።
የይዘት ሥራዎችን በማጠናከር ለሌሎች ብዙኃን መገናኛ ጭምር የመረጃ ምንጭ መሆን መቻሉን፣ ሪፎርም በማካሄድ የቅዳሜ ልዩ ዕትም ተነባቢ ጋዜጣ በማሳተም በጥንካሬ መቀጠሉንና ይህንንም በሌሎቹ ህትመቶች ላይ ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ጌትነት አንስተዋል።
ይህ የለውጥ አሠራር በኢትዮጵያን ሄራልድ ከነገው እሁድ ጀምሮ በመተግበር በይዘቱ ለየት ያለና ጥራቱን የጠበቀ ህትመት ለሕዝብ እንደሚደርስም ጠቅሰዋል።ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል በመጣውና ፈታኝ በሆነው ዱቤ መሰብሰብም የተሳካ ሥራ ተሰርቷል ሲሉም ተቋሙ በጥንካሬ የፈጸማቸውን ተግባራት አብራርተዋል።
የሰው ኃይል አደረጃጀቱ በሁለት ዓይነት አመራር ስር መሆኑ፣ የዕውቀትና የክህሎት ውስንነትና የምርመራ ዘገባ ሥራ በሚፈለገው ደረጃ አለመሰራቱንም በውስንነት አንስተዋል።ይሁንና 36 ከፊል ምርመራ ቀመስ ዘገባዎች ተሰርተዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ «ከዚህም በላይ መሰራት እንዳለበት እናምናለን፣ በቀጣይም ራሱን ችሎ የሚደራጅ የምርመራ ዘገባ ቡድን ለማቋቋም ታስቧል» ሲሉም ጠቁመዋል።
አሁን በተቋሙ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት የድርጅቱ ማሻሻያ አዋጅ ጸድቆ እንዲተገበር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።ተቋሙ እንደ አንጋፋነቱ እንዳልሆነ፣ በጎረቤት አገራት ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ደረጃ ሲነጻጸርም በጣም ባነሰ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።ይህንን በመገንዘብ ምክር ቤቱ የማሻሻያ አዋጁ ጸድቆ ወደ ተግባር ለመግባት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ በበኩላቸው፤ የህትመት መዘግየትና የህትመት ጥራት ችግርን ለመፍታት ከአታሚው ተቋም ጋር መነጋገር እንደሚገባ አንስተዋል።አታሚው ድርጅት ችግሩን እንዲያስተካክል መነጋገር እና መግባባት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ይህ ሳይሆን ከቀረም ለሚፈጠረው ኪሳራ ማተሚያ ቤቱ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።ድርጅቱ የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም የጀመረውን ተግባር ቋሚ ኮሚቴው የአዋጭነት ጥናቱን ተመልክቶ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
ችግሮችን በአሠራርና በሕግ ማዕቀፍ መፍታት እንደሚገባ ያነሳው ቋሚ ኮሚቴው፤ የተዘጋጁና በረቂቅ ደረጃ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸውን በማንሳት፤ የተዘጋጁ መመሪያዎች በተቋሙ ቦርድ አመራር መጽደቅ የሚችሉ በመሆናቸው ጸድቀው ወደ ሥራ መገባት ይኖርበታል ብሏል።
የድርጅቱ ማሻሻያ አዋጅ በፍጥነት ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅና ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ ይገባል ብሏል።ድርጅቱ የህትመት ውጤቶቹን ተነባቢነት ለማሳደግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በተለያዩ የአቀራረብ መንገዶች ማሳደግ መቻሉና የይዘት ሥራዎቹን ከኦንላይን ሚዲያ ጋር አስተሳስሮ ለመስራት ያደረገውን ጥረት በማድነቅ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አመልክቷል፡፡
የተለያዩ አስተሳሰቦችን ባማከለ መንገድ የሃሳብ ነፃነትና ብዝሃነትን ለማስተናገድ የተሰራውን ሥራም በበጎነት አንስቷል።በአገር ውስጥና በውጭ አገር ቋንቋዎች በዲፕሎማሲ፣ በአገር ግንባታ፣ በለውጥ እንቅስቃሴና በገጽታ ግንባታ የተሰሩትን ሥራዎችም በጥንካሬ ገምግሟል።
ውዝፍ ሂሳቦችን ለመሰብሰብ የተደረገውን ጥረትና የዱቤ ሽያጭ ከባንክ ጋር ለማስተሳሰር የተጀመረው ሂደት እንዲጠናከርም ጠይቋል።ቅሬታዎች መቀነሳቸውን ከሪፖርቱ መገንዘቡን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው፤ ያልተፈቱ ችግሮች ተለይተው እንደየደረጃቸው እየፈቱ የውስጥና የውጭ ተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ ትኩረት እንዲሰጠውም አሳስቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በዘላለም ግዛው