በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በአኗኗር ዘይቤ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሲያመጡ እነዚህ ጉልህ ለውጦች የቴክኖሎጂ አብዮቶች ተብለው ይጠቀሳሉ። በታሪክ ብዙ የቴክኖሎጂ አብዮቶች ተመዝግበው ይገኛሉ። የግብርና አብዮት፣ የኢንዱስትሪ አብዮት፣ አረንጓዴው የግብርና አብዮት፣ የባዮቴክኖሎጂ አብዮት እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮት ተጠቃሾች ናቸው። እያንዳንዱ የቴክኖሎጂ አብዮት የራሳቸው የሆነ ልዩና ጉልህ ለውጦች የታጀቡ ሲሆን አንዳንድ አገራት በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ሆነው እናገኛቸዋለን።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በቀደምት ዓመታት በሥልጣኔው ግንባር ቀደም ከሚባሉ አገራት ተርታ ቀድማ ብትሰለፍም፤ አሁን ላይ በቴክኖሎጂው ዳዴ እያለች ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህን እውነታ በመቀየር አገሪቷን በቴክኖሎጂው ከበለፀጉ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ቀን ከሌሊት በመታተር የተለያዩ ችግር ፈች የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት ለአገርና ለወገን እያቀረቡ የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ብዙ ዜጎች አሉ።
ከእነዚህ ታታሪ ዜጎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አማረ ቸሬ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ኮሌጅ በ1976 ዓ.ም በሕንፃ ምህንድስና ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የመስራት ልምድና ፍቅር አላቸው። እርሳቸውም የብረታ ብረት ወርክሾፕ ከፍተው የተለያዩ የብረታ ብረትና የምህንድስና ሥራዎችን የሚሰሩ ሲሆን፤ በእረፍት ጊዜያቸው ሰዎች ክብደት ያላቸውን ዕቃ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስና ማጓጓዝ የሚያስችላቸው የፈጠራ ሥራን ለምን አልሰራም በሚል ተነሳሽነት «በእግር በሚገፋ ፔዳል ክብደት ያለው አንድን ዕቃ ማንሳትና ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ የሚያስችል» የፈጠራ ሥራ ሰሩ። የፈጠራ ሥራው ለአገር እድገት ያለው ፋይዳ ምን እንደሚመስል አቶ አማረ ቸሬ ይናገራሉ።
እንደ ፈጠራ ባለቤቱ ገለጻ፤ የፈጠራ ሥራው የብስክሌት ፔዳል የተገጠመለት ሲሆን፤ ፔዳሉን በማሽከርከር ማሽኑ ላይ በተገጠመው አራት የመጠቅለያ ገመድ ወይም ካቦ (ጥቅል የሽቦ ገመድ) አማካኝነት አንድን ከባድ ዕቃ በቀላሉ ከታች ወደላይና ከላይ ወደታች እንዲሁም ወደ ግራና ቀኝ ለማንቀሳቀስና ለማጓጓዝ የሚያገለግል የፈጠራ ሥራ ነው።
ከአምስት ዓመት በፊት የፈጠራ ሥራውን እንደሰሩት የጠቆሙት አቶ አማረ፤ የፈጠራ ሥራውን የተሻሻለ ቁሳቁስ በመጠቀም ከሰሩ በኋላ ያለውን ክፍተት በተጨባጭ በማየት እንደገና ማሻሻላቸውን ይገልፃሉ። እንደእርሳቸው ገለጻ፤ የመጀመሪያዋን የፈጠራ ሥራ የሰሩት ፌሮ ብረትን በመጠቀም ነበር።
ነገር ግን የመጀመሪያውን ከብረት የተሰራውን የፈጠራ ሥራ በመበተን ዳግም አሻሽለው ሲሰሩ መጀመሪያ ከሰሩት ዕቃን ወደታችና ወደ ላይ ብቻ የማጓጓዝ ተግባር በተጨማሪ ዕቃን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀሻ ማሽን እንዲሆን አስቻሉት።
ተሻሽሎ የተሰራው የዕቃ ማጓጓዣ ማሽን ከበፊቱ በተሻለ ክብደት ያላቸው ዕቃዎችን ለማጓጓዝ እንዲያስችል ጠንከር ተደርጎ በጥራት መስራታቸውን ይጠቁማሉ። ስለዚህ በግራና በቀኝ ሚዛኑን እንዲጠብቅ በማድረግ በአንዴ ወደ ላይና ወደታች ወይም ከግራና ከቀኝ በኩል በቀላሉ 80 ኪሎ ክብደት የሚመዝን ዕቃን በፍጥነት ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ ያስችላል።
በተጨማሪም ሚዛን መጠበቂያ ክብደት በተቃራኒው በኩል እንዲኖር በማድረግ የሕንፃ ግንባታ በሚካሄድበት ወቅት በሰው ኃይል ሕንፃዎች ላይ ለማውጣትና ለማውረድ አስቸጋሪ የሆኑ እንደ ጀነሬተርና ቫይብሬተር የመሳሰሉ ማሽኖችን በቀላሉ እስከተፈለገው ወለል ድረስ ማውጣትና ማውረድን የሚያስችል አድርገውታል።
የፈጠራ ሥራቸው በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በ2011 ዓ.ም የተመዘገበ ሲሆን፤ የፈጠራ ባለቤትነት መብት የምስክር ወረቀትም አግኝተዋል። የፈጠራ ሥራቸውንም በቀላሉ በአገር ውስጥና በአካባቢው የሚገኙ የውጭ ምንዛሬ የማይጠይቁ እንደ ብረት፣ ችንጋ፣ ሰንሰለት፣ የጋሪ ጎማ፣ ገመድ፣ ካቦ እንዲሁም የብስክሌት ቁሳቁሶችን ለፈጠራ ሥራው ተስማሚ እንዲሆን አድርጎ በመቀየር በግብዓትነት ተጠቅመውበታል።
አቶ አማረ የፈጠራ ሥራው ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን ፋይዳ እንዳብራሩት፤ በአገሪቱ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ወጪንና ጊዜን የሚቆጥቡ ሲሆን፤ ትልልቅ ሕንፃዎች ግንባታቸው በሚከናወንበት ወቅት ከፍተኛ ወጪ፣ የሰው ኃይል፣ የነዳጅና የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ሳያስፈልግ በቀላሉ ከመሬት (ከግራውንድ) እስከ ተፈለገው ወለል ድረስ የተለያዩ ክብደት ያላቸው የግንባታ ቁሳቁሶችንና ለግንባታ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች በሰው ኃይል ለማውጣትና ለማውረድ የሚያስቸግሩ ቁሳቁሶችንና ማሽኖችን ለማውጣትና ለማውረድ ያስችላል።
እንዲሁም የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የነዳጅ እጥረት ቢከሰት ሊፍት (አሳንሰር) ይቆምብኛል ብሎ ስጋት ሳይኖር፤ በትንሽ የሰው ኃይል በቀላሉ ለሕንፃ ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እስከተፈለገው ወለል ድረስ ማቅረብ ያስችላል። በአጠቃላይ የመሠረተ ልማት የግንባታ ሥራ የተሳለጠ ከማድረጉም ባሻገር ከፍተኛ ወጪን እና ድካምን የሚቀንስ ነው ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ሰሚት
አካባቢ ሲገነባ በነበረ አንድ ባለአራት ወለል የሕንፃ ግንባታ ላይ የፈጠራ ሥራው ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ መቻላቸውን ያወሱት የፈጠራ ባለቤቱ፤ በትንሽ የሰው ኃይል ያለምንም ብክነት የፈጠራ ሥራውን በመጠቀም በሦስት ቀን ዘጠኝ ሺ ብሎኬቶችን ከአንደኛ እስከ አራተኛ ወለል ድረስ ማጓጓዝ መቻላቸውን ገልጻዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ይሄንን ብሎኬት በሰው ኃይል ከግራውንድ ወደ አራተኛ ወለል ይውጣ ቢባል አንድ ጠንካራና ጎበዝ የቀን ሠራተኛ እስከ አራተኛ ወለል ቢያንስ በቀን 200 ብሎኬቶችን ቢያወጣ ነው። ስለዚህ ይህ ሰው ይሄንን ዘጠኝ ሺ ብሎኬቶች ወደ አራተኛ ወለል ለማውጣት ቢያንስ አንድ ወር ከ15 ቀናት ይፈጅበታል።
ስለዚህ ባለሀብቱ ሥራው ከሚጓተት በአንድ ቀን ብሎኬቶቹ ወደ አራተኛ ወለል ይውጣ ቢል 45 ሰዎች ያስፈልጉት ነበር። በመሆኑም በወቅቱ በነበረው የቀን ሠራተኛ አማካኝ የቀን ክፍያ ሁለት መቶ ብር ለ45 የጉልበት ሠራተኞች ቢከፍል ዘጠኝ ሺ ብር መክፈል ግድ ይለው ነበር።
በተጨማሪም በሰው ኃይል ብሎኬቶቹ በሚጓጓዙበት ወቅት በመሰባበር ብክነት ይከሰት ነበር። ነገርግን ባለሀብቱ ይሄን የፈጠራ ሥራ በመጠቀም በትንሽ የሰው ኃይል ጊዜንና ወጪን ቆጥቦ ያለምንም ብክነት የግንባታ ሥራውን በማሳለጥ የግንባታ ሥራውን ማከናወን ችሏል ይላሉ።
የፈጠራ ሥራው በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላልና ምቹ በመሆኑ በየትኛውም ቦታ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን፤ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የፈጠራ ሥራውን በመጠቀም ውሃን ከወንዝ ወይም ከጉድጓድ ውስጥ ጠልፎ በማውጣት የጓሮ አትክልት ለማልማት እና ለእንስሳት የመጠጥ ውሃ በቀላሉ ለማቅረብ እንደሚረዳም ነው የገለፁት።
ሲሚንቶ፣ እህልና የግንባታ ቁሳቁሶችን በቀላሉ ከመኪና ላይ ለማውረድና ለመጫን የሚያገለግል ሲሆን፤ በመጋዘን ውስጥ መሰል ዕቃዎችን በትንሽ የሰው ኃይል ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ያስችላል። በተጨማሪም ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕቃ ማውረጃና ማውጫ አገልግሎት መዋል ይችላል ይላሉ።
የፈጠራ ሥራውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ቁሳቁሶችን በመጠቀም ተሻሽሎ ቢሰራ፤ ከዚህ በተሻለ ጥቅም እንዲሰጥ በማስቻል የተለያዩ ከባድ ዕቃዎችንና ማሽኖችን ጨምሮ ለማንሳት እንደሚያስችል ይናገራሉ።
«የተለያዩ የፈጠራና የብረታ ብረት ሥራዎችን ስለምሰራ የፈጠራ ሥራውን ስሰራ ያጋጠመኝ የቴክኒክም ሆነ የክህሎት ችግር አልነበረም» የሚሉት አቶ አማረ፤ የፈጠራ ሥራውን የሚያከናውኑበት የመስሪያ ቦታ ማጣት፤ በመንግሥትና በባለሀብቱ ዘንድ የፈጠራ ሥራውን የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ ተደርጎ እንዲሰራ የሚደረግ ድጋፍ አለመኖር እና በመንግሥት በኩል በተሳካ መልኩ የፈጠራ ሥራ ለሚሰሩ ሰዎች ለመስራት የሚያስችላቸው የብድር አገልግሎት አለመመቻቸት ጋር ተያይዞ ችግሮች መኖራቸውን አውስተዋል።
እንደአቶ አማረ፤ ለፈጠራ ሥራው የፈጠራ ባለቤትነት መብት የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ከማግኘታቸው ውጪ የፈጠራ ሥራውን ሲሰሩም ሆነ ከሰሩ በኋላም ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ከመንግሥት ባለድርሻ ተቋማትም ሆነ ከባለሀብቶች ምንም ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ተናግረዋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው አውደ ርዕይ የፈጠራ ሥራቸውን እንዲያሳዩ ከመጋበዝ ውጪ ሌላ ለፈጠራ ሥራቸው የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለም አክለው ይገልፃሉ።
የፈጠራ ሥራውን በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ እና የብድር አገልግሎት እንዲሁም የመስሪያ ቦታ ባለማግኘታቸው እስካሁን ለገበያ ማቅረብ አለመቻላቸውን ገልጸው፤ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ምቹና ለማንኛውም የሥራ ዓይነት ለማዋል አመቺ በመሆኑ፤ ማንኛውም ሰው እንደ ሥራ ባህሪው የፈጠራ ሥራውን አሰርቶ መጠቀም እንደሚችልም ነው የሚናገሩት። የፈጠራ ሥራውን በዓይነት፣ በጥራትና በብዛት ለማምረት የሚያስችላቸው ፋይናንስና የብድር አገልግሎት ከአገኙ ለገበያ በማቅረብ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
የፈጠራ ባለቤትነት የምስክር ወረቀት ያላቸው ሰዎች የፈጠራ ሥራቸውን ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉበትና ሥራቸውን የሚያሻሽሉበት የተለያዩ ድጋፎች በመንግሥት ዘንድ ሊደረግላቸው ይገባል ይላሉ። ስለዚህ በመንግሥት በኩል እንደ ፈጠራ ባለቤቶቹ ፍላጎት የተለያዩ የብድር አገልግሎትና የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት በፈጠራ ዝንባሌያቸው በማደራጀት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። እንዲሁም ማህበረሰቡ የፈጠራ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን በመደገፍና በማበረታታት የተሻለ የፈጠራ ሥራ እንዲሰሩ በማድረግ በአገር ውስጥ የተሰሩ ቴክኖሎጂዎችንና ምርቶችን በመጠቀም የተሻለ ጥራት ያላቸው ቴክኖሎጂዎች እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ አማረ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በሶሎሞን በየነ