የሕይወት ፈተናዎች የወለዱት ምግባረ-ሰናይ ተቋም

ሕይወት በውጣ ውረድ የተሞላች ናትና መራራውንና ጣፋጩን ገፅታዋን እንዲሁም መውደቅና መነሳትን ታሳያለች። ታዲያ በዚህ የውጣ ውረድ ጉዞ ውስጥ የሕይወትን ፈተና ታግለው የትናንቱን መራራ ትግል በድል ቋጭተው ጣፋጩን የጉዞ ምዕራፍ ያጣጣሙ ብዙዎች ናቸው።ከእነዚህም መካከል ያለፉበትን አስቸጋሪ የሕይወት ውጣ ውረድ አስታውሰው፣ የሌሎች ሕይወት የተሻለ እንዲሆን የሚያስችሉ መልካም ተግባራትን የሚያከናውኑ ቅን ሰዎችም አሉ።

የ‹‹ላይፍ ሴንተር የበጎ አድራጎት ድርጅት›› መሥራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉ ግርማይ የሚያከናውኑት በጎ ተግባርም የዚህ ዓይነት የሕይወት ገጠመኝ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ሕይወት በውጣ ውረድ የተሞላች ናትና የወይዘሮ ሙሉ ትዳር የገጠመው አደጋ ልጆቻቸውን ያለአባት የማሳደግን ፈተና ይዞባቸው መጣ። ለሦስት ዓመታት ያህል በኬንያ በስደት ከኖሩ በኋላ፣ ወደ አሜሪካ የመሻገር ዕድል አገኙ። እንኳን በስደት፣ በሀገር ላይ በወገንና በቤተሰብ መሐል ሆኖ ልጆችን ያለአባት ማሳደግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። የወይዘሮ ሙሉም ልጆቻቸውን ያለአባት የማሳደግ ትግልና ኃላፊነት ቀላል አልነበረም።

ወይዘሮ ሙሉ ከ12 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታቸው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፤ የተመለሱት ደግሞ እናታቸውን ለማየት ነበር። በወቅቱ በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ የመሰማራት እቅድም አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ መጥተው የተመለከቱት ነገር ያለፉበትን የሕይወት ውጣ ውረድ እንዲያስታውሱና ዛሬ የሚያከናውኑት የበጎ አድራጎት ተግባር በውስጣቸው እንዲጠነሰስ ምክንያት ሆነ፡፡

‹‹ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑና የሚለምኑ ልጆችንና እናቶችን ካየሁ በኋላ እረፍት አልነበረኝም፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፣ እናት ልጆቿን ብቻዋን ስታሳድግ የምትሸከመው ድርብ ኃላፊነት አለ። እንዲያም ሆኖ የአባታቸውን ቦታ መሙላት አይቻልም፡፡›› ሲሉ ይገልጻሉ።

‹‹ልጆቼን ያሳደግኩት ራሴን ጎድቼ ነው። እናቶች ብቻቸውን ሆነው ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በስሜት፣ በኑሮ፣ በጤናም ሆነ በአካል ምን ያህል ጫና እንደሚኖርባቸው እኔ አይቻለሁ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በተለይ በድህነት ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ያለአባት የሚያሳድጉ እናቶችንና ሕፃናትን እንዳስባቸው አድርገውኛል›› በማለት ያብራራሉ፡፡

‹‹ልጆች ያለአባት ሲያድጉ የሚያጋጥማቸውን ስብራት አውቀዋለሁና እነዚህን ሕፃናትና እናቶችን ለመርዳት አንድ ነገር መጀመር አለብኝ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ያን ያሰብኩት ገንዘብ ስለነበረኝና ስለሞላልኝ አልነበረም፤ ምኞቱና ፍላጎቱ ነው የነበረኝ። የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያከናውን ተቋም ለማቋቋም ወሰንኩ። ፈቃድ የማውጣቱን ሂደት እየከወንኩ ጎን ለጎን ሦስት ልጆችን በራሴ መርዳት ጀመርኩ፡፡›› ይላሉ።

‹‹ ፈቃዱን ካገኘሁ በኋላ በአሜሪካ ከሚገኙ በጎ አድራጊዎች ገንዘብ ለማግኘት እንዲቻል በአሜሪካም ተመሳሳይ ፈቃድ አወጣን። ከዚያ በሚገኘው ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሥራ በመደገፍ ሥራው ቀስ በቀስ ቀጠለ። ስለዚህ ‹‹ላይፍ ሴንተር›› እንዲፀነስና እንዲወለድ ያደረገው የእኔው የመከራ ሕይወት ነው ብዬ አምናለሁ። ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ከራሴ ሕይወት የተወለደ ነው። በዚያ ሕይወት ውስጥ ባላልፍ ኖሮ ምናልባት በዚህ ዓይነት ተግባር ላይ ላልሰማራ እችላለሁ ብዬ አስብ ነበር። እግዚአብሔር መከራዬን ተጠቅሞ ‹‹ላይፍ ሴንተር›› እንዲወለድ አደረገ ብዬ አስባለሁ›› በማለት ያስታውሳሉ።

በ2005 ዓ.ም የተመሠረተው ‹‹ላይፍ ሴንተር የበጎ አድራጎት ድርጅት››፣ ወላጃቸውን ባጡ ሕፃናትና ልጆቻቸውን ያለአባት ብቻቸውን በሚያሳድጉ እናቶች ላይ አተኩሮ የሚሠራ ምግባረ ሰናይ ተቋም ሲሆን፤ ለሕፃናት ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ለእናቶች ደግሞ የንግድ ሥራ ሥልጠናና የሥራ መጀመሪያ ገንዘብ (በብድር መልክ) ድጋፍ ያደርጋል። ሕፃናት የሚያገኙት የገንዘብ እርዳታ ለምግብ፣ ለጤና፣ ለትምህርት ቤትና ለሌሎች እንክብካቤዎች ይውላል። ድርጅቱ ከወረዳና ከቀበሌዎች ጋር በመተባበር ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሕፃናትና እናቶችን በመመልመል የገንዘብና የሥልጠና ድጋፍ ይሰጣል። እናቶች ለሦስት ቀናት ያህል ሥልጠና ይወስዳሉ። የንግድ ሥራ እንዴት እንደሚሠራ፣ እንዴት ገንዘብ መቆጠብ፣ ትርፋማ መሆንና ከድህነት በመውጣት ማደግ እንደሚቻል በሥልጠናው ግንዛቤ እንዲያገኙ ይደረጋል።

የሥልጠናው ዓላማ የድህነትን አስተሳሰብ ከአዕምሯቸው በማውጣት የ‹‹ይቻላል››ን መንፈስ ማስረጽ ነው። ከሥልጠናው በኋላ እናቶቹ መሰማራት የሚፈልጉበት የሥራ መስክ ተለይቶ የተቋሙ ባለሙያዎች ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ያሟሉላቸዋል። ድርጅቱ ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በእጅ (Cash) አይሰጥም፤ ይህም ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያስችላል። ግለሰቦቹ ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩም የድርጅቱ ባለሙያዎች ክትትል ያደርጋሉ። ሴቶቹ ለመነሻ ያህል ከድርጅቱ ያገኙት ገንዘብ በ18 ወራት ውስጥ የሚመለስ ሲሆን፣ ሌሎች ሴቶች ደግሞ እንዲጠቀሙበት ይደረጋል። ‹‹እናንተ የመለሳችሁትን ገንዘብ ሌሎች ሴቶች ተበድረው ይጠቀሙበታል›› የሚለው የድርጅቱ ምክር፣ ሴቶቹ በትጋት ሠርተው ገንዘቡን እንዲመልሱ ያበረታታቸዋል።

ወይዘሮ ሙሉ እንደሚገልፁት፣ ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ለሕፃናትና እናቶች ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ የሰብዕና ግንባታ ተግባራትንም ያከናውናል። ‹‹ሕፃናት በስፖንሰርሺፕ የሚያገኙት የገንዘብ እርዳታ ለምግብ፣ ለጤና፣ ለትምህርት ቤትና ለሌሎች እንክብካቤዎች ያግዛቸዋል። ሌሎች የሚያስፈልጓቸው ተጨማሪ ድጋፎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ልጆቹ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚያስጠናቸውና የቤት ሥራ (Home Work) የሚያሠራቸው ሰው የለም፤ አብዛኞቹ ወላጆች በድህነት ውስጥ ያሉና ያልተማሩ በመሆናቸው ልጆቹን አያግዟቸውም ብለን ስለምናምን አስተማሪ ቀጥረን ከትምህርት ቤት በኋላ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲማሩ እናደርጋለን። በትምህርታቸውና በጤናቸው እንዲታገዙ እንዲሁም የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን ይላሉ።

‹‹የባህርይ ለውጥ እንዲያመጡና መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችሉ በየዕድሜ ደረጃቸው የሚሰጡ ብዙ ሥልጠናዎች አሉ። ወደ ጎዳና እንዳይወጡ፣ ጥፋት ላይ እንዳይገኙ፣ ለቤተሰብ እንዳያስቸግሩ እናደርጋለን። እነሱን ለመደገፍ ደግሞ ወላጆቻቸውንም እናሰለጥናለን። በቤተሰብ ሥልጠና (Family Training) መርሃ ግብር አማካኝነት ስለልጆች አስተዳደግ ሥልጠና እንሰጣለን። የቤተሰብ አለመግባባት (Family Conflict) ሲያጋጥም ችግሩን ለመፍታት እገዛ እናደርጋለን። እኛ የምንሠራው ልጆቹ በልተው እንዲያድሩ ብቻ ሳይሆን ጤነኛ አዕምሮ እንዲኖራቸው ጭምር ነው። እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ፣ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚወዱ እና ታዛዦች እንዲሆኑ አድርጎ ለመቅረፅ ጥረት እናደርጋለን።

ገንዘብ መወርወር ብቻ ፋይዳ የለውም። እነዚህንም እንደራሴ ልጆች ለመውደድና ለመንከባከብ ለፈጣሪ ቃል ገብቼ ሥራውን ከልቤ መሥራት እንዳለብኝ በፅኑ አምናለሁ። የእኛ ፍላጎት ልጆቹ በመልካም ሥነ-ምግባር አድገውና ጥሩ ዜጎች ሆነው ነገ ጥሩ መሪዎች እንዲሆኑ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፣ ድርጅቱ ለእናቶች ከሚሰጠው ሥልጠናና የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪም እናቶቹ ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያሳድጉ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳላቸው፣ የንግድ ሥራቸውን እንዴት እንደሚሠሩ… መሰል ሥራዎች በተመለከተ ክትትል እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።

ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት አስተዳደግና እገዛን በተመለከተ ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ቤተሰብ/ማኅበረሰብ ተኮር አመለካከት አለው። ሕፃናት የቤተሰብና የማኅበረሰብ እንክብካቤና ክትትል ስለሚያስፈልጋቸው በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋም ውስጥ ሰብስቦ ከማሳደግ ይልቅ ከቅርብ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር እንዲያድጉና እንዲኖሩ ማድረግ የተሻለ ስልት እንደሆነ ያምናል።

ታዲያ ይህ የ‹‹ላይፍ ሴንተር›› በጎ ተግባር ውጤት እንዳስገኘ ወይዘሮ ሙሉ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ‹‹ላይፍ ሴንተር›› እስካሁን ድረስ 280 ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ሴቶቹ ራሳቸው ጀምረው በግላቸው የሚያንቀሳቅሷቸው 275 የንግድ ሥራዎችም አሉ። ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ከቁጥር መብዛት ይልቅ፣ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ልጆችና እናቶችን በጥራትና መታገዝ በሚገባቸውና በሚያስፈልጋቸው ደረጃ ማገዝ የተሻለ ተግባር እንደሆነ ያምናል።

‹‹በጣም የሚያስገርሙ ለውጦችን እያየን ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፣ በ‹‹ላይፍ ሴንተር›› እገዛ አድገው ዛሬ የራሳቸውን ሥራ የሚሠሩትን ጽዮን እና ቤተልሄም የተባሉ ወጣቶችን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ጽዮን በ‹‹ላይፍ ሴንተር›› አድጋ፣ ተምራና ተመርቃ ዛሬ የራሷ የሆነ የፈሳሽ ሳሙና ብራንድ ባለቤት እስከመሆን የደረሰች ጠንካራ ሴት ናት። ቤተልሄም ደግሞ በልብስ ሥራ ሙያዋ ተደናቂ የሆነች የ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ፍሬ ናት። ሥራዋ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና በሚኒስትሮች ጭምር የተጎበኙላት ጽዮን እና በሥሯ ለሌሎች ወጣቶች ጭምር የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለችው ቤተልሄም፣ የ‹‹ላይፍ ሴንተር›› የበጎ አድራት ተግባራት ውጤታማ እንደሆኑ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

ወይዘሮ ሙሉ ‹‹በእናቶች ባለቤትነት የተያዙ ቢዝነሶችን መመልከት በጣም ያስደስታል፤ ያኮራልም። ወደ ብድር ከገቡ በኋላ ሲጠነክሩ አስተውለናል። በብድር አገልግሎት ቢዝነሳቸውን ያሳደጉ ሴቶች አሉ። እስከ 300ሺ ብር ካፒታል ያላቸው ሴቶች አሉ። ራሳቸውንና ልጆቻቸውን የሚረዱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን ከፍ ያለ ብድር አቅርበንላቸው የመካከለኛ ገቢ ባለቤት እንዲሆኑና ሀብት እንዲያፈሩ የማድረግ ፍላጎት አለን። አንዲት ድሃ ሴት እዚህ ደረሰች ማለት ተንገላትቼ ልጆቼን ላሳደግኩት ለእኔ ትልቅ ኩራት ነው። ለሕፃናቱና ለእናቶች በምናደርገው ድጋፍና የሰብዕና ግንባታ ጥሩ ውጤት አይተናል። ልጆቹ መልካም ልጆች ናቸው፤ ሰዎች ሲጎበኟቸው ስለመልካም ባህርያቸው ይመሰክሩላቸዋል። በድርጅቱ እገዛ አድገውና ተምረው ከኮሌጅ የተመረቁና ተቀጥረው የሚሠሩ ልጆች አሉ፤ በዚህ ዓመትም የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚፈተኑ አሉ›› በማለት የሥራቸውን ፍሬያማነት ያስረዳሉ።

‹‹ላይፍ ሴንተር›› በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ በዋግኸምራ ዞን፣ ሰቆጣ አካባቢም የበጎ አድራጎት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ድርጅቱ በአካባቢው ለሚኖሩ 58 ልጆች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም ዘጠኝ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል። ውሃውን በመጠቀም 10 ሴቶች በግብርና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አድርጓል። በብድር አገልግሎት 45 ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በቀጣይ ቀናት ይህ ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል።

‹‹ላይፍ ሴንተር›› ለሚያከናውናቸው ተግባራት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው በአሜሪካ ከሚገኙ በጎ አድራጎ ግለሰቦችና ተቋማት እንደሆነ ወይዘሮ ሙሉ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያውያንም በመሰል ተግባራት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባቸውም ይመክራሉ።

በቀጣይም ድርጅቱ ሥራውን በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የማስፋት እቅድ እንዳለው ወይዘሮ ሙሉ ይናገራሉ። ‹‹የውሃ፣ የሥራ አጥነት… ችግሮች ያሉባቸው በርካታ አካባቢዎች ስላሉ ሥራውን ማስፋት እንፈልጋለን። ወደ ከተሞች የሚፈልሱትን ሕፃናትና ሴቶች ባሉበት ቦታ ሆነው እገዛ እንዲያገኙ ማድረግ የተሻለ ነው። ልጆች አድገውና ተምረው ሥራ አጥ እንዳይሆኑ የሙያ ትምህርት ቤት የመክፈት እቅድም አለን›› በማለት ስለተቋሙ የወደፊት እቅዶች ይገልጻሉ። የበጎ አድራጎት ተግባራትን የሚያከናውኑ ምግባረ ሰናይ ተቋማት ልምዶቻቸውን የሚለዋወጡባቸው መድረኮች እንዲኖሩም ምኞታቸው ነው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *