ለፋሽን ኢንደስትሪው መስፋፋት የኢንተርፕራይዞች ሚና

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር በየጊዜው የሚሰሯቸው የፋሽን አልባሳት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሲደረግ አይታይም፡፡ ተቋማቱ በቆዳ፣ በጨርቃ ጨርቅ /በቴክስታይል/ እና በጋርመንት (አልባሳት) ዘርፍ የሚሰሯቸው ሥራዎች ለበዓል ማድመቂያነት እንዲውሉ ከማድረግ ባሻገር ትኩረት ተነፍጓቸው ስለመቆየቱ በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ የሚዘጋጀው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

ተቋማቱ ዓመቱን በሙሉ በብዙ ድካምና ልፋት የሚያዘጋጇቸውን የፋሽን አልባሳት የቴክኒክና ሙያ ሳምንቱ ማድመቂያ ከሆኑ በኋላ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሰጡ ወይም በጨረታ እንዲሸጡ ሲደረግ መቆየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ አሁን ላይ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ ተቋማቱ የሚያዘጋጇቸውን የፋሽን አልባሳት ህብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ የቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ አብዲ አወል ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እስከዛሬ ድረስ በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ (በቆዳ፣ በጨርቃጨርቅ (በቴክሳታይል)፣ በአልበሳት (ጋርመንት) የሚያዘጋጇቸውን የፋሽን አልባሳት የፋሽን ትርዒት ላይ ከማቅረብ በዘለለ ሥራዎቻቸው ትኩረት ተሰጥቷቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች አሉ፡፡ ተቋማቱ እምቅ ችሎታቸውን ተጠቅመው በርካታ ሥራዎችን በየጊዜው እየሰሩ ቢሆንም ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡

ከዚህ ቀደም በየዓመቱ የሚያዘጋጇቸው አልባሳት በቴክኒክና ሙያ ሳምንት ላይ የፋሽን ትርዒትን ለማቅረብ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ አልባሳቱ ከፋሽን ትርዒቱ በኋላ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚሰጡበት ወይም በጨረታ የሚሸጡበት መኖራቸውን ባለሙያው ይጠቁማሉ፡፡

ዘንድሮ ተቋማቱ ለሚሰሯቸው የፋሽን አልባሳት በተለያየ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ጠቅሰው፣ የተቋማቱን ሥራዎች ለኢንተርፕራይዞች እንዲሸጋገሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉም ይገልጸሉ፡፡ የተመረጡት አልባሳት ልክ እንደ ቴክኖሎጂ ትኩረት አግኝተው ለኢንተርፕራይዞች እንዲሸጋገሩ መደረጉን ይናገራሉ፡፡ ኢንተርፕራይዞች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን እያባዙ ለህብረተሰቡ እንደሚያስተላልፉ ሁሉ አልበሳቱንም ለማስተላለፍ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመላክተዋል፡፡ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ በተካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በተቋማቱ መካከል የፋሽን ትርዒትና የአልባሳት ዲዛይኒንግ ውድድር ተካሄዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አብዲ፤ ውድድሩ ከሌላ ጊዜ ለየት ባለመልኩ መከናወኑንም ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በውድድሩ ተቋማቱ ከግብዓት እና ከሰው ኃይል አንጻር እኩል አቅም የሌላቸው ስለመሆኑ የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም ስምንት ኮሌጆችና ስድስት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን ለየብቻቸው በማወዳደር ከየመደቡ ሁለት ሁለት ተወዳዳሪዎች ለአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ በውድድሩም ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ምስራቅ እና ተግባረ እድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ለአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ሲያልፉ፤ ከኮሌጆች ደግሞ ኮልፌና ጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች ለውድድር የቀረቡ ናቸው፡፡

ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት፤ በውብና ማራኪ ዲዛይነር የተሰሩ የቆዳ፣ የቴክስታይል እና የጋርመንት ሥራዎች የቀረቡበት እንደነበር ነው አቶ አብዲ የሚናገሩት። ውድድሩን ምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአንደኝነት ማጠናቀቁንም ገልጸዋል፤ ተግባረ እድ ፖሊቴክኒክ፣ ኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እና ጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች እንደቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይም በዲዛይነሮች መካከል በተመረጡት ሦስት ዘርፎች የዲዛይኒንግ ውድድር መካሄዱን አስታውሰው፤ በዚህም ከተቋማቱ ምርጥ ተብለው የተለዩ ሦስት አሰልጣኝ ዲዛይነሮች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ይናገራሉ፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቴክኖሎጂዎችን ለኢንተርፕራይዞች በማሸጋገር እንዲባዙ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገርም ከውጭ ሀገር የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ከዋና ዋና ግቦቻቸው አንዱ መሆኑን አቶ አብዲ ይጠቁማሉ፡፡ በውድድሩ የቀረቡት አልባሳትና የቆዳ ምርቶች በእጅጉ ለየት ያሉና ማራኪ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ እነዚህን መሰል አልባሳት ከውጭ ከሚገቡት በሀገር ውስጥ የሚባዙበት ሁኔታ ቢመቻች ከውጭ ሀገር የሚመጣውን መተካት እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ከዚህ ባሻገርም ለኢንተርፕራይዞች የሥራ እድል ፈጠራም ከፍተኛ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠቁማሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የጨርቃጨርቅ አልባሳት በሀገር ውስጥ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉና በከፍተኛ ደረጃ ችግር ፈቺ የሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህ የተመረጡ አልባሳት ለኢንተርፕራይዞች መሸጋገራቸው፣ መባዛታቸውና ለህብረተሰቡ መድረሳቸው ላይ ባሉት ሂደቶች ላይ የዳሰሳ ጥናት ይካሄዳል፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ የሚገኘውን ግብረ መልስ መሰረት በማድረግ በየጊዜው እየተሻሻሉና እየዘመኑ በተሻለ መልኩ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

አልባሳቱን ለማባዛት የሚመረጡ ኢንተርፕራይዞችም አቅማቸው፣ ሙያቸው (ክህሎቱ) እና በቂ የሰው ኃይል ያላቸው መሆኑ በደንብ በማየት እንደሚመረጡ አቶ አብዲ ገልጸዋል፤ አልባሳቱ ወደ ኢንተርፕራይዞች ሲሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞቹ ጋር የአልባሳቱን ዲዛይኖች ለማባዛት በቂ እውቀት ላይኖር ይችላል በማለት፤ ይህንን ችግር ለመፍታትም ቀደም ብሎ የአዋጭነት ትንተና የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚያም የተመረጡ ኢንተርፕራይዞች የዲዛይኒንግ ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚደረግ ነው ያመለከቱት፤ የሙያ ክፍተት ያለባቸውም በኮሌጅ ባለሙያዎች በነጻ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት አቅማቸውን እንዲያዳብሩ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡

አቶ አብዲ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለፋሽን ኢንዱስትሪ እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተቋማቱና ምርቶቻቸው ግን ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱን ነው የገለጹት፤ በተቋማቱና ምርቶቻቸው ላይ ህብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው የሚሉት አቶ አብዲ፣ ሚዲያው ሽፋን በመስጠት ረገድ ክፍተት ያለበት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ በቆዳ፣ በቴክስታይልና በጋርመንት ዘርፍ ለሚሰሯቸው ሥራዎች ከግብዓት፣ ከቁሳቁስና ከሰው ኃይል አንጻር ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ አንዳንድ ተቋማት ከአልባሳቱ በተጨማሪ ጫማዎችንም የማምረት አቅም እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ የፋሽን ኢንዱስትሪውን ሊያሳደጉ የሚችሉ ሥራዎች መስራት እንዳለባቸው አቶ አብዲ ተናግረው፤ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘንድሮ በፋሽን አልባሳት ውድድሩ ያሸነፉ ተቋማት በከተማ የተለያዩ ቦታዎች በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ማህበረሰቡን በማንቃት ውብ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የፋሽን ኢንዱስትሪው ቢሰራበት ከውጭ ሀገር የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ባማረ መልኩ ዲዛይን በተደረጉ አልበሳት በከፍተኛ ሁኔታ መተካት እንደሚቻል ያነሱት አቶ አብዲ፤ ዘንድሮ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ በሚደረገው ዳሰሳ ጥናት መስተካከል ያለባቸው ነገሮችና ክፍተቶችን በመቅረፍ ከፍተኛ ካፒታል ማውጣት ሳያስፈልግ ልምዱን በመስጠት ብቻ ለበርካቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *