. ድርጅቱ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል፤
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር በሚታተሙ የህትመው ውጤቶች አማካኝነት የሀሳብ ብዙነትን ለማስተናገድ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑንና የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት ሚዲያ ሆኖ እንዲቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኣሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ የተቋሙን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተቋሙ በይዘት ዘርፍ ተጠቃሽ የሆኑ ለውጦችን ማስመዝገቡ፣ የሀሳብ ብዙነት የሚደመጥበት ሚዲያ መሆን መጀመሩ እንዲሁም የተቋሙ የተከማቸ የዱቤ ገቢ በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉ በቋሚ ኮሚቴው ተመስግኗል።
የእለቱን ስብሰባ የመሩት የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ እንደተናገሩት፤ የተቋሙ የህትመት ውጤቶች የሁሉም ድምጽ የሚሰማባቸው መሆን አለባቸው፤ ከዚህ አንጻር ባለፉት ዘጠኝ ወራት አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል። ይህንን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለ ሆኖ፤ የህትመት ውጤቶቹን ስርጭት ማሳደግና ተነባቢነትን መጨመር ያስፈልጋል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ጥያቄዎችን የሰነዘሩ ሲሆን፤ በዋናነትም “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” የሚለውን አመለካከት በተቋሙ ውስጣዊና ውጫዊ አሰራር ከማስረጽ አንጻር ምን ተሰራ፤ አነጋጋሪ ስራዎችን በቋሚነት ከመስራት ረገድ በታቀደው ልክ ለምን አልተሰራም፤ ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣትና ምቹ የስራ ቦታን ለመፍጠር ምን ተከናወነ፤ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ለተነሱት ጭያቄዎች ማብራሪያ የሰጡትና ሪፖርቱን ያቀረቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደተናገሩት፤ “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” የሚለውን አመለካከት በተቋሙም ከተቋሙም ውጭ በአግባቡ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል። ቃሉ የድርጅቱ የህትመት ውጤቶች መሪ ቃል ሆኖ አሁንም ድረስ መዝለቁን፣ በተቋሙ ውስጥ ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ ሰራተኞች ለዘመን መለወጫ ድጋፍ መደረጉን፤ ከተቋሙ ውጭ ላሉ አቅመ ደካሞች ደግሞ በየበአሉ የዘንድሮውን የትንሳኤ በአል ጨምሮ የበአል መዋያ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።
የተቋሙን የህትመት ስርጭት ለማሳደግ ያለውን የማተሚያ ቤት ችግርና የህትመት ዋጋ መናር ያስረዱት አቶ ጌትነት፤ ይህንን ችግር ለመሻገር ድርጅቱ የተቋሙን ስትራቴጂ እቅድ ከልሶ መልስ ለመስጠት የሞከረ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በ2012 በጀት አመት የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም የአዋጭነት ጥናት አድርጎ መጨረሱን አብራርተዋል። የተቋሙን የአዋጅ ማሻሻያ ከጸድቀ በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ምክርቤቱም ለዚህ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
ከይዘት አንጻር በጋዜጦች ላይ አነጋጋሪ ስራዎች መውጣት መጀመራቸውን ያብራሩት የድርጅቱ የይዘት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሄኖክ ስዩም በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ ከሚፈልገው አንጻር ገና ብዙ መስራት እንዳለብን ብንረዳም ለውሳኔ ሰጪው አካል ግብአት የሚሆኑ በተጨባጭም ለውጥ ያመጡ አነጋገሪ ወይንም ከፊል የምርመራ ዘገባ ባህሪያት ያላቸውን ስራዎች መስራት መቻሉን ተናግረዋል። ሙሉ የምርመራ ዘገባ ለመስራት ያለውን አገራዊና ተቋማዊ የአቅም ውስንነትም አብራርተዋል።
ሴት ሰራተኞችን ወደ አመራርነት ከማምጣት እና እንዲሁም ምቹ የስራ ቦታ ከመፍጠር አንጻር የተሰራውን ስራ ያብራሩት የድርጅቱ የገበያ ልማት፣ አቅም ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው፤ በተቋም ደረጃ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት አራት ሴት የማነጅመንት አባላት እንዳሉ ተናግረዋል። የሴቶች ዳይሬክቶሬትንም በውክልና በማሰራት ለሴት ሰራተኞች የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ እንዲያገኙ መደረጉን፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሴት ሰራተኞችም ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን ገቢያቸውን የሚያሳድጉበት ስራ እንደተመቻቸላቸው አስታውቀዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በመጨረሻም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ መልካም ስራዎችን ይበልጥ በማከናወን በውስንነቶች ላይ ደግ አጠንክሮ በመስራት ለበለጠ ውጤት መስራት እንደሚገባ አሳስቧል።
በተለይም የተቋሙን የማሻሻያ አዋጅ በፍጥነት ወደ ምክር ቤቱ እንዲቀርብ የተጠናከረ ስራ ከስራ አመራር ቦርዱ ጋር ማከናወን እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ፎቶ፡- ገባቦ ገብሬ