ራሱን ማከም የማይችል ሐኪም

 ለበርካታ ወራት ተሰውሮ የነበረው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬ በሠፈራችን ተከስቷል፡፡ በሠፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል፡፡ ወደ በተስኪያን የሚሄዱት የእኛ ሰፈር ሰዎች፤ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬ ስለተከሰተ በተስኪያን መሄዳቸውን ትተው ንግግሩን ለማዳመጥ ወደ ዋርካው ስር ተሰባሰቡ፡፡

ይልቃል አዲሴ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው ዛሬም ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ስር እስኪሰበሰቡ ድረስ “ሀቡ ዘነጋሲ ለነጋሲ ፤ ወግዚአብሔር ለእግዚብሔር (የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ፡፡)” እያለ የተለመደ ዲስኩሩን በጩኸት ይናገር ጀመረ፡፡

የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታ ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ፤ ይልቃል አዲሴ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ እህ.. እህ… ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ ‹‹ አሁን አሁን የኑሮ ውድነት እንድ ዓለማችን የጋራ ችግር ሆኖ እየተመለከትነው እንገኛለን፡፡ በዓለም ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት የኑሮ ውድነት ተከስተዋል፡፡ ለእነዚህ የኑሮ ውድነት መንስኤው አንድም ፖለቲካዊ ለውጥ ነው ፡፡ ሁለትም ከጦርነት ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነው፡፡ አሁን በእኛ ሰፈር እና እድር የተከሰተው የኑሮ ውድነት አብይ ምክንያት በዓለም ላይ እየተፈጠረ ያለው አዲስ የፖለቲካ አካሄድ እና የኃይል አሰላለፍ ይመስለኛል፡፡

ታሪክ የበፊት ማንነታችንን የሚያሳይ መነፅር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ቀደም ባሉ ጊዜያት የሰው ልጅ ሊቋቋማቸው የማይችላቸው የኑሮ ውድነቶች ውስጥ ማለፉን ከታሪክ አይተናል፡፡ ይህ የሆነው ግን አንድም በአንድ ሀገር አብዮት ፍንዳታ ሲያጋጥም፤ ሁለትም አንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የመሰለ ዓለምን የሚያናጋ እና የዓለምን የኃይል አሰላለፍ የሚቀይር ጦርነት ሲከሰት ነው፡፡

ከዚህ አንጻር አሁን በዓለማችን የተከሰተው የኑሮ ውድነትም በዓለማችን አዲስ የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ መኖሩን አመላካች ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን ሳነሳ ከሰሞኑ አንድ ጓደኛዬ ያወራኝን አስታወሰኝ፡፡ ያለፈው ሳምንት ቅዳሜ አዳሩን ሲያቃዠው በማደሩ በሰፈራችን ህልም መፍታት የሚታወቁትን እመይቴ ማን አህሎሽን ህልም ለማስፈታት የእጅ መንሻ የምትሆን አንድ ቁና እህል ይዞ ወደ ቤታቸው ይሄዳል፡፡

እመይቴ ማናህሎሽ ቤት ደርሶም ‹ደህና አደራችሁ?› ሲል አንድ ኮረዳ ቢጤ በደሳሳ ጎጇቸው በር አንገቷን ሰገግ አድርጋ ወደ ቤታቸው የመጣውን ሰው እያየች እመይቴ ማን አህሎሽ መኖራቸውን ገና ሳይጠይቃት ‹እሜቴን ፈልገህ ነው ? እርሳቸው የሉም› አለች ፡፡ ራሷ ጠያቂ ራሷ መላሽ ሆና ፡፡

ጓደኛዬም ለምን እንደመጣ ሳትጠይቀው ለምን እሜቴ የሉም ብላ እንደመለሰችለት ስለገባው ወደ ቤቱ ተመልሶ ለመሄድ ዘወር ያለ መስሎ፤ ሆነ ብሎ ከኪሱ ድፍን ድፍኑን ብር ሞዥረጥ አድርጎ መቁጠር ጀመረ። ወዲያውኑ እሜቴ የሉም ብላ የነበረችው ልጅ ‹ይቅርታ ጋሽዬ እመይቴ እሜቴ የሉም ያልኩህ ጎረቤት ሂደው ስለነበር ሳላያቸው በኋላ በር ገብተው ኖሮ ሲጠሩኝ መኖራቸውን አየሁ፡፡ ና ግባ ትለዋለች፡፡ ጓደኛዬም የልጅቱ አድራጎት ቢያናድደውም ንዴቱን ዋጥ አድርጎ ለእጅ መንሻ የያዛትን አንድ ቁና እህል ከጭቃ ከተሰራች መደብ ላይ አስቀምጦ እመይቴ ማን አህሎሽን እጅ ነሳ እና ተቀመጠ፡፡

እመይቴ ማን አህሎሽን ከጥጥ የተሰራ ነጠላቸውን ተከናንበው ከበሬ ቆዳ በተሰራ ምንጣፍ ላይ ቁጭ ብለዋል፡፡ ሰላምታ ከተቀያየሩ በኋላ የመጣበትን ጉዳይ ያስረዳል፡፡ ጥሩ ! ይህን ህልም እንዲፈታልህ ፈልገህ ከሆነ ‹ቀድሚያ ክፍያ ክፈል› ይሉታል።‹ስንት ልክፈል?› ብሎ ይጠይቃል፡፡ እመይቴ ማን አህሎሽንም ‹አንድ መቶ ብር› አሉ፡፡ ጓደኛዬም ‹ምነው እማማ ህልም ለመፍታት አንድ መቶ ብር አይበዛም?› ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ እመይቴ ማን አህሎሽንም ‹በዩኩሬን እና በራሸያ ጦርነት ምክንያት ዋጋ ማስተካከያ አድርገናል፡፡› ብለውት አረፉት፡፡

ወደ ነበርኩበት ልመለስና›› ብሎ ይለቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጠለ ‹‹ ..በአዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ ወይም በአዲስ የፖለቲካ አብዮት ከሚፈጠሩ የኑሮ ውድነቶች ለማምለጥ ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች በሚችሉት ሙያ ላይ ንቁ ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሲባል ፖለቲከኛው በፖለቲካው ፤ መምህሩ በማስተማሩ፣ አርሶአደሩ በእርሻው ወዘተ፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ በሰፈራችን እንደሚታየው ገበሬውም ፣ ቄሱም ፣ ሼኩም ፣ ተማሪውም ፖለቲከኛ ሆነ፡፡ ገበሬውም ፣ ቄሱም ፣ ሼኩም ፣ ተማሪውም ፖለቲከኛ ከሆነ በዓለም ላይ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት መቋቋም አንችልም፡፡ አይደለም በዓለም በሀገራችን የሚፈጠሩ ጥቃቅን ኩነቶች ከሚፈጥሯቸው የኑሮ ውድነት ማዕበሎች መውጣት አንችልም፡፡ በዩኩሬን እና በራሺያ ጦርነት ብናመካኝ እንኳን ከሞት ማምለጥ አንችልም፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ጠበብት እንደሚናገሩት አንድ ጤናማ ፖለቲካ በምታካሂድ ሀገር 10 ከመቶ ያልበለጠ ህዝቦቿ በፖለቲካው መስክ ይሳተፋሉ፡፡ የቀረው 90 በመቶው ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በዚህ አካሄዳቸውም የሀገራቸውን ሁለንተናዊ ለውጥ ማፋጠን ችለዋል፡፡ አብዛኛው አምራች ሃይል በፖለቲካው ተሳታፊ ከሆነ ግን የኑሮ ውድነቱን ከማባባሱ ባሻገር የሀገረ መንግሥቱ እንደ ሀገረ መንግሥት መቀጠሉ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ የልጆቻችንን ነገን በመቀማት ልጆቻችንን ሀገር አልባ እናደርጋለን፡፡ ስለሆነም መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት በቅጡ መወጣት አለበት፡፡›› ትንሽ ትንፋሽ ወሰደ፡፡

ይልቃል አዲሴ ንግግሩን እንደገና ቀጥሎ “የጀግና ሰው መልኩ ሁለት ብቻ ነው ፡፡ አንድም መሰዋት መሆን ሌላኛው የወደ ፊት እድሉ ነው ፡፡ ፖለቲካን ሰበብ አድርጎ የሚሰርቅ ፣ ሰው የሚገድል ፣ የሚያፈናቅል ሰው እንዲሁ መልኩ ሁለት ብቻ ነው ፡፡ አንዱ ተቀጥቅጦ ተዋርዶ መሞት ሲሆን፤ ሁለትም ተዋርዶ እና ተንቆ ቀማኛ! ሌባ! እየተባለ እየተሰደበ መኖር ነው፡፡ ጀግና ቢሰዋም ታሪኩ በጥሩ ነገር እየተወሳ ለመልካም ነገር ምሳሌ ይሆናል። በሚደረገው ተጋድሎ ከሞት ከተረፈም በሱ ልክ ለሀገር የሚጠቅሙ ሰዎች እያዘጋጀ ወገኖቹን ያጀግናል! ይመራል፡፡ ሌባ እና ዘራፊ ግን ሲሞትም የሚሞተው የእርኩስ ሞት ነው! ቀባሪ እንኳን አያገኝም፡፡

ሌባና ዘራፊ ሰፈራችሁን ሊያጠፋ በመጣ ጊዜ የማይካለከል ሰውም ከሌባው እና ከቀማኛው እኩል ነው፡፡ አንድም በዘራፊው በደል ይደረስበታል፡፡ ሁለትም ሰፈሩን ከቀማኞች እና ከገዳዮች መከላከል ያልቻለ ፈሪ እየተባለ ሲሰደብ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ለሰፈራችሁ የሚያስቡ በመምሰል የፖለቲካ መለያ ያንጠለጠሉ የእናንተን ነገ ከሚነጥቁ ነጣቂዎች ራሳችሁን ጠብቁ! ይህንን ካደረጋችሁ ጅግና ናችሁ፡፡ ካላደረጋችሁ ግን የእነሱ አባሪ እና ተባባሪ ሆናችሁ በታሪክ ተወቃሽ መሆናችሁ የማይቀር ነው” ብሎ ይልቃል አዲሴ እየተናገረ እያለ፤ ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ እንደተለመደው ዛሬም የይልቃልን ንግግር አቋረጠው፡፡

አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ የይልቃልን ንግግር ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው ገልጾ፤ ንግግሩን እንዲህ ቀጠለ‹‹… ይልቃል አዲሴ ለነገሮች ትርጉም በመስጠት እና በመተንተን የሚያክለው የለም ፡፡ ይሁን እንጂ የአሁን ዘመን አንዳንድ ፖለቲኛ ነን ባዮችን ከሚሰሩት ሥራ ተነስተው እኩይ ምግባራቸው የሚሆን ሁነኛ ስም ያገኘላቸው አልመሰለኝም፡፡ እንዴትስ ስም ሊያገኝላቸው ይችላል?

ምክንያቱም የአሁን ዘመን አንዳንድ ፖለቲከኛ ነኝ ባዮች ንጹሃንን የሚያስገድሉ፤ ከህጻናት እስከ መነመኮሳት የሚያስደፍሩ እና የሚደፍሩ፣ የሀገርን ንብረት በማውደም ሃሴት የሚያደርጉ ፣ በአጋጣሚ አውዳሚዎቹ እና ደፋሪዎቹ ሲሞቱ ደግሞ ጥሩ ነገር ሲሰሩ እንደሞቱ ሁሉ ሙሾ እያስወረዱ ሻማ የሚያበሩ ልዩ ፍጥረቶች ናቸው። ስለእውነት እነኚህ ምን ሊባሉ ይችላሉ? በእኔ በኩል እነዚህን ምን እንደምላቸው ስለተቸገርኩ እንደዘፋኙ

ስያሜ አጣሁላት፣

እስኪ ስምአውጡላት ፡፡ ብያለሁ!

በአጠቃላይ እነዚህ ፖለቲከኞች ነን ባዮችና በየፌስ ቡኩ ጥላቻና ልዩነትን ሲሰብኩ የሚውሉ የእነሱ ተቀጽላዎች ለእዚች ሀገር አይበጇትም፡፡ እንደውም ያጠፏታል፡፡ ጎበዝ፤ ከመጥፋታችን በፊት ልንነቃ ይገባል።

አቅመ ቢስ ፖለቲከኛ ነን ባይ መክሊታቸውን ያላወቁ ሰዎችን አምኖ መከተል እና አድርጉ የሚሉትን ማድረግ ትርፉ አንካሳ አህያን እንደመጠበቅ ነው፡፡ እነ ሞረሽ (ስም አይጠሬዎቹ) ሁልጊዜ ጥላቻና ልዩነትን በመስበክ ብቻ ሀገራችንን ሊያሳጡን ነው፡፡ ከዚያም አልፈን እነሱን የፌስቡክ ወሬ ብቻ እያሳመጥን እድንውል አደርገው ለከርሞው በርሃብ ሊጨርሱን ምኞታቸው ነው፡፡ ‹እረ ምን ምኞት ብቻ ፤ ዕቅዳቸውም ይመስለኛል፡፡›

ከእነሱ የፌስ ቡክ ወሬ ተላቀን ሀገራችንን መጠበቅ ደግሞ የእኛ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ትናንት ከባዕዳን ወራሪዎች አባቶቻችን እንዳስጣሉን ሁሉ ዛሬ ከፌስ ቡክ ወራሪዎች ሀገራችንን ልናስጥላት ይገባል፡፡ እውነት እላችኋለሁ እነሞረሽም ሆኑ እኛ የምንሞተው ለወደድነው ነገር ነው፡፡ እነሱ ለጥፋት ሲሞቱ እኛ ለመልካም ነገር ነው የምንሞተው፡፡ ወደ ፊት በታሪክ የምንወሳበት አውድ ግን ለእኛ ኩራት ሲሆን ለእነሱ ግን ሀፍረት መሆኑን አልጠራጠርም፡፡

የፖለቲካ ጠበብት እንደሚሉት ራስን መግዛት እና መቆጣጠር እንዲሁም የመርህ እና የዓላማ ጽናት መጀመሪያው ‹ሀሁ› ነው ፡፡ ይሁን እንጂ በእኛ ሰፈር የሚታዩ ከመክሊታቸው ውጪ ፖለቲከኛ ለመሆን የሚንፈራፈሩ አካላት ራስን መግዛት እና መቆጣጠር እንዲሁም የመርህ እና የዓላማ ጽናት የተሰኙ የፖለተከኛች የመጀመሪያውን «ሀሁ» ፈጽሞ አያውቁትም፡፡ አንድ ቀን ሥራ ሲያጡ በማህበራዊ ሚዲያ ጽፈው ብዙ ተከታይ በማግኘታቸው ብቻ ራሳቸውን እንደፖለቲከኛ የቆጠሩ ከንቱዎች ናቸው፡፡

እነኚህ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች መነሻ እና መድረሻቸው አጥፍቶ መጥፋት ነው፡፡ የሚገርመው ከራሱም ወገን ሆነ ከተቃራኒው ሰው ቢሞት ንብረት ቢወድም ደንታ የለውም፡፡

ባህሪን ፖሊሲ ወይም መርህ ሊገዛው አይችልም፡፡ ሊሞርደው ሊጠግነው ይችላል፡፡ ግን ችሎ በተፈለገው ልክ አያስተካክለውም፡፡ እነኚህ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኛ ፖለቲከኞች አሁን ላይ ህዝብን ከህዝብ የማባላት ሱሳቸው አገርሽቶባቸው ከእነ ሞረሽ ጋር የረከሰ ጋብቻ ፈጽመው ሊያጠፉን ተነስተው ነበር፡፡ በጎሳ ሊያቧድኑን ፈለጉ፡፡ ግን አልቻሉም ፡፡

ጥላቻ ሀገርን አያቀናም፡፡ በተለይም ‹የእኔ ከአንተ ይበልጣል›፤ ‹የእኔ ነገር ሁሉ ትክክል ነው›፤ ‹እኔን ብቻ ስማኝ › ከሚሉና አንዱን አሳንሶ ሌላውን አንኳሰው ከሚመጡ መሰሪዎች እራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ በተለይም አብረን በኖርን ህዝቦች መካከል ኃይማኖትን ከኃይማኖት፤ ጎሳን ፤ከጎሳ፤ ብሄርን ከብሄር በማናቆር ትፍር ለማግኘት ከሚጥሩ የበግ ለምድ ከለበሱ ቀበሮች እራሳችንን ልናድን ይገባል፡፡

በነገራችን ላይ ከየትኛውም ጎሳ ብትሆን ፤ ምንም ምክንያት ብትሰጠው ጎሰኝነትን የሰበክ ዕለት በጉንዳን ጉድጓድ ገብቶ እንደመተኛት ወይም ንብን ከቀፎዋ ድረስ ሂዶ ለመግደል እንደመሞር አልያም በደነበረ ፈረስ ላይ ተቀምጦ የደነበረውን ፈረስ ለማስቆም በደነበረው ፈረስ የነበረን ገመድ አንገት ላይ እንደማጥለቅ ይቆጠራል፡፡ ወይም ራስን በበርሜል በሚፈላ ዘይት ውስጥ እንደመጨመር ነው ፡፡

ምክንያቱም የጎሳ ጥላቻ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ለሌላው ሰብዓዊ ፍጡር ሊኖረው የሚገባውን ኀዘኔታና ርህራሄ ከሰው ልብ ፈልቅቆ አውጥቶ ከአውሬ በባሰ ጭካኔ ይተካዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የተፈጠረው ጥላቻ ሁሉንም ሳይመርጥ እኩል መብላቱ የማይቀር ነው።” ብሎ አብሿሙ ከንፈ ጉደታ ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡

በመጨሻም ፖለቲከኛ ነን፤ አክቲቪስቶች ነን፤ የፌስ ቡክ አርበኞች ነን የምትሉ በሙሉ የእውነት አዋቂ ፖለቲከኛ ከሆናችሁ የፖለቲከኝነታችሁ መለኪያ አንዱና ዋነኛው ዘርፍ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል መቻል ነው፡፡ ስለዚህም ኑሯችንን እንዴት እንደሚሻሻል ጠቁሙን፤ ከቻላችሁ ደግሞ አውርታችሁ ሳይሆን ሰርታችሁ እኛንም ፤ ሀገርንም ለውጣችሁ ምሳሌ ሁኑን፡፡ ሃኪም ነን ካላችሁ እራሳችሁን አክማችሁ እና አድናችሁ አሳዩን፡፡ ነገር ግን አንዳችሁም ይህንን ማድረግ እንደማትችሉ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡” ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎችም ለይልቃል ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸው ስብሰባው ተበተነ።

ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *