የተፈጥሮ ቱሪዝም የስነ ምህዳር ጥበቃ ፋይዳ

ኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክ፣ የስነ ህንፃ ጥበብና የስነ ፈለክ እውቀትን ጨምሮ በርካታ ሃብቶችን የያዘች ቀደምት ስልጣኔ ከነበራቸው ጥቂት አገራት ተርታ የምትመደብ ነች። እነዚህ ሃብቶች ኢትዮጵያዊነትን ከመግለፃቸውም በላይ በአግባቡ ከተያዙና ለቀሪው ዓለም ከተዋወቁ እምቅ የቱሪዝም ሃብት ናቸው። የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ከማነቃቃት ባሻገር በዓለም ዙሪያ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን ግንዛቤ በማሻሻል መልካም ስምና ገፅታን የመገንባት አቅም ይፈጥራሉ።

ከላይ ካነሳናቸው ሃብቶች ባሻገር ኢትዮጵያ በውብ ተፈጥሮና መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ የታደለች አገር ነች። በቀሪው ዓለም የማይገኙ አእዋፋት፣ የዱር እንስሳት፣ አገር በቀል እፅዋት፣ ወንዞች እና ሌሎች እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች መገኛ ነች። ይሁን እንጂ ይህንን ሳይከፈልበትና ሳይለፋበት የተገኘ ስጦታ ወደ እድል መቀየርና አገርና ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ መገንዘብ አያዳግትም።

በቱሪዝም እሴትነት በጉልህ ከሚጠቀሱ ዘርፎች መካከል “የተፈጥሮ ቱሪዝም” በቀዳሚነት ይነሳል። ይህ ዘርፍ ጎብኚዎች በልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ ተዘዋውረው የተፈጥሮን ፀጋዎችን እንዲመለከቱ፣ መንፈሳቸውን እንዲያድሱ፣ ከአዳዲስ ስነ ምህዳር ጋር እንዲላመዱ፣ አእዋፋትን፣ የዱር እንስሳትን፣ መልከዓ ምድርን፣ አገር በቀል እፅዋቶችን እንዲመለከቱና እውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ የሚረዳ ነው። ከሌላው የዓለም ክፍል የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለመመልከት የሚመጣው ቱሪስት ከሚያገኘው በረከት ባሻገርም የሃብቱ ባለቤት የሆነው አገርና ዜጎች ከጎብኚዎች በከፍተኛ ሁኔታ በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ ይሆናሉ። በዚህ ውስጥ የቱሪዝም ዘርፍ “ሰጥቶ በመቀበል” መርህ እያደገና እየጎለበተ ይመጣል።

የተፈጥሮ ሃብት በሰው ልጅ ጥረት የሚገኝ አይደለም። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ምድር የቸረችውን ፀጋ ተንከባክቦ፣ አሳድጎና ይበልጥ አስውቦ የማቆየት አቅም አለው። ከዚህ ባሻገር በተፈጥሮ ቱሪዝም ሃብቶቹን ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በማጋራት እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል። ከሁሉም በላይ ግን ከተፈጥሮ ሃብትና ቱሪዝም የመጠቀምን ያህል ሃብቱን የመንከባከብ፣ ስነ ምህዳሩን የመጠበቅ እና የማቆየት ኃላፊነትም በእኩል ደረጃ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም እነዚህን ሀብቶች በተፈጥሮ ከመቸሯ ውጪ ሃብቶቹን ጠብቆ በማቆየት ረገድ ክፍተቶች እንደሚታዩባት ይገለፃል። በተለይ ስነ ምህዳሩ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚረዱ እፅዋቶችን እንዳይመነጠሩ ለሰው ሰራሽና የሰደድ እሳት አደጋ እንዳይጋለጡ፣ በውስጣቸው የሚኖሩ አእዋፋት፣ የዱር እንስሳት፣ ፓርኮች ይዞታቸውን ሳይለቁ እንዲቆዩ ለማስቻል የሚደረገው ጥረት አመርቂ እንዳልሆነ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። ይህ እውነት ዓለማችን ከገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሲደመር ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ ያደርገዋል። ሁኔታው በጥቅሉ የተፈጥሮ ቱሪዝምን በማዳከም የአገር ምጣኔ ሃብትን የማድቀቅና ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም የሚያስቀርም ነው።

ኢትዮጵያ በዓለማችን በተፈጥሮ ሃብት ከታደሉ አገራት በቀዳሚነት ልትጠቀስ የምትችል አገር ስለመሆኗ በርካታ ወገኖች ይመሰክራሉ። በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ የብዙሃንን ቀልብ ሊስብ የሚችል መልከዓ ምድር የታደለች እንደሆነች ዓለምም ይመሰክራል።

ይሁን እንጂ ሃብቶቹ በልዩ ልዩ አጋጣሚ ለጉዳት ሲጋለጡ ይስተዋላል። በፓርኮች አካባቢ ህገወጥ ሰፈራ፣ የደን ጭፍጨፋና መሰል ሃብቱን የሚያወድሙ ድርጊቶች እንደሚከሰቱ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተፈጥሮ የሚከሰት የሰደድ እሳትን እንዲሁም መሰል አደጋን መከላከል የሚያስችል በቂ አቅም መገንባት አለመቻሉም እንዲሁ እንደ ክፍተት ይነሳል። በድርቅ እና በልዩ ልዩ ምክንያት የጠፉ እፅዋትን አገር በቀል የደን ሃብቶችን መልሶ አለማልማትም እንዲሁ ከችግሮቹ መካከል ናቸው።

እነዚህ ተደማምረው ሀገሪቱ “ከተፈጥሮ ቱሪዝም” መጠቀም ያለባትን ያህል እንዳታገኝ እንዳደረጋት መረጃዎቹ ያመለክታሉ። የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ (በተደጋጋሚ በእሳት ቃጠሎ በሚደርስበት ጉዳት)፣ የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ እና ሌሎችም መሰል የመስህብ ስፍራዎች የዚህ ጉዳት ምሳሌ ናቸው። ይሁን እንጂ በተቃራኒው በውብ የተፈጥሮ ሀብት የታደሉ እንደ ጮቄ ተራራ፣ ወንጪና በደቡብ ምእራብ የሚገኙ ውብ የተፈጥሮ ስፍራዎች አሁንም ድረስ የዓለምን ቀልብ እንደሳቡ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ክፉኛ የተመናመነውን የሀገሪቱን የደን ሀብት መልሶ ለመተካት እንዲሁም የተፈጥሮ ስነ ምህዳሩን ለመጠበቅ ላለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይፋ አድርጎ በዛፍ ችግኝ ተከላ ላይ በስፋት ሰርቷል። በዚህም በአራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ የዚህ መርሃግብር የመጀመሪያው ምእራፍ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምእራፍ ተሸጋግሯል። በሁለተኛው መርሀ ግብር የመጀመሪያ ዓመት/ ዘንድሮ/ ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊየን ችግኞች ይተከላሉ፡፡

የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተፈጥሮ ኡደትን ለመጠበቅ፣ ፓርኮች ይዞታቸውን እንዲጠብቁና እንዲለሙ የሚያስችል፣ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ታቅዶ እየተከናወነ የሚገኝ ንቅናቄ ነው። ይህ ተግባር በአገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስፍራዎች ጋር (እንደ ገበታ ለአገር፣ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለትውልድና ሌሎች ፕሮጀክቶች) ጋር ሲደመር ኢትዮጵያን በጊዜ ሂደት የተፈጥሮ ቱሪዝም ምርጥ መዳረሻ እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም። ለዚህም ነው የቱሪዝም ሚኒስቴር የመርሃ ግብሩ ቀዳሚ ተሳታፊ መሆኑን በልዩ ልዩ አጋጣሚ እየገለፀ የሚገኘው።

‹‹ዛሬን ነገ እንትከል›› በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ቀን ከ500 ሚሊየን ችግኝ በላይ በተተከለበት ወቅት የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በጋራ በመሆን ችግኝ ተክለዋል። በክረምቱም 162 ሺ ችግኞች የመትከል እቅድ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ “ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የአረንጓዴ መርሃግብርን አስጀምራ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው” ያሉት የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ በዚህም ዓመት “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ እንዲሁም ለትውልድ መልካም የሆነ ነገር ለማውረስ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ቱሪዝም ሚኒስቴር በዚህ ንቅናቄ 162 ሺህ ችግኞችን መትከል አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጸው፣ በቀጣይም ቅርሶች ባሉባቸውና በፓርኮች አካባቢዎች የሚቀጥል እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ ንቅናቄ ሀገርን ከመታደግ ባሻገር ለቱሪዝም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ያሉት አምባሳደር ናሲሴ፣ የተፈጥሮን ስነ ምህዳሩን መጠበቅ የሚሰደዱ የዱር እንስሳዎች ወደመኖሪያቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግና ይህም ለኢኮ ቱሪዝም ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው እንደሚሉት፣ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ “ነገን ዛሬ እንትከል” መርሃ ግብር ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቅርስ ባለአደራ ማህበር ባዘጋጀው ቦታ ላይ ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እና ሌሎች የቱሪዝም ዘርፉ ደጋፊ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ አካሂዷል። በዚህ ልክ በሁሉም ክልል የሚገኙ የቱሪዝም ዘርፉ ተሳታፊዎች ለአካባቢ ጥበቃ ላይ ትልቅ ድርሻ ባለው በዚህ የችግኝ ተከላ ላይ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።

“በአሁኑ ጊዜ እንዲለሙና በደን ሽፋን ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈለገው የአገር በቀል ዛፎች ችግኞች ናቸው” የሚሉት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፤ አገር በቀል ዛፎች ከስነ ምህዳሩ ጋር የተስማሙ መሆናቸውን ይናገራሉ። የችግኝ ተከላው የስነ ህይወት ስብጥሩ እንዲሰፋ እንደሚያስችል፣ የዱር እንስሳት እንዲጠለሉበት እድል እንደሚሰጥም ገልፀዋል። በመሆኑም በሁሉም ፓርኮች፣ በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንዲሁም የስነ ህይወት ልማት የሚያስፈልጋቸውና ተፈጥሯዊ ችግኝ በሚፈልጉ ስፍራዎች በሙሉ በዚህ የክረምት መርሀ ግብር ሽፋን ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

“ከምናገኘው ንፁህ ውሀ፣ ከምንተነፍሰው አየር ባለፈ የተፈጥሮ ስብጥር መኖሩ ለጉብኝትና ለመንፈስ እርካታ ወሳኝ ነው” የሚሉት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ፀጋዎች በተጨማሪ ልማትና እንክብካቤ በማድረግ ተጨማሪ እሴት እንዲሆን መስራት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ። ለመንፈስና ለአይን ማራኪ አካባቢን መፍጠር መቻል ኢኮ ቱሪዝምን ለማስፋፋት እድል የሚፈጥር አጋጣሚ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጮቄ ኢኮ ቱሪዝም፣ በወንጪ ደንዲ፣ በአዱላላ ኢኮ ቱሪዝም እውቅና አግኝታለች። ዘንድሮም በሶስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ /በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች/ በተፈጥሮ ሃብትና መስህብነታቸው ተመራጭ የሆኑ መዳረሻዎች እውቅና እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንና ጥናቶች መጠናቀቃቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ ስፍራዎች እውቅና እያገኙ ሲሄዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮና በመልክዓ ምድር የሚሳቡ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መዳረሻ የማድረግ ፍላጎታቸው እንደሚጨምር ያስረዳሉ። ከዚህ መነሻ የተፈጥሮ ኡደቱንና ስብጥሩን መጠበቅ፣ ደኖችና አገር በቀል እፅዋትን ማስፋፋት፣ ለዱር እንስሳት፣ አእዋፋት እና ለመሰል ስነ ህይወት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል። የቱሪዝም ሚኒስቴርም ይህንን መነሻ በማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በቀዳሚነት እየተሳተፈ እንደሆነ አስታውቀዋል።

እንደ መውጫ

ኢኮ ቱሪዝም (የተፈጥሮ ቱሪዝም) የተፈጥሮ መስህቦችን ወይም የተፈጥሮ ቦታዎችን ከመጎብኘት የበለጠ አንድምታ ያለው ነው። ይህ ሲባል የመስህብ ስፍራውን ኃላፊነት በተሞላበት እና በዘላቂነት መጠቀምን የሚያካትት ነው። ቃሉ እራሱ የሚያመለክተው በአካባቢ ጥበቃ ላይ በማተኮር ወደ ተፈጥሯዊ አካባቢዎች መጓዝን ነው። ግቡም ቱሪስቶች ተፈጥሮን እንዲመረምሩ እድል በመስጠት እንዲሁም ስለ አካባቢ ጥበቃና ጥረቶች ማስተማር ነው። ኢኮ ቱሪዝም እንደ ማዳጋስካር፣ ኢኳዶር፣ ኬንያ እና ኮስታሪካ ያሉ መዳረሻዎችን በእጅጉ ተጠቃሚ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዓለም ኢኮ ቱሪዝም ገበያ እ.ኤ.አ በ2019፣ 92 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንዳስገኘና በ2027 ደግሞ ወደ 103 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ ግዙፍ ኢኮኖሚ በአግባቡ ተጠቃሚ ለመሆን በተለይ የስነ ምህዳር ጥበቃው ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ያነሳሉ። የብዝሀ ህይወትን እና ተፈጥሮን ለማሻሻል እና ለመጠበቅ ዘላቂ መፍትሄዎችን መስጠት እንዳለበትም ያስገነዝባሉ። አረንጓዴ አሻራን የመሰሉ መርሀ ግብሮች በዓለማችን ላይ መስፋፋት እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ። ይህ ተግባር የስነ ምህዳር ዋነኛ አካል እንደሆነ ነው የሚያስገነዝቡት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት በተለምዶ በተፈጥሮ ላይ የተመሰረተ ልምድ በሚፈልጉ ቱሪስቶች ከሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ገቢ የሚተገበር ቢሆንም፣ በዘላቂነት የቱሪዝም ድርጅቶች፣ ከምርምር ወይም ቀጥተኛ የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች ጋር መቀናጀት እንደሚኖርበት የዘርፉ ምሁራኑ ምክራቸውን ይሰጣሉ። የኢትዮጵያ መንግስትም ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ስነ ምህዳሩን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ይፋ እያደረገ እየተገበረ ይገኛል። በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥም በርካታ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል፣ በመንከባከብና በማፅደቅ የአየር ንብረትን ለውጥ ከማሻሻል ባለፈ የኢኮ ቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያሳድግ ተስፋ ተጥሎበታል።

ዳግም ከበደ

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *