በ‹‹ፒጃማ›› የተሸፈነ ማንነት

ፒጃማ ለብሳ መንገድ ዳር ቆማ አንድ ነገር እየጠበቀች ያለች ትመስላለች። ምን እየጠበቀች እንደሆነ ግን ለጊዜው አይታወቅም። ከሰፈሯ እየወጣች ነው ብሎ ለመገመትም ያስቸግራል። ከታች እስከ ላይ የለበሰችው እንደነገሩ ነው። አንድ ቦታ ደረስ ብላ ለመመለስ ያሰበች ነው የምትመስለው። እግሯ ግን ወደ ቤተክርስቲያን አመራ። ለሷ ከምንም በላይ ምቹ ስፍራ ቤተክርስቲያን ነው። የሥራ ሰዓቷ እንደደረሰ ግን አልዘነጋችም። ሀሳቧም የቤተክርስቲያኑን ደጀ ሰላም ተሳልማና ፀሎት አድርሳ ወደሥራዋ መመለስ ነበር።

በዚህ አጋጣሚ ነበር ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ የተቀየረውን ወይዘሮ ቅድስት ሊበንን ያገኘኋት። ‹‹እንደዚህ ሆነሽ የት ልትሄጂ ነው?›› አልኳት። መልስ ሳትሰጠኝ እንባዋን እንደጎርፍ ማውረድ ጀመረች። ሳግ ተናንቋት ጥያቄዬን መመለስ አቃታት። የውስጧን ለማውጣትና ሀሳቧን ለመግለፅ አልቻለችም። እንባዋ አሁንም አሁንም በጉንጮቿ ላይ እየተንከባለለ ከንፈሯን ያርሰዋል። ትንሰቀሰቃለች። አንድ ነገር ገመትኩ። የማትፈልገው ሕይወት ውስጥ ሳትገባ እንዳልቀረች ገመትኩ።

አዎ! ግምቴ ትክክል ነበር። ወይዘሮ ቅድስት ቤት የዋለውን አካል ጉዳተኛ ባሏን፣ የደረሱ ሴት ልጆቿንና ወንድ ልጇን ለመታደግ ስትል ሴተኛ አዳሪ ሆናለች። ገና ሳይመሽ ‹‹የምሽት ሥራ ስላለብኝ እንዳትጠብቁኝ ተኙ›› ብላ በማታ የመውጣቷም ምስጢርም ይህ ነበር። በእርግጥ ቅድስት ዛሬ ብቻ ሳይሆን የትናንት የልጅነት ሕይወቷም በፈተና የተሞላ ነበር። አንድም ቀን ደስታን አጣጥማ አታውቅም። የደስታ ትርጉሙ ምን እንደሆነም አልተረዳችም። በተለይ እናቷን ስታጣ ሁሉ ነገር ጨልሞባት ነበር።

ወይዘሮ ቅድስት ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ጨረታ አስኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የቤተሰቧ የመጨረሻ ልጅ ብትሆንም እንደ በኩር ልጅ ብዙ ኃላፊነት ተጥሎባት ነው ያደገችው። ከእናቷ ቀጥሎ ትልቁ ኃላፊነት የወደቀውም በእርሷ ላይ ነበር። በዚያ ላይ አባታቸውን ስለማያውቁትና ስለማይረዳቸው ሁሉን የማድረግ ግዴታ ነበረባት። ከዚህ ውስጥ ከባዱ ሥራ በጠዋት ጫካ ሄዶ እንጨት መልቀምና መሸጥ ነበር።

ቤተሰቡ በእርሷ ሙሉ ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ወይዘሮ ቅድስት በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እንጨት ለቅማ መሸጥ አልበቃትም። እናም አራትና አምስት ጊዜ ጫካ እየተመላለሰች እንጨት ለቅማ መሸጥ ግድ ሆነባት። እንዲያም ሆኖ አልቻለችም። ቤተሰቡ ከሚራብ ብለው እናቷም ከጫካ እንጨት ለቅሞ መሸጡን አብረዋት ለአመታት ሠርተዋል።

ወይዘሮ ቅድስት ይህን ያህል መስዋዕትነት ለቤተሰቧ ስትከፍል በብርቱ ተፈትናለች። በሥራ አጋጣሚ በእግሯ ላይ የአካል ጉዳት ደርሶባታል። በዚህ ጉዳቷ ሕይወት ጨልሞባታል። ዓመት ከስድስት ወር የአልጋ ቁራኛ ሆና በህመም ማቃለች። በዚህ መሃል የገዛ ስጋዋ የሆነው ወንድሟ አስቀይሟታል። የወንድሟ ድርጊት ትልቅ ጠባሳም ጥሎባት አልፏል። ይህ ጉዳቷ ዛሬም ድረስ ተከትሏት ከአዕምሮዋ ሊጠፋ አልቻለም። ለትናንት ችግር ያልተንበረከከችው ወይዘሮ ቅድስት ዛሬ ሠርቶ መግባት ዳገት ሆኖባታል።

ወይዘሮ ቅድስት የአካል ጉዳት ያጋጠማት በድንገት ነበር። አንድ ቀን እንደተለመደው እንጨት ለመልቀም ወደ ጫካ ሄዳ ተሸክማ ስትመለስ አዳለጣትና ወደቀች። አንድ እግሯ ወደ ፊት አንድ እግሯ ወደ ኋላ ቀረ። በጊዜው ዋና ሃሳቧ እንጨቱን ቶሎ ሸጣ ቤተሰቧን መመገብ ነበር። ህመሟን ችላ እንጨቱን ተሸክማ ገበያ ደርሰች። እንደ ሁልጊዜው ግን ዳግመኛ ወደ ጫካ ሄዳ እንጨት መልቀም አልቻለችም። በእግሯ ላይ የደረሰው ጉዳት እንደበፊቱ በቀላሉ ሊያራምዳት አልቻለም። ስለዚህ ምርጫዋ ቤት መዋል ሆነ። በወቅቱ እናቷ ስለነበሩ ግን ፈተና አይተው አስታመሟት። እግሯ ይቆረጥ ቢባልም ለክፉ ሳይሰጧት ተንከባከቧት። ዛሬ ትንሽም ወጥታ መግባት የቻለችው በእናቷ ምክንያት ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ወይዘሮ ቅድስት ከአካል ጉዳቷ በባሰ የተሰቃየችው እናቷን ባጣች ጊዜ ነበር። ከጎኗ ሆነው አይዞሽ ሲሏት የነበሩትም እሳቸው ናቸው። ከእናቷ ሞት በኋላ የነበረው ሕይወቷም በእጅጉ የከበደ ነበር። ዛሬም ቢሆን ማማረሯ በደረሰባት የአካል ጉዳት ብቻ ሳይሆን በእናቷም ሞት ጭምር ነው።

የእናቷን ሞት ባስታወሰች ቁጥር ‹‹ፈጣሪ ቢወደኝ ምን አለ እናቴን ዛሬ ድረስ ቢያቆይልኝ›› ትላለች። ምክንያቱም እናቷ አንዴ በሰው ቤት እንጀራ ጋግረው ሌላ ጊዜ ደግሞ አሻሮ ቆልተው ነው ያሳደጓት። እናቷ ለእርሷ የልጆቿ እናትና አለኝታ፤ የባለቤቷ መከታ ነበሩ። ዛሬም ቢሆን መንገድ ወጥታ ያልቀረችው በእርሳቸው ምክንያት ነው። እርሳቸው በሕይወት ሳሉ አንድ ክፍል ቤት በማውረሳቸው ነው ዛሬ ቤተሰቧን ሰብስባ መኖር የቻለችው።

ዛሬ እነ ወይዘሮ ቅድስት ቤት እንጀራ ተጋግሮ አይበላም፤ ተገዝቶ እንጂ። ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ሆኗል። ጤፍ ገዝቶ ለማስፈጨትና ጋግሮ ለመብላት የሚያስችል ገቢ የለም። ስለዚህ ከተገኘ ተገዝቶ ይበላል። ካልተገኘ ደግሞ ጦም ይታደራል። ወይዘሮ ቅድስት ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ስታስበው እንባ ይቀድማታል። በቤቷ የሚበላ ጠፍቶ የምግብ ቤት ትርፍራፊ ለምና ነው ራሷንና ቤተሰቧን የምትመግበው። መድኃኒት የምትወስደውም ይህንኑ ትርፍራፊ በልታ ነው።

‹‹በዚህ ችግርና ስቃይ ልጆቼም ሆኑ ራሴ መራብ የለብንም›› ብላ የተነሳችው ቅድስት፤ ከአካል ጉዳቷ በመጠኑ እንዳገገመች በቀጥታ ወደ ሥራ ገባች። ሥራው ለአንድ አካል ጉዳተኛ ሰው የማይታሰብ ቢሆንም አማራጭ ግን አልነበራትም። በወቅቱ በቀላሉ የሚገኘው ሥራ የጉልበት ሥራ ነውና እርሷም ይህንኑ ሥራ ምርጫዋ አድርጋ ጀመረችው። በዚህ ሥራ ቤተሰቧን ለማኖር ብዙ ለፋች። እግሯን እየቆጠቆጣትና እየተንቀጠቀጠች ለዓመታት ሠራችው።

ወይዘሮ ቅድስት የእርሷን እጆች የሚጠብቁ አራት ልጆች አሏት። ባለቤቷም ቢሆን ገንዘብ አጥፊና ጠጪ ስለሆነ ብዙም አያግዛትም። ስለዚህ ሁሉን ችላ የቤቱን ጉድለት መሙላት ግዴታዋ ነበር። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ዓመታትን ገፋች። እንግዲህ ይህንን ስቃዩዋን የተመለከተው የምትኖርበት ወረዳ ‹‹የድሀ ድሀ›› በሚል በሴፍቲኔት ውስጥ ገብታ እንድትሠራ ሲያደርጋት ነው ከጉልበት ሥራው የተላቀቀችው። ሴፍቲኔቱ ብዙ ችግሯን አቃሎላታል። የሴፍቲኔት ሥራው ሲጠናቀቅ የተሰጣትን ገንዘብ ይዛ የጉልት ሥራ ጀመረች።

ህመሟን በቀላሉ የምትቋቋመው በእንደዚህ ዓይነት ሥራ እንደሆነም ታምናለች። ምክንያቱም አረፍ ብላ እንድትሠራ ያግዛታል። እናም ጊዜ ሳትፈጅ ብድር ወስዳ ባላት ላይ ጨምራ መሥራቱን ቀጠለች። በጉልት ሥራው ውጤታማ ነበረች። ይህ ጊዜ በመጠኑም ቢሆን ደስተኛ የነበረችበት ነው። ጥሩ በመሥራቷ ቤተሰቦቿን በትንሹም ቢሆን ደስተኛ አድርጋ ኖራበታለች። ልጆቿም ቢሆኑ እንደልባቸው ሳይሸማቀቁ መማር ችለዋል። በቤት ውስጥ የሚበላ ነገር ጠፍቶም አያውቅም ነበር።

ሆኖም ይህም የሥራ ጊዜ እንደ ትናንቱ የሚያጨልም ነገር ገጠመው። ባለቤቷ ጥበቃ በነበረበት መሥሪያ ቤት ውስጥ ችግር ተፈጠረ። ንብረት ጠፋና እርሱም ታሰረ። ለዋስ ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ተጠየቀ። እርሷ ደግሞ ይህንን የማድረግ አቅም አልነበራትም። ይሁን እንጂ የልጆቿን አባት በእስር ቤት መተው አልፈለገችም። እናም ምርጫዋን አንድ ነገር ላይ አደረገች። የተበደረችውን ብድር መክፈል አቁማ እርሱን ማስፈታቱ ላይ አተኮረች።

ባለቤቷን አስፈትታ ብድሯን እንደምትከፍል አምና ነበር። ሆኖም በልዩ ጉዳይና አካል ጉዳተኛ በሚል የተሰጣቸው ጉልት በግብረኃይል በመፍረሱ ሃሳቧ በቀላሉ ሊሳካላት አልቻለም። በዚህም እንዳለፈው ጥሩ ገቢ የማግኘት ህልሟ አከተመ። ቤተሰቧን የምትመግብበት ምንም ዓይነት ሥራም አልነበራትም።

ወይዘሮ ቅድስት ከወንዱ ልጇ በስተቀር ሁሉንም እያስተማረች ነው። እርሱም ቢሆን በራሱ ፍላጎት ከሰባተኛ ክፍል አቋረጠ እንጂ ያላደረገችለት ጥረት አልነበረም። በእርግጥ እርሱም ትምህርቱን ለማቋረጥ ምክንያት ነበረው። የእናቱ ልፋት ከአቅሙ በላይ ቢሆንበት እናቴን ላግዝ ብሎ የትምህርት ፍላጎቱን ገቷል። አሁን የቀን ሥራ እየሠራ እንደ አንድ አባወራ ቤተሰቡን ያግዛል።

‹‹ለእግሩ እንኳን ጫማ የለውም። ሁል ጊዜ ለቤተሰቡ ያስባል። በጀሪካን ውሃ በማመላለስና ሌሎች የሸክም ሥራዎችን በመሥራት ነገሮችን አቅልሎልኛል። እንደውም እርሱ ባይኖር ኖሮ ይህን ዓመት በምንም አላልፈውም ነበር›› ስትል ልጇ ምን ያህል ባለውለታዋ እንደሆነ ትገልፀዋለች። ‹‹የቀን ጨለማ ሆኖብኝ ብርሃንን የማየው በእርሱ ነው›› ትላለች።

ለወይዘሮ ቅድስት ሴቷ ልጇም ባለውለታ ነች። ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ መሸጋገሪያ ሆናታለች። እርሷ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ብትሆንም ከትምህርት መልስ ቡና ጠጡ እየሠራች ታግዛታለች። ትሠራለች፤ ሰው ቤት ልብስም ታጥባለች። ይህም ሆኖ አመሉ ያልለቀቀው ባለቤቷ ቤት ያለውን ገንዘብ ይዞ በመውጣት ይጠጣበታል። በዚህም ለቤት የሚሆነውን ወጪ በቀላሉ መሸፈን አልቻለም። ስለዚህ ልጆቿ በቤት ውስጥ ያለውን ችግር አይተው እንዳይሳቀቁ ስትል የማይሆን ሥራ ለመሥራት ተገደደች።

ወይዘሮ ቅድስት ቤተሰቧን ለማቆየት ስትል ያልሠራችው ሥራ አልነበረም። ዛሬ ግን ያ ሁሉ የቀረ ይመስላል። በዚያ ሥራ የምትቀጥልበት ሁኔታ ላይ አይደለችም። አካል ጉዳቷና የኤችአይቪ ኤድስ ተጠቂ መሆኗ ደግሞ ነገሮችን በቀላሉ እንዳታከናውን አድርጓታል። የጉልበት ሥራ እንኳን ለመሞከር አትችልም። እንደ ትናንቱ እንጨት ለቅሜ ልሽጥ ብትልም እንደ ልብ እንጨት አይገኝም። በጉልት ንግዱም ልዝለቅበት ብትል ምንም ምቹ ሁኔታ የለም። ስለዚህ የመጨረሻዋ ምርጫ ያደረገችው ገላዋን መሸጥ ነው።

አሁን ወይዘሮ ቅድስት ምሽት አማራጭ የሆነበትን ሴተኛ አዳሪነት «ሕይወቴ» ብላ ጀምራዋለች። ከዚህ ችግሯ ለመውጣት ያላደረገችው ጥረት አልነበረም። አንዱ ሙከራዋም ወረዳው ችግሯን ይረዳላት ዘንድ በየጊዜው እየሄደች መለመኗ ነው። የተሰጣት ምላሽ ግን የማይጠበቅና የማይታመን ነበር። የወረዳው ኃላፊ ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ከመግባቷ በፊት «አግዙኝ» ስትለው ‹‹ካዋጣሽ ቀጥይበት›› ነበር ያላት። ይህ ምላሽ ተስፋ አስቆርጧት ወደዚህ ሕይወት ገብታለች።

ወይዘሮ ቅደስት ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሥራዋ የምትሄደው ዘወትር የሌሊት ልብስ (ፒጃማ) ለብሳ ነው። ይህንን የምታደርገው ደግሞ ሥራዋን ልጆቿ እንዳያውቁባት ነው። ከቤት ስትወጣ ለልጆቿ ዘወትር አንድ ነገር ትላቸዋለች። ‹‹የምሽት ሥራ አለብኝ አትጠብቁኝ ተኙ›› ከዚያ ልብሷን ወዳስቀመጠችበት ሄዳ ትቀይራለች። ለሴተኛ አዳሪነት የሚመች አለባበስም ትለብሳለች። ብርድ እየቆጋት ወንዶችን አናግራ፤ ገንዘብ ሠርታ ምሽቱን አሳልፋ በጠዋት ወደ ቤቷ ትመለሳለች።

ለቅድስት አሁን ዋነኛ ተስፋዋና ከዚህ ችግር መውጫዋ አንድ ነገር ብቻ ነው። ይህም የአካል ጉዳተኛና የኤችአይቪ ኤድስ ተጠቂ በመሆኗ ችግሯ ከግምት ውስጥ ገብቶ የምትሠራበት ቦታ እንዲሰጣት ትፈልጋለች። ለዚህ ደግሞ የምትኖርበት ወረዳ የሚመለከተው የሥራ ክፍል ኃላፊነት እንዳለበት ትጠቁማለች።

ኤች አይ ቪ ኤድ በደሟ ውስጥ እንዳለ ያወቀችው በአጋጣሚ ነበር። የእህቷ ልጅ የምትረዳበት ድርጅት ሄዳ ተመርመሩ ሲባል ተመረመረች። በወቅቱ ነፍሰ ጡር ነበረች። በወቅቱ የምርመራው ውጤት ሲነገራት ምንም አላለችም። ለሌላው አስተምራለሁ የሚል ምላሽ ነበር የሰጠችው። ነገር ግን አይደለም ማስተማር እያደር ህመሙ ፀንቶ እንደልብ እንዳትንቀሳቀስ አገዳት። ፈተናውንም መጋፈጥ አቃታት።

የበሽታው ተጠቂ መሆኗ ሌላም ነገር እንድታይ አድርጓታል። ወዳጅና ጠላቷን ለይታበታለች። በዚህ የችግሯ ጊዜ ሁለት ጓደኞቿ ከጎኗ አልራቁም። አንደኛዋ ባላት አቅም ሁሉ ረድታታለች። ሌላኛዋ ደግሞ ሁለት ልጆቿ በሜሪጆይ እንዲታገዙ ደግፋታለች። የዋሉላትን ውለታም ‹‹በቤተሰባቸው ያግኙት›› ስትል ትመርቃለች።

‹‹አካል ጉዳተኛ ብሆንም ሠርቶ የመለወጥ ህልም አለኝ። አዕምሮና ተስፋ ያለው ሰው ደግሞ ያሰበበት ከመድረስ የሚያግደው ነገር የለም። ስለዚህ የምሠራበት ቦታ ከተሰጠኝ ለሌሎች ጭምር መምህር እንደምሆን እምነት አለኝ።›› ትላለች ወይዘሮ ቅድስት። ከዚህ አሰቃቂ ሕይወት እንድትወጣ የምትኖርበትን የክፍለ ከተማና የወረዳውን መልካም ፈቃድ ትጠይቃለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *