የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከቻድ አቻቸው ጋር የኦሊምፒክ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም ያከናውናሉ። ጨዋታውንና የቡድኑን ዝግጅት አስመልክተው አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ትናንት በኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሠልጣኙ ለኦሊምፒኩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከዋናው የሉሲዎች ስብስብ ከሦስት ተጫዋቾች በስተቀር እንዳልተካተቱ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የወጣትና ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖችን በማሠልጠን የሚታወቁት አሠልጣኝ ፍሬው፣ ለኦሊምፒክ ማጣሪያ በአብዛኛው ለወጣትና አዳዲስ ተጫዋቾች እድል መስጠታቸውን የገለፁ ሲሆን፣ በርካቶቹ ተጫዋቾችም በመካከለኛና ምስራቅ አፍሪካ(ሴካፋ) ከ20 ዓመት በታች የተሳተፉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በዚህም ብሔራዊ ቡድኑን ለረጅም ዓመት የሚያገለግሉ ተጫዋቾችን ማፍራት ዓላማቸው አድርገው እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የዛሬውን የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታ በተመለከተ አሠልጣኙ ሲናገሩም፣ ‹‹ተጫዋቾቼ የተሻለ ነገር ይዘው ለመምጣት እንደሚችሉ መናገር እችላለሁ፣ ተጫዋቾቹ ከረጅም ጊዜ እረፍት በኋላ ነው ወደ ዝግጅት የገቡት ፣ እኔም ወደ ነበሩበት አቅም እንዲመለሱ ሰርቻለሁ›› በማለት ተናግረዋል፡፡
እንደ አሠልጣኙ ገለፃ፣ የሉሲዎቹ የዛሬ ተጋጣሚ ስለሆኑት የቻድ ብሔራዊ ቡድን አንዳንድ ነገሮችን ለማጣራት ሞክረው ብዙ መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉም፡፡ ያም ሆኖ ሉሲዎቹ ባለፉት የዝግጅት ቀናት ከሜዳ ላይ የተግባር ሥልጠና በተጨማሪ የንድፈ ሃሳብ ሥልጠና እየወሰዱ ደካማና ጠንካራ ጎናቸውን እንዲያውቁ ጥረት ተደርጓል፡፡
በመጪው የፈረጆቹ ዓመት 2024 ፓሪስ ትልቁን የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክን በታሪኳ ለሶስተኛ ጊዜ ታስተናግዳለች፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ለመሆን በየአህጉሩ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ሉሲዎቹ የሚያደርጉት ማጣሪያ የዚህ አንዱና የመጀመሪያው አካል ነው፡፡
በኦሊምፒኩ በሴቶች እግር ካስ አፍሪካን በመወከል ሁለት ሀገራት ተሳታፊ ይሆናሉ። አህጉሪቱን ለመወከልም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሥር የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች አራት ዙር ባለው የማጣሪያ ውድድር ላይ መካፈል የግድ ይላቸዋል፡፡ በዚህ ማጣሪያ ላይ ከሚካፈሉ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ብሄራዊ ቡድኗም በዞኑ የመጀመሪያ ዙር ማጣርያ ከቻድ ጋር መደልደሉ የሚታወቅ ነው። ሉሲዎቹ በዓለም ሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ከዓለም 125 ደረጃን ይዘው ሲገኙ ተጋጣሚያቸው ቻድ በበኩሏ በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ካልተሰጣቸው ሀገራት ተርታ ትመደባለች። የሁለቱ ሀገራት አሸናፊ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያውን ከናይጄርያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያከናውን ይሆናል፡፡
ቡድኑ ለዚህ ጨዋታ እንዲረዳውም ካለፈው ወር ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል በመሰባሰብ ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲያደርግ ቆይቷል። በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የሉሲዎቹ ስብስብ በዝግጅት ሂደቱ ከሲሼልስ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ለማድረግ መርሃ ግብር ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ፤ የሲሼልስ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በገጠመው ችግር ምክንያት ጨዋታውን ማድረግ እንደማይችል በደብዳቤ በማሳወቁ ሊካሄድ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ደበሶ ከተባለ የወንዶች ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኗል።
ሉሲዎቹ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በሚያደርጉት መደበኛ ልምምድ ላይም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተው ተመልክተዋል።የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳኛቸው ንግሩ እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ አቶ ሸረፋ ዱለቻ እና ወይዘሪት ብዙአየሁ ጀምበሩ ልምምዱ ላይ እንደተገኙም ፌዴሬሽኑ በድረገጹ ጠቁሟል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2015