“የቴክኖሎጂ ሽግግር በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የካቲት 28/2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ላይ ሳይንሳዊ ገለፃና የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ላይ መንግስት በእቅድና ሳይንሳዊ በሆነ አሰራር ተደግፎ ከመስራት ይልቅ ስራዎች ያለእቅድ በዘመቻ የሚከናወኑ በመሆኑ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር የተጠበቀውን ያክል በአገሪቱ እንዳልተሸጋገረና አገሪቱ በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች በተደረገው ገለጻና ውይይት ላይ የሰላ ትችት ተሰንዝሮ መግባባትም ተደርሶበታል። በመሆኑም የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዋና ዋና እንቅፋቶችና ቁልፍ መፍትሄዎቹ ምንድን ናቸው?
በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካልና ኢንዱስትሪያል ትምህርት ክፍል ተመራማሪና መምህር የሆኑት እንደ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ትንታኔ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት አንድን የዳበረ ቴክኖሎጂ ካደገበት ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኖሎጂያዊ አውድ ወስዶ ወደ ሌላ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክሎጂያዊ አውድ ማላመድ ሲሆን፤ አንድ ቴክኖሎጂ ተሸጋገረ የሚባለው ተጠቃሚው ቴክኖሎጂውን በደንብ አውቆ በሚገባ ሲጠቀምበት፤ ለአካባቢው ተስማሚ አድርጎ ሲቀዳው፤ ቴክኖሎጂው ሲበላሽ መጠገንና መስራት ሲቻል፤ ማሻሻያ (ሞዲፊክ) ሲያደርግ እና በተቀባዩ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክሎጂያዊ አውድ ውስጥ ማላመድና ማሰራጨት ሲቻል ነው።
የቴክኖሎጂ ሽግግር በኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ እየተሸጋገረ ነው ብለን ብንጠይቅ እንደኔ አይመስለኝም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገሪቱ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የቴክኖሎጂ ሽግግር መሻሻል ቢያሳይም፤ ለአብነት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ መካከል በአገሪቱ እድሜ ጠገብ የሆነውን የሲሚንቶ ፋብሪካን ብንወሰድ ቴክኖሎጂውን ወደኛ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክሎጂያዊ አውድ አላላመድነውም አላሰራጨነውም።
ስለዚህ የሲሚንቶ ፋብሪካ ቴክኖሎጂ በአገራችን ተሸጋግሯል ወይ ቢባል አልተሸጋገረም። በመሆኑም መሰል ቴክኖሎጂዎችን በአገሪቱ ለዘመናት ብንጠቀምም ቴክኖሎጂውን ግን ወደ አገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሮ እየተጠቀምንበት ስላልሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ዝቅተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
በተመሳሳይ የዘራ ኢንጂነሪንግና ማኑፋክቸሪንክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የፀረተባይ ማምረቻ ፋብሪካ መስራችና ስራ አስኪያጅ እንዲሁም በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የድህረ ምረቃ ተማሪዎች አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር እያሱ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ በአገሪቱ በቂ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደለለ ገልጸው፤ ምንም እንኳን በአገሪቱ በቂ የቴክኖሎጂ ሽግግር ባይኖርም በቀላሉ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉ አብዛኛው ማህበረሰቡ የሚጠቀሟቸው ምርቶች ከውጭ ተመርተው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው። በመሆኑም ማህበረሰቡ በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ተደግፈው የሚመረቱ ምርቶችን ለመጠቀም እምነት እንዳይኖረውና በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ የተመረቱ ምርቶች እንዳይበረታታ የሆነበት ነባራዊ ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል።
በሌላ በኩል የአይኮግላብ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አሰፋ በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂ በአገሪቱ እየተሸጋገረ ያለው ማህበረሰቡ በተፈጥሮ በተለያዩ ሴክተሮች ላይ በሚሰራበት የስራ ዘርፎች በአንድንድ የስራ ባህሪ አስገዳጅነት የእውቀት ሽግግሩ ይካሄዳል።ነገርግን አንድ ቴክኖሎጂ ታቅዶበት፣ እውቀት ተኮር ሆኖ፣ ጉዳትና ጥቅሙ ተለይቶ ወደ አገሪቱ እየተሸጋገረ ያለበት አግባብ ባለመኖሩ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በሀገሪቱ የተሳካነው ለማለት አያስደፍርም። እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በእጅጉ ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ መሆኑን ይናገራሉ።
የአገራችን የቴክኖሎጂ ሽግግር ችግሩ አንድ አይደለም እንቅፋቶቹ ብዙ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፤ ማንኛውም የቴክኖሎጂን ሽግግር የሚያዘገይና የሚያግድ ነገር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅፋት እንደሆነ ይቆጠራል። ስለዚህ የህግ፣ የመሠረተ ልማት፣ የተግባቦትና ባህላዊ እንቅፋቶችና መሰናክሎች ዋና ዋና የአገራችን የቴክኖሎጂ እንቅፋቶች ናቸው።
የፋይናንስ ችግር፣ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ በድርጅት ውስጥ ያለ የግል ግንኙነት፣ የተንዛዛ ድርጅታዊ አሰራር፣ ውሳኔ ሰጭ የሆኑ አመራሮች በቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት በቂ የቴክኖሎጂ እውቀት አለመኖር፣ የአዋቂዎች እምቢተኝነት እና ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ተግዳሮቶች በአገራችን የተሳካ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዳይኖር ተጨማሪ እንቅፋቶች ናቸው። በአጠቃላይ የአመለካከት ችግር አገራችን በቴክኖሎጂው ዳዴ እንድትል አድርጓታል ብለዋል።
ፕሮፌሰር እያሱም በተመሳሳይ በአገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር የተሳካ እንዳይሆን ዋና ዋና ችግሮች የሚሉት፤በቴክኖሎጂው ዘርፍ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት አለማግኘታቸው፤ ህፃናትን ከልጅነት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በቴክኖሎጂ ኮትኩቶ ለማሳደግ የሚረዳ ፖሊሲ አለመኖር፤ ህብረተሰቡ ስለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን፤ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚያስተምሩ መምህራኖች የተለያዩ ስልጠናዎችን አለማግኘት እና መንግስት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ለሚሰሩ ዜጎች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ጥቂቶቹ ናቸው። በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አንችልም የሚል የስነ ልቦና የበታችነት ወይም የባርነት አመለካከት አገሪቷን በቴክኖሎጂ ባርነት ስር እንድትወድቅ አድርጓታል ይላሉ።
አቶ ጌትነት በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር በአገሪቱ የተሳካ እንዳይሆን ምክንያት የሚሏቸው፤ በአለም ላይ እየፈለቁ ያሉ ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ስራዎችን ወደ አገሪቱ አውድ ቀይሮ የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል የእውቀትና የክህሎት ውስንነት መኖር። ማህበረሰቡ ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ እያሸጋገረ ያለው በትምህርት ተደግፎ ሳይሆን በልምድ መሆኑ።
እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ተቋማት ቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን ፋይዳ በግልጽ ያለመረዳት ችግር መኖር። በአጠቃላይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት ሰጥተው አንድን ቴክኖሎጂ እንዴት አድርገን አገር በቀል እውቀት እናድረገው በሚል ተጨባጭ ግብ አስቀምጠው ስለማይሰሩ፤ ህብረተሰቡ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለዘመናት ቢጠቀማቸውም የራሱ ሳያደርጋቸው ቆይቷል ብለዋል።
በባለሙያዎቹ እምነት በአገሪቱ የተሳካ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር መከናወን ያለባቸው በርካታ ተግባራቶች አሉ። በዋናነትም፤ ወደፊት ለመራመድ ማነቆ የሆነውን የአመለካከት ችግርን መቅረፍ ያስፈልጋል። እንዲሁም የቴክኖሎጂ በር ጠባቂዎችን ማደራጀት የሚያስፈልግ ሲሆን፤ እነዚህ ቅን አገር ወዳድ ግለሰቦች ባካበቱት እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ባላቸው ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትስስርና ግንኙነቶች ምክንያት ለተፈላጊ ቴክኒካዊ መረጃዎች ቅርብ በመሆናቸው በፍጥነት ለሚለዋወጠው ቴክኖሎጂ ንቁዎች ናቸው፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ምክር ይሰጣሉ፤ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ ገበያ ተመጣጣኝነቱንና ተስማሚነቱን አይተው ተወዳዳሪ ጥቅሙን ያጣራሉ፤ ልብ የሚያማልሉ ማስታወቂያዎችን በብስለት ይመዝናሉ።
ስለዚህ የቴክኖሎጂ ሽግግር በኢትዮዽያ ዘለቄታዊ ዕድገት እንዲኖር የሚያስችሉ ሲሆን፤ በትንሽ ኃይል ከፍተኛ ምርት በማምረት ሰፊ የሆነ የሀብት ሥርጭት እንዲኖረ ያደርጋል። እንዲሁም በአገሪቱ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች እነዚህን እድሎችና ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ባላቸው ቁርጠኝነትና የቴክኖሎጂ አስተዳደር ችሎታ ስኬታማነትን እንዲጨምሩ የሚያደርግ ነው። እንዲሁም ነባርና እና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዋና ተዋናዮች መሆን አለባቸው።
በተጨማሪም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ምርት የመተካት ሥራ የፖሊሲዎቻችን ተቀዳሚ ዓላማ ከሆነ እንደ ቻይና በአጭር ጊዜ አመርቂ የቴክኖሎጂ ዕድገት ማምጣት የሚቻል ሲሆን፤ አገር በቀል እውቀቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ለመለየትና ለመገምገም የሚረዱ ዘዴዎች መመቻቸት አለበት። የአገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ለማሻሻል የመሠረተ ልማት፣ የብድር አገልግሎት፣ የምርምር በጀት ወ.ዘ.ተ መመቻቸት ያለበት ሲሆን፤ በምህንድስና ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ ምርምሮች አገር በቀል እውቀቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ለማሻሻል ትኩረት ማድረግ አለበት።
በአጠቃላይ በአገሪቱ የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የትምህርት ሚኒስቴር፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በ ”ሶስትዮሽ ትስስር” እጅ ለጅ ተያይዘው መስራት ይኖርባቸዋል። እንዲሁም በዘመቻና በፖለቲካዊ ውሳኔ ሳይሆን በአገሪቱ በጥናትና በምርምር የተደገፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊኖር ይገባል።
ይሄን ማድረግ ከተቻለ አገሪቱ ያላትን የተማረ ወጣት ኃይል፣ ተፈጥሮ ሀብትና ብዝሀነት በመጠቀም በጥቂት አመታት ውስጥ አገሪቱን የቴክኖሎጂ ደሴት ማድረግ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም። ነገርግን አገሪቷ በማንኛውም ዘርፍ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በጥራትና በአይነት ደረጃውን በጠበቀና በተሳካ ሁኔታ በማሸጋገር የአደጉ ሀገሮች የደረሱበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ተርታ በማሰለፍ፤ ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ካልቻለች አገሪቷ ለዘመናዊ ባርነት ተገዥ መሆኑ አይቀሬ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በሶሎሞን በየነ